Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምርት እንዳይባክን መስራት ይገባል!

0 257

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምርት እንዳይባክን መስራት ይገባል!

                                                        ደስታ ኃይሉ

በመኸር ምርት 345 ሚሊዩን ኩንታል ሰብል ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ከፍተኛ የምርት ሰብል እንዳይባክን የምርቱ ባለቤት የሆነው አርሶ አደርና በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት የተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። የምርት ብከነት ተወዳዳሪነትን የሚያሳንስ እንዲሁም አምራቹ ከምርቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ የሚያደርግ በመሆኑ ለየት ያለ ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድ ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው መንግስት የማስፋት ስትራቴጂን በመጠቀም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ይህም በአነስተኛ ማሳ ላይ ብዙ ምርት ማግኘት ያስቻለ፣ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የላቀ ሚና ተጫውቷል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ እንደመሆኑ መጠን፤ የአርሶ አደሩ የአመራረት ዘይቤ መለወጡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።

በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት ተችሏል። ይህም አጠቃላይ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍ አድርጓል። በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የተገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የምርትና ምርታማነት ማደግ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም በመጀመሪያው የዕቅድ ዓመት ላይ የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

የግብርና ልማት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ይችል ዘንድ በበሁለተኛው አምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት ተሰጥቶታል። እንደሚታወቀው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በሀገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ የአርሶ አደሩ ህይወት በአያሌው ተለውጧል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙት አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ይህ ትርፍ አምራችነታቸውም ከተጠቃሚነታቸውባሻገር ሌሎች አካባቢዎች በተፈጥሮአዊው የድርቅ አደጋ በሚጠቁበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት እየሞሉ ነው። ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ይታሰባል።

በቅርቡ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በ2009 የምርት ዘመን ከ345 ሚሊዩን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በአብዛኛዎቹ የመኸር አብቃይ አከባቢዎች የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ በአሁኑ ወቅት ጥሩ የምርት ሁኔታ በእርሻ ማሳ ላይ መኖሩን ሚኒስቴሩ መግለፁ ይታወሳል። አርሶ አደሩም በእሸትና በቡቃያ ደርጃ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ የመጠበቅ፣ በየጊዜው ማሳውን የመፈተሽ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ ክትትል ማድረጉ ተመልክቷል።

ተባዮችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና በመከላከል በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ማሳ ላይ የሚገኘውን ምርት ወደ ጎተራው እስኪገባ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ እያደረጉ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የሰብል ምርቱን ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። እንዲሁም የአርሶ እደሩን ጉልበት የሚያግዙ የሚደግፉና ጉልበቱን ውጤታማ የሚያደርጉ መጠነኛና አነስተኛ የሜካናይዜሽን ስራዎች እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው።

ታዲያ ከዚህ የሚኒስቴሩ ማብራሪያ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ መንግስታዊ ጥረት ላይ የተወሰኑ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ነው። ርግጥ የግብርና ምርት የጥራት ችግርና ብክነት አሁንም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች ናቸው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በድህረ- ምርት አያያዝና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ሶስተኛው የግብርና ምርታችን እንደሚባክን ተረጋግጧል። መባከን ብቻም ሳይሆን በአጨዳ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃት፣ በማበራየት፣ በመጓጓዝና በማከማቸት የማምረት ሂደት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ምርት በወቅቱ ባለመታጨዱ ምክንያትም ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናብ ተበላሽቶ ለብክነትና ለጥራት መጓደል የሚጋለጥበት ሁኔታም መኖሩ ይታወቃል።

ይህ ሁኔታም አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ከለፋበት ምርት እንዳይጠቀም የሚያደረግ ነው። ምርት ለብክነት ከተጋለጠና ጥራቱም ካሽቆለቆለ ተገቢውን ዋጋ ሊያስገኝ አይችልም። አንድ የምርት ዓይነት ሲታጨድ፣ ሲወቃና ሲበራይ እንዲሁም ሲጓጓዝና ሲከማች የሚባክን ከሆነ ከብዛት ሊገኝ የሚችል ጥቅም አይኖርም።

በእነዚህ የምርት ሂደቶች ወቅትም አመራረቱ ተገቢ ላልሆነ የጥራት ችግር ከተጋለጠ ከምርቱ አግባብ የሆነ ገቢን ማግኘት አይቻልም። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሰበስብብበት ነው። እናም ምርቱ ለብክነትና ለጥራት ማነስ እንዳይጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ማሳ ላይ የሚገኝ ምርት የአርሶ አደሩ የላብ ውጤት ነው።

አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ተጠቅሞ እዚህ ደረጃ ያደረሰው ሰብል በስተመጨረሻው ለብክነትና ለጥራት መጓደል ችግር መጋለጥ የለበትም። የላቡን ፍሬ በሚያገኝበት በአሁኑ ወቅት በተግዳሮቶች ሳቢያ ከምርቱ ተጠቃሚ ሳይሆን መቅረት የለበትም።

የምርት ብክነትና የጥራት መጓደል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በሚገባ የማያረጋግጡ ከመሆናቸው ባሻገር፤ መንግሰት የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በሚያደርጋቸው ተግባራት ላይ ጥላ የሚያጠሉም ጭምር ናቸው።

ይህ ሁኔታ የአርሶ አደሩን ህይወት ከድህነት አዙሪት በፍጥነት እንዳይወጣ የሚያደርግ መሰናክል ስለሆነ በቀላሉ የሚታይ ተግዳሮት አይደለም። እናም አርሶ አደሩ በማምረት ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።

በተለይ በአጨዳ ወቅት ምርቱ ከአረም ጋር እንዳይደባለቅ፣ ታጭዶ ንፁህ በሆነ ቦታ እንዲቀመጥና ምርቱ ለአላስፈላጊ የዝናብ አደጋ እንዳይጋለጥ በማድረግ ጥራቱን መጠበቅ ከአርሶ አደሩ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ምርቱ እንዳይባክን በአሰባሰብ ሂደቱ ላይ በቂ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል። ምርቱ ሲበራይ በንፋስ ተጠልፎ እንዳይሄድ፣ በሚበራይበት ቦታ ካለ ባዕድ ነገር ጋር እንዳይደባለቅ፣ ንፅህናው አስተማማኝ እንዲሆንና በአግባቡ እንዲመረት ማድረግም ይጠበቅበታል።

የምርት ጥራት በተጠበቀ ቁጥር ሁለት ጉዳዩችን ማሳካት ይቻላል። አንደኛው የሚመረተው ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ጥሩ ዋጋ እንዲያወጣ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አርሶ አደሩ በለፋው መጠን ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ያደርገዋል።

ይህም አገራችን እንደ ሀገር አሳካዋለሁ ብላ የያዘችውን የህዳሴ ራዕይ እውን ለማድረግ የሀገሪቱ የዕድገት ምንጭ የሆነው የግብርና ምርት ለዓላማዋ መሳካት ከፍተኛውን ድርሻ እንዲኖረው ያደርጋል። ስለሆነም ምርት እንዳይባክን አርሶ አደሩም የሁን ከእርሱ ጋር በቅርበት የሚሰሩ የግብርና ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy