Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተጠናክሮ የቀጠለው ኢኮኖሚያችን

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተጠናክሮ የቀጠለው ኢኮኖሚያችን

                                                         ታዬ ከበደ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ አማካይ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት 9 በመቶ እንደሚያድግ በድረ ገፁ ላይ አስፍሯል። ይህ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት የኢኮኖሚያችንን መጠናከር እንደሚያሳይም ድረ ገፁ አብራርቷል። ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም የዓለም ኢኮኖሚ የተቀዛቀዘ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግን ጫናውን ተቋቁሞ ግስጋሴውን መቀጠሉ የኢኮኖሚውን ጥንካሬ የሚያሳይ መሆኑንም አስረድቷል። ይህ ትክከለኛ የአገራችንን የዕድገት ጎዳና የሚያሳይ ነው።

እርግጥም ኢትዮጵያ አኮኖሚ ባለፉት 26 ዓመታት ከፍተኛ እመርታን አሳይቷል። ዛሬ ላለለንበት የምጣኔ ሃብት ቁመና ከትናንት ጀምሮ ሲከናወኑ የመጡት ተግባራት መሰረቶች ናቸው። እናም ወደ ኋላ መለስ ብሎ የተከናወኑትን ልማታዊ ተግባራት በመጠኑ መቃኘት ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የደርግ ስርዓት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠንካራ ክንድ የዛሬ 26 ዓመት ገደማ በተገረሰሰ ማግስት፤ የመንግስት ዋነኛ ስራ በመላ ሀገሪቱ ተተብትቦ የቆየውን የደርግ የዕዝ ኢኮኖሚ አሰራር መዋቅር የመለወጥና የማሸነፍ ኃላፊነት ነበር።

ሆኖም የተመሰቃቀለውን የደርግ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ አሰራርን በ‘ነበር’ ለማስቀረት ቀላል ትግል አልጠየቀም። በዚህ ሂደት ውስጥም እስከ አራት ዓመታት ድረስ ያገለገለው የሽግግር መንግስት ውስብስብ አሰራሮቹን እያስወገደ በመምጣቱ፤ አገሪቱ ከነበረችበት ስር የሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እየተሰራ ለነበረው ዕመርታዊ ለውጥ በር ሊከፍት ችሏል። ይህ የለውጥ ምዕራፍም ተጠናቀቀ። ይህ ምዕራፍ ተጠናቀቀ ሲባል ታዲያ በቃላት ሊገለፁ የሚይችሉ በጣም ፈታኝና አዳጋች ተግዳሮቶች መታለፋቸውን ልብ ሊባል ይገባል።

ላለፉት 26 ዓመታት የሀገራችንንን ኢኮኖሚ ስር ከሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲሁም የህዝቡን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ስራ ላይ ውለዋል። ውጤታቸው ስኬታማ እንደነበርም ከእነዚህ ዓመታት በፊት የነበረችውንና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በማየት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል።

የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር የጎላ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ልዩነት አላት። ደርግ ከእነ ዕዝ ኢኮኖሚዋ ባለ ባዶ ካዝና አድርጓት ጥሏት የሄደው የትናንትዋ ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ በበሊዮን የሚቆጠር በጀት መዳቢ ሆናለች። የቢሊዮን ፕሮጀክቶችን ገንቢም ሆናለች።

ኢትየጵያ የትናንት ቁስሏን ከመመልከት ይልቅ ህዘቦቿን በአንድነት እያሳተፈች በልማት ጎዳና በመገስገስ ላይ ትገኛለች። በዚህም ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የምትሻለዋን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች።

ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል በመግቢያዬ አካባቢ የጠቀስኩትን ዓይነት ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦችን እያስመዘገበች በሂደት የምስራቅ አፍሪካን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት ለመምራት የምትችልበትን አቅም መገንባት የምትችል መሆኑን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጭምር እማኝነታቸውን እየሰጡ ነው።

እርግጥ ዓለም አቀፉ ተቋማት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያወጧቸው የትንበያ ዘገባዎች ለእኛ ከማሰብ አሊያም ኢትዮጵያን ለመጥቀም ከመፈለግ የመነጩ አይደሉም። በሀገራችን ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የምጣኔ ሃብት አቅምን ከመተንበይ የተገኙ ግኝቶችን መሰረት አድርገው የሚያከናውኑት ተግባር መሆኑን ማንም የሚስተው ሃቅ አይመስለኝም።

እናም በመጪው ጊዜያት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከአገራዊ እመርታ ባሻገር የአፍሪካ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ትናንት አገራችን በትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራች ያከናወነቻቸው ስራዎች ዛሬ ለምንገኝበት እምርታ ምቹ ምህዳርን መፍጠር የቻሉ በመሆናቸው ነገም ተመሳሳዩን አንደሚገድሙ እርግጥ ነወ።  

የደርግ ስርዓት ከወደቀ በኋላ ያንን የደቀቀ ኢኮኖሚ ለማቃናት ከባድ መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ አስቀድሞ የተተነበየ ጉዳይ ነበር። እናም በወቅቱ ተራራ የሚያክለውን የሀገሪቱን ድህነት ለመዋጋት ሶስት መርሆዎች መቀየሳቸውን እናስታውሳለን።

በመሆኑም በመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት መንግስትና ህዝብ የተጓዙባቸው መንገዶች በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተንሰራፋውን ድህነት ለማሸነፍ ፈጣን ባለመሆናቸው፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ የዕድገትና ድህነትን የማስወገድ መርህ መዘርጋት አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሔ ሆኖ ተወስዷል።

እስከ የመጀመሪያው ተሃድሶ ዋዜማ ድረስ የፈራረሱና ያረጁ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋማትን ለማደስ፣ ኢኮኖሚውን ከኋሊት አዙሪት በማላቀቅ ወደፊት ለመመልከትና ትክክለኛ አቅጣጫን እንዲይዝ ለማድረግ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ቀላል አልነበሩም።

በእነዚህ ዓመታት በዋነኛነት የመንግስት አስተዳደርንና ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልተማከሉ የማድረግ፣ ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ገበያ መር ስርዓት የማምጣት፣ በፖሊሲ መዛባት በጦርነትና በተፈጥሮዊ ክስተቶች ሳቢያ የተሽመደመደው ኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲቀየር የማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል። ውጤትም ተገኝቶባቸዋል።

ከመጀመሪያው ተሃድሶ መባቻ ጀምሮ በተወሰዱት ርምጃዎች የተሟላ ዝግጅት በመደረጉ እንዲሁም ህዝቡም መንግስት የቀረፃቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ በማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ወደ ተሻለ እመርታ ሊሸጋገር ችሏል።

በተለይ ላለፉት 10 ዓመታት መንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎችን በተመረጠ አኳኋን በመስራቱ ብሎም ያሉትን ውስን ሃብቶች መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል እንዲሁም የልማት ሃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበትና የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ፈጣን፣ ቀጣይነትና ፍትሃዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲመጣ ተደርጓል።

ባለፉት 10 ዓመታት የተመዘገቡት የፈጣንና ተከታታይ ምጣኔ ሃብታዊ እመርታዎች ውስጥ አገራችን ዕውን እንዲሆኑ ያደረገቻቸው የልማት ዕቅዶች የነበረንን የዕድገት ፍጥነት ይበልጥ አፋጥነውታል። ለዚህም በተለይም የመጀመሪያው የልማት ዕቅድና በአሁን ወቅት እየተተገበረ ያለው ሁለተኛው የዕድገት እቅድ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሁለተኛው የልማት ዕቅድ መጨረሻ ላይ መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ለውጥ ለማምጣት ተግታ እየሰራች በመሆኑ የገንዘብ ተቋሙ እንዳለው ነገም ምጣኔ ሃብቷን ይበልጥ የማታሳድግበት ምክንያት የለም። ምክንያቱም አገራችን የምትከተለው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲህ ዓይነቱን እመርታ ማስመዝገብ የምትችል በመሆኑ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy