Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን በጨረፍታ

0 371

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን በጨረፍታ

                                                       ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ ትርጉም ያላቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነባች ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ አሁን ካሉበት የግንባታ ቁመናቸው ከፍ ብለው ሲጠናቀቁ የአገራችንን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉና በልማቱ ላይ በታታሪነት እየተሳተፈ ያለውን ህዝብ በፍትሃዊነት መጥቀም የሚችሉ ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው በፈጣን ዕድገት ላይ ባሉት ታዳጊ ሀገር ለሚገኙ ዜጎች ኤሌክትሪክ ብርሃንማ ጉልበትም ነው፡፡ እናም ከከተሞች ዳርቻ ፈቅ ሳይል ዘመናትን ያስቆጠረው የሀገራችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተደራሽነት ወሰኑን ከቀን ወደ ቀን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡

መላ ህይወቱን ከኩራዝ ጋር አቆራኝቶ “መብራት አይንሳችሁ” በሚል ብሂል የኤሌክትሪክ ብርሃንን ከሩቅ ይናፈቅ ለነበረው አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ምኞቱን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በመከናወን ላይም ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ለልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለአቅርቦቱ የተሰጠው ትኩረትም ድርሻው የጎላ ነው፡፡ ኃይል ለማቅረብ የየወቅቱን የልማት ጥያቄዎች ከመመለስ ባለፈ የዘርፉን ሥራ በማስፋትና በማቀላጠፍ ከድህነት ነፃ የሚያወጣ የሀገሪቱን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተቃኘ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም የሀገሪቱ ኢነርጂ ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡

የፖሊሲው ዓላማ የሀገሪቱን የኢነርጂ ሀብት ከአጠቃላይ የመንግሥት የልማት ስትራቴጂ አኳያ ማጎልበትና ሥራ ላይ ማዋል፣ ሌሎች የየአካዳሚ ዘርፎች የዘረጉትን የልማት አቅጣጫ የሚደግፍ ግልጽና ውጤታማ የኢነርጂ ኃይል እንዲኖር ማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል ውጤታማ የኢነርጂ አጠቃቀም እንዲኖር ማስቻል ብሎም ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ መዋዠቅ ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት በመፍጠር ኢኮኖሚውን መታደግ የሚሉ ዓላማዎችንም ጭምር በማንገብፉ ሥራውን ጀምሯል፡፡

እነዚህን ዓላማዎች ለማካት የኢነርጂ ፖሊሲው ቀጣይነትና አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲሁም ዘርፉን የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት ፈጣን ኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር እንዲኖር መመሪያዎችን ለመዘርጋት ከፍ ሲልም ሀገር በቀል የሆኑና የአየር ንብረት ብክለትን የሚያስወግዱ የኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ፖሊሲው ለውሃ ኃይል ልማትን እንዲሁም የኢነርጂ አጠቃቀም ስብጥር በማበረታታት ለታዳሽ የኢነርጂ አጠቃቀም፣ ለፀሐይ ኃይል፣ ለንፋስ እና ጂኦተርማል ልማትና ዋጋ ተወዳዳሪነት ትኩረት የሰጠ ነው፡፡

ተስማሚ የፖሊሲ ርምጃዎችን ለመውሰድ ደረጃ በደረጃ የህዝቡን ተለምዷዊ የኢነርጂ አጠቃቀም ወደ ዘመናዊውና ለአየር ንብረት ጥበቃ አጋዥ የሆነ አጠቃቀም የመቀየር ዓላማን አንግቧል፡፡

እንደሚታወቀው የኢፈረዴሪ መንግስት በሀገራችን ለሚገኝ ሁሉም ነዋሪ ዓለም አቀፍ ጥራትና ብቃት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠትና ተወዳዳሪ የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ኢንዱስትሪ የመሆን ትልሙን ለማሳካት በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ውጤትም እያገኘ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅትም አገሪቱ ያላት የኤሌክትሪክ ኃይል የተወሰነ ቢሆንም፤ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደውን የኃይል ፍላጎትን በማደግ ላይ የሚገኘውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት በአግባቡ ማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ የኃይል አቅርቦቱን በቀጣይነት በማሳደግ ረገድ ሥራው ቀጥሏል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁለንተናዊ አገልግሎት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ ባለፉት 26 ዓመታት በተለይም ደግሞ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ በርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ከውሃ፣ ከንፋስና ጂኦተርማል በመገንባት ላይ ሲሆን የኃይል ማስተላለፊያ ማከፋፈያ ጣቢያዎችንም ጎን ለጎን ለመገንባት ከሚመረተው ኃይል ጋር በማጣጣም በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

በዋናነትም ከሚጠቀሱት ግንባታዎች መካከል የጢስ አባይ 2 ውሃ ኃይል ማመንጫ— 73 ሜጋዋት ፣ የጊቤ1 የውሃ ኃይል ማመንጫ— 184 ሜጋ ዋት፣ የተከዜ ውሃ ኃይል ማመንጫ— 300 ሜጋ ዋት፣ የግልገል ጊቤ 2 ውሃ ኃይል ማመንጫ— 420 ሜጋ ዋት እንዲሁም ከበለስ ውሃ ኃይል ማመንጫ— 460 ሜጋዋት እና ከፊንጫ አመርቲነሽ ውሃ ኃይል ማመንጫ— 97 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ማግኘት ተችሏል፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በተለይም ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበሩ የኃይል አቅርቦት አማራጮች ፈቅ ብሎ ሌሎች አማራጮችም ለሀገሪቱ የኃይል እጥረት መቀረፉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚያችሉ የታየበትም ነው፡፡

የአገራችንንና የቀጣናውን የኤለክትሪክ ሃይል ይቀርፋል ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ከሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት መሃንዲሶቹም ግንበኞቹም የፋይናንስ ምንጮችም እራሳችን ሆነን እየገነባነው ያለ የህዳሴያችን ታላቅ ፕሮጀክት ነው እንዳሉት ህዝቡ የራሱ ብሎም ብቸኛው ጠላታችን ድህነት ነው የሚለውን አጀንዳ በማንገብ ህብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደለት ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት እየተጋ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን አንድነትን ከአሳየበት ትይንት ባሻገር፤ የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ የማጥላላት ዘመቻ በማድረግ ላይ የሚገኙት የውጭ ኃይሎችና የሀገር ውስጥ ተላላኪዎችንም ምን ያህል ከህዝብ ያፈነገጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ያጋለጠ ታላቅ ፕሮጀክት ሆኗል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሆነ ሌሎች ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲገነቡ ልማቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረውንም ትስስር ያመላከተ ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ወደ ጎረቤት ሀገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል በመላክ ሀገራቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት እነርሱንም ጭምር የሚጠቅም መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡ ሀገሪቱም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሀገራችን ለቀጣይ ዕድገት ተጨማሪ አቀም እንድታገኝ የሚያደርጉ የህዳሴያችንን ሁነኛ መሠረቶችንንም ይጥላሉ፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሀገራችን እና በቀጣናው ሀገራት መካከል መተማመን ላይ የተመሰረተ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት የሚሰጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠርም ያስችላል፡፡ ከጂቡቲና ከኬንያ ጋር የተጀመረው የሁለትዮሽ የኃይል አቅርቦት ስምምነት ከቀጣናው ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ጤናማ ግንኙነት አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋነኛ ዓላማ በማደግ ላይ ያለውንና ወደፊትም የመሪነት ሚናውን ከግብርናው ይረከባል ተብሎ ለሚጠበቀው የኢንዱስትሪ ዘርፍ በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፈውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከሊሎች ሃገራት ጋር ትስስርን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ የዚህም ድምር ውጤት ህዝቦቿ ካሉበት የድህነት አዘቅት ተላቀው አመርቂ ልማት ለማስመዝገብ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት ያላት ሀገር ለማቆየት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ በጨረፍታ ለመመልከት የሞከርኳቸው ሜጋ ፕሮጀክቶቻቸን ከሀገራችን አልፈው የቀጠናውን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት መሸፈን የሚችሉ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ እንደ አገር በሚያስገኙልን ጥቅም እየጨመሩ ለመጡት የልማት ስራዎቻችን በቂ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy