በሰንደቅ ዓላማው ስር የተሰባሰበ ህዝብ!
ታዬ ከበደ
ላለፉት ዓመታት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ርብርብ አድርገዋል። የአገራችን ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው በተለይም ላለፉት 10 ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድ ውጤቶች ማምጣት ችለዋል።
እንደሚታወቀው ሁሉ ያለፉት ጨቋኝና አምባገነን ስርዓቶች የሀገራችንን ህዝብ በእጅጉ ጎድተውታል፡፡ ስርዓቶቹ ለስልጣናቸው ሲሉ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማፈን የራሳቸውን ወንበር ሲያደላድሉ ኖረዋል። የህዝቡን ተስፋ አሟጠው በመውሰድ ተስፋ ቢስ አድርገውታል።
ስልጣንን በዘር ግንድና በኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተቆናጠው ህዝቡን አላላውስ ብለውት በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲዳክር ከማድረጋቸውም በላይ፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አንገቱን ደፍቶ እንዲሄድ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ምስጋና ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ይሁንና ዛሬ ይህ ታሪክ ዳግም ላይመለስ ጓዙን ጠቅልሎ ተሰናብቷል። ህዝቦች በራሳቸው ፈቃድ ተስማምተው ባፀደቁት ህገ-መንግስት ሰላማቸውን፣ ልማታቸውንና ዴሞክራሲያቸውን ያለ ገደብ እያጣጣሙት ነው። ልማትንም እያካሄዱ አገራቸውንና ራሳቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው።
ሀገራችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል። በመሆኑም ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ምን ያህል ሁሉም ሀገር የሚፈልጋት መሆኗን ያረጋግጣል።
ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራዊው ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ሀገሪቱ ለዘመናት ከምትታወቅበት የድህነትና የኋላቀርነት ታሪክ በሂደት እየቀየረ ከመሆኑም በላይ፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባሰገኘው ልማታዊ እመርታ ለአለም ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡
እንደሚታወቀው የአንድ ሀገር ህዝብ በምግብ ሰብል ራሱን ችሏል የሚባለው በሀገሪቱ ከተመረተው አጠቃላይ ምርት የሚኖረው የነፍስ ወፍ ድርሻ ተሰልቶ ነው። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ህዝብ የነፍስ ወከፍ የምግብ ሰብል ድርሻ ሲሰላ በወር ሶስት ኩንታል መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም በምግብ ሰብል በአብዛኛው ራሳችንን መቻላችንን የሚያመላት ነው። በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የድርቅና የረሃብ አደጋ ማንም ሰው እንዳይሞት ዋስትና ሆኗል ማለት ይቻላል። ይህ የሆነውም ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው በፅማት ስለሰሩ ነው።
ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው በመሰባሰብ በዴሞክራሲ ረገድም ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስቱ በአንቀፅ ስምንት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ-መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ደንግጓል።
ይህ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያሳየው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። የስልጣኑ ባለቤት ህዝብ እንጂ ማንም አይደለም። የትኛውም አካል ያለ ህዝብ በጎ ፈቃድና ይሁንታ ስልጣን ሊይዝ አይችልም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከህዝቡ እውቅና ውጭ በውጭ ሃይሎች የሚዘወር ዴሞክራሲ እዚህ ሀገር ውስጥ እውን ሊሆን አይችልም። የሀገራችን የፖለቲካ ጉዳይ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ብቻ እንጂ ሌላ የማንም አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። የውጭ ሃይሎች ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የዚህን ሀገር ዴሞክራሲ ሊያቀጭጨው ካልሆነ በስተቀር ሊያጎለብተው አይችልም።
በሌላ በኩልም ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል። ይህን የተዘጋ ዶሴ ማንም ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሊያስገባው አይችልም—ህዝቡ ይህ እንዲሆን አይፈቅድምና።
ዴሞክራሲ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ቢኖሩትም፤ አፈፃፀሙ ግን እነደ ሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ሊሆን ይገባዋል ብዬ አምናለሁ። የባዕድ ሀገርን ዴሞክራሲ “እንደ ወረደ” አምጥተን እዚህ ሀገር ውስጥ እውን እናድርገው ብንል፤ አገራችን ካሳለፈችው አባጣና ጎርባጣ እንዲሁም ጨቋኝና አንገት አስደፊ መንገዶች ብሎም የህዝቡ ባህልና ስለ ዴሞክራሲ ያለው ምልከታ ተደማምረው ተግባሩን እውን ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም።
ያም ሆኖ ዴሞክራሲን አዚህ ሀገር ውስጥ ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኗል። መንግስትም የዴሞክራሲውን ምህዳር ለማስፋት ይህን የሞት ሽረት ጉዳይ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጨባጭ ሁኔታችን ጋር በማጣጣም ገቢራዊ ለማድረግ እየሰራ ነው። ይህን ሲያከናውንም መሰረታዊ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውንና ሀገራችንም የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎችን በማስከበር ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 31 “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት አለው። ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ናቸው” በሚል በተደነገገው መሰረት፣ ማንኛውም ዜጋ ባሻው ማህበር ወይም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታቅፎ መንቀሳቀስ እንዲችል በመደረጉ ሀገራዊ ዴሞክራሲው አቅም በፈቀደ መጠን እንዲሰፋ ተደርጓል። በዚህም ለዴሞክራሲው መጎልበት ወሳኝ ሚና ያላቸው በርካታ ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን እያከናወኑ ነው። ይህ የሆነውም ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው የጋራ ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ስለጣሩ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠል መብታቸው መጠበቁን፣ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መበት አለው፡፡ እንዲሁም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት የተረጋገጠለት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል።
ከዚህም ጋር ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ መስኮች ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸውንና ከዚህ በፊት በነበረው ልዩነት ምክንያት የተፈጠረባቸውን ጫና ለመቅረፍ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተደንግጓል።
በጥቅሉ የአገራችን ህዝቦች የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ መብቶች ላለፉት 26 ዓመታት ጥቅም ላይ ውለው መላውን ህዝቦች ተጠቃሚ አድርገዋል። ይህ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት እውን የሆነው ዜጎች በህገ መንግስቱ ጥላ ስር ተሰባስበው ለአንድ የጋራ ዓላማ ስለቆሙ ነው።