Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተጀምሮ የሚቋረጥ ፕሮጀክት የለንም!

0 246

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተጀምሮ የሚቋረጥ ፕሮጀክት የለንም!

ዳዊት ምትኩ

ሰሞኑን በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አገራችን እየገነባች ያለችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ‘ተቋረጠ’ የሚል አስገራሚ አሉባልታ ሲናፈስ ነበር። ሆኖም ግድቡ በአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎትና በ“ይቻላል” መንፈስ ተጀምሮ በዚሁ መንፈስ በከፍተኛ የህዝብ ርብርብ እየተካሄደ ያለ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ግድቡን የጀመሩት እንደሚጨርሱት ስለሚያውቁ ነው። እዚህ አገር ውስጥ በህዝቡ ገንቢነት ተጀምሮ የተቋረጠ ፕሮጀክት የለም። የህዳሴውም ግድብ ለሰከንድ እንኳን ሳይቋረጥ ስራው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተካሄደ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመጽዎችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የይቻላል መርህን በተግባር ማዋል ያስቻለ ብሎም ከራስ አልፎ በሚደረገው ሽያጭ የህዝቡን ውለታ በዕድገት የሚመልስ በመሆኑ ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን የሚቋረጥበት ምክንያት የለም፡፡

እርግጥ ቀደም ባሉት ጊዜያት ግብፆች ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ እንዳትጠቀም የፋይናንስ ግኝቶችን ስታግድ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ አሁን ግን ይህ ሁኔታ ተለውጧል፡፡ ምክንያቱም አዲሲቷ ኢትዮጵያ የትናንቷ ባለመሆኗ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ ላለፉት 10 ተከታታይ ዓመታት ልማታቸውን ማሳደግ ችለዋል።

በዚህም ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። ይህ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው አቅምም ዜጎቿ የተፈጥሮ ሃብታቸውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የዚህ አቅም ሁነኛ መገለጫ ነው።

እርግጥ የሀገራችን ህዝቦች በየትኛውም የልማት ስራ ላይ ፋና ወጊ ናቸው። በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የባንዴራቸው ፕሮጀክት መሆኑን በመገንዘባቸው ለግድቡ ከፍፃሜ መድረስ እየተረባረቡ ነው። እጅግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ ለግድቡ ግንባታ ከዕለት ቀለባቸው ጭምር እየቀነሱ በገዛ ፈቃዳቸው እያከናወኑ ያሉት የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የቀሳቁስና የሞራል ድጋፍ እጅግ የሚያኮራ ነው።

ግድቡን ለመገንባት ለዘመናት ሳይደፈር የቆየውን የዓባይን ወንዝ የመድፈር ተግባር በዚህ ትውልድ እውን ሆኗል። በዚህም ይህ ትውልድ የትናንቱን ትውልድ የልማት ጥያቄ፣ የዛሬውን ትውልድ ተጠቃሚነትና የነገውን ትውልድ አደራ ተቀብሎ እየሰራ ነው። የታላቁ የአትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዚህ ረገድ ሁነኛ ማሳያ ነው። መቻላችንን የምናሳይበት የቁርጠኛ ህብረታችን አንድ መገለጫ ነው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በዕውቀቱ ለመደገፍ የገባውን ቃል አሁንም ቀጥሏል። ምንም እንኳን ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሃይሎች የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያወሩም፤ በኢትዮጵያ ህዝቦች ርብርብ ግንባታው ዛሬም ድረስ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልተቋረጠም። “የነብርን ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም” እንዲሉ አበው፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህን ፕሮጀክት አውን ለማድረግ ልማቱን በነብር ጭራ መስለው ይዘውታል። አይለቁትም።

በተምሳሌታዊ ዘይቤው የነብርን ጭራ ከለቀቁ በነብሩ መበላት ስለሚሆን፤ ተምሳሌታዊውን የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በመተው ወደ ድህነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ አይሹም። ማደግና መበልጸግ እንደሚችሉ አንድ ማሳያ የሆነውን የግድቡን ግንባታ በመተው የድህነት መገለጫ ሊሆኑ አይከጅሉም። ይህ ታሪክ በሂደት እየተቀረፈ፣ ህዝቡም ከዕድገት የሚያገኘውን ጥቅም እያጣጣመ ነው።

እናም የህዳሴው ግድብ ለአንዲት ሰኮንድም ሊቆም የማይችለው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት ማናቸውንም ልማታዊ ተግባሮች ማከናወን እንደምንችል ማሳያ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው። በሌላ በኩልም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተፋጠነ ባለው የልማት ተግባር ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎች “እየበቀሉ” ነው። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ታዲያ ይህን የዕድገት ፍላጎት በአግባቡ ለማስኬድ የኤሌክትሪክ ሃይልን ከከባቢ ብክለት በነፃ መንገድ መጠቀም የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ ታዳሽ የተፈጥሮ ሃይላችንን መጠቀም ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን አሁንም ከነበርንበት የከፍታ ቦታ ተንሸራትተን የኋሊት በድህነት አረንቋ ውስጥ ልንዘፈቅ እንችላለን። ይህን ደግሞ የሚፈቅድ ትውልድ የለም። እናም የህዳሴው ግድም ለአፍታም ቢሆን የማይቆምበት ሁለተኛው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

እኛ ስናድግም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራትም የሁኑ ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኛ ከቀጣናው ሀገራት ተነጥለን ልንለማ አንችልም። የእኛ እድገት የቀጣናው ሀገራት ጭምር ነው። የግድቡ ግንባታ የቀጣናውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ችግርም የሚቀርፍ ነው። እናም ሶስተኛው ግድቡ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን ሊቆም እንዳይችል የሚያደርገው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።

መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነዚህን እውነታዎች በሚገባ ያውቃሉ። ምንም ዓይነት ብዥታ የለባቸውም። ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ ዋንጫው በየክልሉ ሲዞር ከተጠበቀው በላይ ገንዘብ በማውጣት ቦንድ የሚገዙትም ለዚሁ ነው።

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈፀሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ይህ ቁርጠኛ የህብረት ስሜት ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ድረስ የሚታይ ነው። ማንም በገሃድ የሚያየውም ጭምር። እናም ይህ የህዝቦች አንድነት የራስን የተፈጥሮ ሃብት በራስ አቅም የማልማትና በእርሱም ራስንና ከባቢውን የመጥቀም ተምሳሌት በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ ለአንድ ሰከንድም ቢሆን የሚቋረጥ አይደለም።

የየትኛውም ሀገር የልማት ምንጭ ህዝብ መሆኑ፣ ከዚህ አኳያ በተለይ ታታሪው የሀገራችን ህዝብ ለማደግ ያለውን ቀናዒ አስተሳሰብና ተግባር በሚፈለገው ፍጥነትና ደረጃ እየተካሄደ ነው። በተለያዩ ወቅቶች እንደተገለፀው የህዝቡ ንብረት የሆነው ይህ ግድብ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

ህዝቡ ለግድቡ አውን መሆን ማንኛውንም ነገር እያደረገ ነው። ወደፊትም ያደርጋል። በጉልብቱም፣ በዕውቀቱም፣ በገንዘቡም በፀሎቱም ጭምር ለግድቡ እውን መሆን እየታገለ ነው። በእኔ እምነት የሰው ስጋና ደም ለግንባታው የሚያገለግል ቢሆን ኖሮ፤ ይህን በመከወን ግድቡን ለማሳለጥ የተዘጋጁ እልፍ ናቸው ብል እንደ ማጋነን የሚቆጠርብኝ አይመስለኝም። የህዳሴው ግድብ ግንባታ አንድነታችንን ይበልጥ ያጠበቀ ነው። መቻልን የቻልንበት፣ አንድ ከሆንንና ከተባበርን የማንወጣው ፈተና አለመኖሩን ያየንበትም ይሁን ያሳየንበት ጭምር ነው። እናም ‘ተቋረጠ’ የሚለው ኡባልታ መሰረተ ቢስ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን ህዝቦች የማደግ ፍላጎትን የማይሹ ሃይሎች ተራ ምኞት መሆኑን መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy