በህገ-ወጥ መንገድ ዛምቢያ ገብተው የተያዙ 70 ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሌላ ዜና ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ሽያጭ ለማከናወን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ዛምቢያ የገቡት ዜጎች የአገሪቱ መንግስት በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የገለጹት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ካሁን ቀደም ዛምቢያ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙና እስከ 15 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ 147 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወቃል።
አሁንም ዛምቢያ ውስጥ የተያዙትን ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ለመመለስ በአገሪቱ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዛምቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ባለሙያዎች አሰማርቶ ከአገሪቱ መንግስት የስደተኞች ጉዳይ ጋር እየተወያየ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሌላ ዜና ሚኒስቴሩ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ እንዲገዙ ለማድረግ በሚሲዮኖችና ኤምባሲዎች በኩል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አቶ መለስ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቦንድ ለመሸጥ መታቀዱንም ገልጸዋል።
በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ጉዳዩን የሚከታተሉ ቋሚ ባለሙያዎች እንዳሏቸው ተገልጿል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከገንዘብ በተጨማሪ በእውቀታቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየሰራን ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ።