Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማህበራዊ አገልግሎቶችን በፍትሐዊነት የሚያዳርስ መንግሥት

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማህበራዊ አገልግሎቶችን በፍትሐዊነት የሚያዳርስ መንግሥት

                                                       ደስታ ኃይሉ

የኢፌዴሪ መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እያካሄደ ያለው ማህበራዊ አገልግሎቶች ፍትሐዊና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚገኙ ናቸው። ይህ የመንግስት ተግባር ትክክለኛ መሆኑን በቅርቡ የዓለም ባንክ ለአገራችን በሰጠው ድጋፍና ብድርና ተረጋግጧል።

መንግስት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ላለፉት 26 ዓመታት በሚገባ ሰርቷል። የተገኘው ለውጥም ቀላል የሚባል አይደለም። እጅግ ሰፊ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት ከ26 ዓመት በፊት አገርን አዋርዶ፣ ህዝብን እያሸማቀቀ ለተመፅዋችነት የዳረገን ብሎም ለዘመናት እንደ ክት ዕቃ በዚህች ሀገር ተጎልቶ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ጠላት ጋር ግልጽ ውጊያ መክፈቱ ይታወሳል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም ያወቁበት ነው፡፡ ይህን ጠላት ለመዋጋትም የሀገራችን ህዘቦች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በመንግስት ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ጀመሩ። በዚህም ውጤት ማምጣት ቻሉ። ዛሬም ወገብ በሚያጎብጥ ዕቅድ ይዘው ህዳሴያቸውን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና እያሉ ነው።

እንደሚታወቀው ዕድገቱ በየክፍላተ-ኢኮኖሚው ሲመነዘር በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የግብርና ዘርፍ በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የ8 በመቶ ዕድገት የሚያስመዘግብ ሲሆን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎችም በቅደም ተከተል ቢያንስ የ19.8 በመቶ እና የ10 በመቶ አማካይ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ የዕድገት አማራጭን በሚመለከት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አርሶ አደሮች ውጤት ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት የዋና ዋና ሰብሎችን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚቻል ዕቅድ ተይዟል፡፡ በዚህም መሠረት የግብርናን ዘርፍ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በመሠረታዊ አማራጭ ከነበረው 8 በመቶ ወደ 11 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡ ለዚህም በዋናነት አስተዋፅኦ የሚያደርገው ዋና ዋና የሰብል ምርቶች በ16 በመቶ እንደሚያድግ ተተንብዮዋል፡፡

የእነዚህ የዋና ዋና የሰብል ምርቶች ከጠቅላላው የግብርና ምርት ተጨማሪ እሴት ያላቸው ድርሻ በአማካይ 40 በመቶ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ምክንያት ይህ የዕድገት ጭማሬ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ላይ ሊኖረው የሚችለው የግብረ መልስ አስተዋጽኦ ሳይካተት በግብርና ዕድገት ምክንያት ብቻ በዕቅዱ ዘመን አማካይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ የዕድገት አማራጭ 12 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚደርስ ተተንብዮዋል፡፡

ይሁንና የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቃኘው በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ ላይ በመመሥረት ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርመሽን ዕቅድ ዘመንም ግብርና በጥቅሉ ሲታይ ዋና የዕድገት ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የላቀ ዋጋ የሚያወጡ የግብርና ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት ያገኛሉ፡፡

እናም በዕቅድ ዘመኑ በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ የ11 በመቶ አመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የማረጋገጥ አቅጣጫ መከተል ለአገራችን ህዳሴ መረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በመጀመሪያ የዚህ ዓይነት ፈጣን ዕድገት የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞው አንዱ ምዕራፍ የሆነው ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ላይ በ2017 ዓ.ም ለመድረስ ወሳኝ ነው፡፡

ስለሆነም የህዳሴ ጉዟችን አንዱ ምዕራፍ በስኬት ለማጠናቀቅ በዕቅዱ ዓመታት ፈጣን ዕድገቱን ማስቀጠል አማራጭ የለውም፡፡ በተያያዘም ፈጣንና ፍትሃዊ ዕድገቱ ለህዳሴ ጉዞው መፋጠን ይበልጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዜጐች እያሳዩት ያለው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ተሳትፎ ጥረታቸው በርግጥም ፍሬ እያመጣ መሆኑንና ከዚህ ፍሬም ተጠቃሚ መሆናቸውን በተግባር እያረጋግጡ በመምጣታቸው ነው፡፡

በመሆኑም በህዳሴ ጉዟችን ዙሪያ እየተፈጠረ የመጣው አገራዊ መግባባት እየጐለበተ ሊሄድ የሚችለው ዜጋው ውጤት እያየና ተጠቃሚ እየሆነ ሲመጣ በመሆኑ ፈጣንና ፍትሃዊ ዕድገቱን ማስቀጠል በቀጣይም መሠረታዊ አቅጣጫ ነው፡፡ ፈጣን ዕድገቱ መሰረታዊ ስትራቴጂ የሆነበት ሁለተኛው ምክንያት ማህበራዊ አገልግሎቶችንና የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችን ለዜጐች በጥራት የማስፋፋት አቅማችን ለማጐልበት ያስችላል፡፡

ሶስተኛው ምክንያት የሚታየውን ድህነትና ሥራ አጥነት በመቅረፍ ረገድ ፈጣንና መሰረተ-ሰፊ ዕድገቱ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑ ነው፡፡ የያዝነውን የ11 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሰፊ መሠረት ኖሮት እንዲቀጥል የሚጠበቅ ቢሆንም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚመዘገበው ከፍተኛ እመርታ እና በኢኮኖሚው አወቃቀር የሚታየው መሠረታዊ ለውጥ ልዩ መለያዎቹ እንደሚሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅዱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ እመርታ በማምጣት በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ሀገራችንን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ማድረግ እና በአጠቃላይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከመጀመሪያዎቹ ቀዳሚ ሀገሮች ምድብ ለማሰለፍ በተቀናጀና በተደራጀ ጥረት መሳካት ያለበት አገራዊ ራዕይ አካል መሆኑን ታሳቢ ያደርጋል፡፡

ታዲያ ሀገራዊ ራዕዩ መሳካቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እና ጥራት ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባ፣ መንግሥትና ሕዝብም ከሁሉም የላቀ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚታዩ ዋና ዋና እንቅፋቶችን ለመፍታት ለዘርፉ ድጋፎችን እንዲያመቻቹና ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ይጠበቃል፡፡

በዚህም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አሁን ካለው ድርሻ በአራት እጥፍ እንዲጨምር በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተመራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ታቅዷል፡፡ በዚህም መሠረት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በ2007 ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የነበረውን የ4 ነጥብ 5 በመቶ ገደማ ድርሻ በአራት እጥፍ በማሳደግ በ2017 ዓ.ም ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ለማድረግ ታቅዷል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ከፍ ብሎ እንደተገለፀው በላቀ ፍጥነት የሚያድግ ቢሆንም መነሻ መሠረቱ በጣም ጠባብ በመሆኑ በትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት ስራው የመጨረሻ ዓመት (በ2012) ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት የሚኖረው ድርሻ 8 በመቶ አካባቢ ይሆናል፡፡

በመሆኑም በሚቀጥሉት ዓመታት ይረጋገጣል ተብሎ የሚጠበቀው የ11 በመቶ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተመራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በጉልህ ማምጣት የሚያስችል ነው፡፡ የእነዚህ ውጤቶች ድምር እይታ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ትክክለኛ ስትራቴጂና ፖሊሲን ይዞ በሚጓዝ ልማታዊ መንግስት እየተመራች ማህበራዊ መስኮችን ጨምሮ ሁሉንም ዘርፎች በፍትሃዊት ለህዝቡ እየተዳረሰ መሆኑን ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy