Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለድህነት ትግሉ ስኬት …

0 306

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለድህነት ትግሉ ስኬት …

አባ መላኩ

የድህነት ትግል የህዝቦች  ትብብርንና  አብሮነትን ይጠይቃል።  የድህነት ትግል እንደነጻነት ትግል የአንድ ወቅት ትግል ሳይሆን  ረጅምና ውስብስብ ነው። በዕርግጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የነጻነት ትግል ረጅምና እልህ አስጨራሽ የነበረ ቢሆንም የድህነት ትግሉ ደግሞ ከዚያም የከፋ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። ምክንያቱም ድህነት ከአገራችን ጋር ለዘመናት በጥብቅ ቁርኝት የዘለቀ መሰረተ ሰፊ የሆነ ነው። በዕርግጥ የድህነት ትግል ህይወትና አካል መገበርን ባይጠይቅም የሁሉንም ዜጋ ርብርብን ግን የሚጠይቅ  ነው። ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት የተናገሯት አንዲት ነገር ውስጤን ሰርስራ ገብታለች። “እንኳን በየሰፈሩና በየጎጡ ተከፋፍለን ይቅርና አንድም ሆነን ዳገቱን መግፋት አልቻልንም” ሲሉ የአንድንትንና የትብብርን አስፈላጊነት አስምረውብታል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን ማጠናከር በመቻላቸው በየዘርፉ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው  ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ናቸው።  

ዘመኑ ፈታኝ የሆነ ዓለም ዓቀፋዊ የሆነ  የውድድር ወቅት ነው። በዚህ ፈታኝ በሆነ  የውድድር ወቅት በድል ለመዝለቅ  ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥምረት ትልቁና ብቸኛው የጥንካሬ ምንጭ ነው።  ለዚህ ጥሩ ማሳያ  አገራችን ናት።  አገራችን ባለፉት 26 ዓመታት በስኬት  መዝለቅ የቻለችው  በጋራና  በአንድነት መጓዝ በመቻላችን ነው።  የአገራችን የፌዴራል ስርዓት ምንም እንከን የለበትም የሚባል ባይሆኑም ለዘመናት ለዘለቁ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘርፈ ብዙ  ችግሮች መፍትሄ አስገኝቷል።  ባለፉት  26 ዓመታት አገራችን በስኬት ላይ እንድትረማመድ  ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ አቅም የፈጠረላት ይህ የፌዴራል ስርዓት  እንደሆነ  ሊሰመርበት  የሚገባ  ጉዳይ ነው። እንደእኔ እንደኔ  የፌዴራል ስርዓቱ  የህዝቦችን  ዴሞክራሲያዊ  መብቶች መረጋገጥ መንስዔ  ከመሆኑ ባሻገር  ቀንደኛ ለሆነው የህዝቦች  ችግር “ድህነት” ጭምር  መፍትሄም ሆኗል። የአገራችን የስኬት ሁሉ ካስማ የፌዴራል ስርዓቱ ነው ማለት ይቻላል።

ድህነት የችግሮቻችን ሁሉ ቁንጮ ነው።  ታላቁ መሪ በአንድ ወቅት ድህነትን በተመለከተ እንዲህ ብለው ነበር።  ከጠላቶቻችን በላይ የከፈው ጠላታችን ድህነት እንደሆነና ይህን የከፋ ጠላታችንን በጋራ መታገል እንደሚገባን አሳስበው  ነበር።   እኚህ ታላቅ መሪ  ከድህነት ለመውጣት የሚደረገው ትግል እንዲጠናከርና  ድህነታችን  ቁጭት እንዲፈጥርብንና የጸረ ድህነት ትግሉን   ለማፋፋም  ሲሉ “እጅና  እግር  ይዘን፣  የሚያስብ  ጭንቅላት  ይዘን፣  በቀላሉ  ሊለማ  የሚችል መሬት  ይዘን፣  ስንዴ  እየለመንን   እንዴት  እንኖራለን”  ብለው ነበር። ድህነትን ማሸነፍ ከቻልን  የአገራችን ችግሮች መቀረፍ እንደሚቻል ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከነበረው ሁኔታ  መረዳት ይቻላል።

ኢትዮጵያ  ከድህነት ለመውጣት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን በማድረግ ላይ  ያለች አገር እንጂ ጨርሳ ድህነትን ያጠፋች አገር አይደለችም። አንዳንድ  አካላት  አገራችን እያስመዘገበች ያለችውን የኤኮኖሚ ዕድገት  በተሳሳተ መንገድ  የተረዱት ይመስለኛል። እነዚህ ወገኖች የሚያነሱት ሃሳብ ኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች ከሆነ ለምን ደሃ መንገድ ላይ ይታያል፣ ለምን ድርቅ ይከሰታል፣ ለምን ሁሉም ተመሳሳይ ገቢ አይኖረውም፣ ለምን እርዳታ ይጠየቃል  ወዘተ  ዓይነት ነው።

እንደኢትዮጵያ ያለ  ዘርፍ ብዙ ችግሮች  የነበሩባት አገር  ባለፉት  ሁለት አስርት ዓመታት ብቻ  እድገት በማስመዝገቧ ከውስብስብ  ችግሯ  ትላቀቃለች  ማለት የዋህነት ነው። በኢትዮጵያ  ይቅርና በምዕራባዊያኖችም ቢሆን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል  ዜጎች አሁንም የዕለት ጉርስና መጠለያ አጥተው በጎዳና ሲንከራተቱ እንዲሁም በርካቶች በመንግስት ምጽዋት የሚኖሩ እንደሆነ ማየት ይቻላል። በየትኛውም አገር ቢሆን ድህነትን መቀነስ እንጂ ድህንትን ጨርሶ ማጠፋት አይቻልም። አገራችን የፈለገችውን ያህል ብታድግና ብትመነደግም  ደሃ መኖሩ አይቀርም።  በርግጥ  የድህነት ደረጃና አይነቱ እንደሚለያይ ከግንዛቤ መውሰድ አስፈላጊ ነው። አሁን ላይ የአገራችን ድህነት መጠን ከግማሽ በላይ ቀንሷል።

የፌዴራል ስርዓቱ ለአገራችን የዕኩልነትና የዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት ከመሆኑም ባሻገር አሁን እየተመዘገበ  ላለው ፈጣን  የኢኮኖሚ ዕድገትና ፍተሃዊ ተጠቃሚነትም  መሰረት ነው።  በአገራችን ዘላቂ  ሰላም  በመስፈኑ  መንግስትና ህዝብ ትኩረታቸውን  ወደ ልማት በማዞራቸው ባለፉት አስራ አራት  ዓመታት በአገራችን  ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ባለሁለት አሃዝ  እድገት በመመዝገብ ላይ ነው። አገራችን እንዲህ ያለ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው  እድገት ማስመዝገብ የቻለችው በርካታ ጠንካራ ኤኮኖሚያዊ አቅም አላቸው የሚባሉ የአውሮፓ አገራት ጭምር በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በነበሩበት እ ኤ አ በ2007/8  ወቅት  ጭምር ነው።  በርካታ የምጣኔ ሃብት  ተንታኞች  የኢትዮጵያ ፈጣን ልማት ሚስጢር የትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ  ውጤት  እንዲሁም መንግስት ህብረተሰቡን ለልማት ማነሳሳት በመቻሉ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

መንግስት ህብረተሰቡን ከድህነት በፍጥነት ሊያወጣ የሚችለውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ መተግበር በመቻሉ አሁን ላይ ከሃያ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ዜጎች ከድህነት ማላቀቅ ተችሏል። የአገራችን እድገት  ከ80-85 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ   በሚኖርበት ገጠረን  መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከልማቱ  አብዛኛውን  የህብረተሰብ  ክፍሎች  ፍተሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።  መንግስት የተገበረው  ፖሊሲ የግብርናውን ክፍለ ኤኮኖሚ ማንቀሳቀስ ሲጀምር ሁሉንም ክፍለ ኤኮኖሚዎች ተንቀሳቅሰዋል።  በአገራችን በሁሉም አቅጣጫዎች ፈጣን ለውጥ በመመዝገብ ላይ ነው። መሰረተ ልማቶችና ማህበራዊ መገልገያዎች  በመስፋፋት ላይ ናቸው።  

ዛሬ ላይ ከ30 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው። የበርካታ የአፍሪካ አገራት የህዝብ ቁጥር  ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ቁጥር እጅጉን ያንሳል። በባለፉት ስርዓቶች አርብቶ አደር የሚበዛባቸው አካባቢዎች እጅግ የተረሱና መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው አካባቢዎች ነበሩ። አሁን ላይ  መንግስት በሰጠው  ልዩ ትኩረት እነዚህ አካባቢዎች  እጅግ የሚገርም ለውጦችን ማስየት ጀምረዋል። ባለፉት ስርዓቶች የረባ ሁለተኛ ደረጃ የሌላቸው አካባቢዎች ዛሬ ላይ  ዩኒቨርሲቲዎች ተቋቁሞባቸዋል። ይህ ነው በሰው ሃብት ልማት ማለት። ይህ ነው ኢንቨስትመንት ማለት ነው።

በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም አገራችን አዎንታዊ ለውጦችን አስመዝግባለች። በማስመዝገብም ላይ ትገኛለች።  የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ነው። እንኳን እንደእኛ ያለ ለዴሞክራሲ ስርዓት ጀማሪ አገር ይቅርና  ሶስትና አራት መቶ ዓመታት የዴሞክራሲ ባህል አለን የሚሉት ምዕራባዊያን  የዴሞክራሲ ስርዓታቸውን በየጊዜው  ጉድለቱን  በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃዎች ሲወስዱ ይታያሉ።  

 

የአገራችን  የፌዴራል ስርዓት  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ አድርጓቸዋል። ባህላቸውን ማሳደግ አካባቢያቸውን ማልማት  ችለዋል። ይህንና ይህን ስርዓት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አስተሳሰብ፣ ትምክህትና ጠባብነት  እጅጉን  እየተፈታተኑት ነው። እነዚህ መሰረታዊ የአገራችን ችግሮችን ለማስወገድ  የጋራ ትግልን ይጠይቃሉ። መልካም አስተዳደርን  ለማስፈን መንግስት ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ  አሳይቷል። ከጥልቅ ተሃድሶው  ወዲህ  በርካታ እርምጃዎችንም በመውሰድ ላይ ነው። መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው በሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ በመሆኑ ሁሉም  የበኩሉን ድርሻ  ሊወጣ ይገባል። ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጠባብነትና ትምክህት ለስርዓቱ አደጋዎች ብቻ ሳይሆኑ ለአገራችንም ህልውና ፈታኝ በመሆናቸው ሁላችንም  በጋራ  ልንታገላቸው  ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy