Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለ24 ሰዓት የማይዝሉ እጆች፤ የማይከደኑ ዓይኖች፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድሱ አንደበቶች

0 443

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዚህ ሥፍራ ለ24ሰዓት የማይዝሉ እጆች፤ የማይከደኑ ዓይኖች፤ የፀሐይ ግለት የማያዳክማቸው ኢትዮጵያውያን፤ ከድህነት ጋር ፍልሚያ የገጠሙ ጀግኖች፤ የአገር አደራን የተሸከሙ ጫንቃዎች የበላይነት አላቸው፡፡ ክንደ ብርቱዎች በዚህ ሥፍራ ግብግብ ገጥመዋል፤ ድህነትን አጥፍቶ ዕድገትና ስልጣኔን በማሰብ፤ አዲስ ታሪክ ለመክተብ ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡

እነሆየታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰሞኑን በአገሪቱ የሚገኙ የሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች እና ከፍተኛ አመራሮች፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተወካዮች፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ የክልልና የከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ በአገሪቱ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ኃላፊዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ የአካል ጉዳት ላይ የሚሰሩ ማህበራት ተወካዮች፣ የግል ትምህርትና ሙያ ተቋማት ማህበራት ተወካዮች እና በአገሪቱ የሚገኙ የግል እና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሚገነባበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡

በጉብኝቱ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደጀኔ አየለ አንዱ ናቸው፤ የህዳሴው ግድብ አዲስ ዕይታ የፈጠረ እና በሥነ ጽሑፋችንም ላይ ሌላ የቀለም ቀንዲል በማስቀመጥ በር ከፋች የሆነ ብሄራዊ ኩራታችን ነው ይላሉ፡፡

በእርሳቸው እምነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለትምህርት ስርዓቱ እንደ አንድ ታላቅ ቤተሙከራ የሚያገለግል ሲሆን፤ ለአገሪቱ እና ዓለም አቀፍ ምሁራን ተጨማሪ የምርምርና የትኩረት ሥፍራ ይሆናል ፡፡ ባለፈው ዓመት በዚህ ቦታ ተገኝተው ነበር፡፡ ያኔየነበረው የግንባታ ደረጃ ከዛሬው ጋር ሲያነፃፅሩት ከጠበቁት በላይ መፋጠኑ አግራሞት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሌላኛው የአድዋ ድላችን ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ጣሊያን አገራችን ስትወር በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉስ ለተባበሩት መንግሥታት አቤት ሲሉ፤ አብዛኛው የዓለም ህዝብ ቀልዶባቸዋል፡፡ በኋላ ግን ህዝባቸውን አስተባብረው ድል ተጎናጽፈዋል፡፡›› የሚሉት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለህዳሴው ግድብ በርካታ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በር ሲያንኳኳ ምላሽ ሲያጣ፤ የራሱን ህዝብ አስተባብሮ ታሪክን ቀይሮታል። ልክ እንደ አድዋ ታሪክ ሲሉ የታሪክ ግጥምጥሞሹን ይናገራሉ፤ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ጴጥሮስ፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቤየል ቤልቾክ ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ሲጎበኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በእርሳቸው ሃሳብ የህዳሴው ግድብ መጠናቀቁን ብቻ አይጠብቁም፤ ገና ሌላ የህዳሴውን ግድብን የመሰሉ ፕሮጀክቶችን ይናፍቃሉ፡፡ የጋምቤላ ከተማን ለሁለት ክፍሎ የሚሄደው የባሮ ወንዝም ልክ እንደ አባይ ተገድቦ ወደ ሱዳን ከመሰደዱ በፊት ኃይል እንዲያመነጭ ይመኛሉ፡፡ «እንዲሆን አሁን የተጀመረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል ማጠናቀቅ እና ተጨማሪ አቅም መገንባት ያስፈልጋል» የሚል አቋም አላቸው፡፡ ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ገጽታ ከሚጠበቀው በላይ የሚቀይር እንደሆነም ያምናሉ፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አምሳሉ በድሞ ደግሞ፤ የህዳሴው ግድብ እንዲሁ በቀላሉ ግድብ ተብሎ የሚገለፅ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ከደም እና አጥንታቸው የተዋሃደ የማንነት አሻራቸው ያረፈበት፤ ዘላለማዊ ኩራት የሚያላብስ ፕሮጀክት ነው ይላሉ፡፡ አሶሳ ዩኒቨርሲቲም የህዳሴውን ግድብ ዲዛይን መለያ (ሎጎያደረገው ሲሆን፤ ይህም በሰዎች አስተ ሳሰብ እና ሥነልቦና ላይ የሚኖረው አንድምታ በእጅጉ የላቀ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡ የህዳሴው ግድብ ብዙ ታሪኮችን የሚያድስና ያልተጠበቀ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንደሚያመ ጣም ይተነብያሉ፡፡

ወይዘሮ ሰዓዳ ከዲር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው፤ የግድቡ ግንባታ ሂደት ከሚጠበቀው በላይ አስደሳች እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ «ግድቡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ የነካው እና የሁሉም ላብ ያረፈበት በመሆኑ ወደር የሌለው ደስታ ያጎናጽፋል፡፡ ግድቡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ተምሳሌት የሚሆን፤ የአገሪቱን ገፅታ በተሻለ መልኩ የሚቀይር በመሆኑም ልዩ ያደርገዋ» ባይ ናቸው፡፡ በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረትም ያለጥርጣሬ እንዲሳካ ግድቡ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ይላሉ፡፡

«በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ለአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ግንባታ እና አስተሳሰብ ለመቅረጽ የራሱ ድርሻ አለው፡፡ የትናንቱ ትውልድ ኢትዮጵያን በድህነቷ ነበር የሚያውቃት፤ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ይህን ግድብ እንደ አንድ የአገሪቱ የምጣኔ ሃብት አድርጎ ስለሚማር የራሱን አስተዋጽ ያበረክታል›› ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው፤ ስለአክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ጀጎል ግንብ እና ሌሎች የአገሪቱን ታሪካዊ ቅርሶች የሚያወድሱ የኢትዮጵያውያን አንደበቶች በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ቅርስ አግኝተዋል ሲሉ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአገሪቱ ታላቅ ቅርስ እንደሆነ ያስረዳሉ፡

«በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ላይ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካላትን ወክለን በቦታው ተገኝተናል» ያሉት ሚኒስትሩ፤ የመላው የአገሪቱ ዜጎች ዋነኛ የዕለት ተዕለት ጉዳይ በመሆኑ፤ እስከፍፃሜው ድረስ በትምህርት ዘርፍ ያሉት ሁሉ የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ በላቀ መልኩ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት፡፡ በአሁኑ ወቅት በግድቡ ግንባታ ላይ የሚሳተፉ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውያን ሲሆኑ፤ ይህም የትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የለውጥ መሳሪያ እንደሆነ ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ፤ ግድቡ በተያዘለት መርሐ ግብር እና ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እስካሁን ለ24 ሠዓት ግንባታው በመከናወን ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የመላው ኢትዮጵውያን ሕዝብ ተስፋ በዚህ ግድብ ላይ የተንጠለጠለ ከመሆኑም በተጨማሪ እውን ሆኖ ማየቱ ካለው ጉጉት አኳያ ታላቅ መስዋዕት እየከፈለ መሆኑ ይገባናል ይላሉ፡፡ ይህን የህዝብ እና የአገር አደራ በታላቅ ወኔ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዓይን እና ጆሮ ብሎም መላ አካላቱ ከዚህ ሥፍራ እንዳለ እንረዳለን፡፡ ስለሆነም የዚህን ህዝብ የማይነጥፍ ድጋፍ እና ሞራል ፍፃሜውን ለማግኘት መቃረቡንና ይህ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ሐውልት ሆኖ እንደሚቀጥል በመጠቆም፤ በትምህርት ሴክተሩ ላይ ያሉ አካላት ግድቡ ፍትሐዊ አጠቃቀምን መርህ ያደረገ ብሎም ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ ማማ የሚያመጥቃት ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ከማንም በላይ ሊሰብኩ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy