Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትግሉ የሞት የሽረት ነው!

1 403

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትግሉ የሞት የሽረት ነው!

አሜን ተፈሪ

የኢትዮጵያ መንግስት እና ገዢው ፓርቲ የስርዓቱ ዋነኛ ተግዳሮቶች አድርገው የሚለከቷቸው ነገሮች አሉ፡፡ በ1993 ዓ.ም ከተካሄደው ‹‹የተሐድሶ ጉባዔ›› ጀምሮ (አራተኛው ድርጅታዊ ጉባዔ) የመልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ሳይነሳ የታለፈበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ በዚህ የተሐድሶ የትግል ጉዞ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እና ተግባር ለሥርዓቱ አደጋ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ከታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በተካሄዱ ሁለት ድርጅታዊ ጉባዔዎች (ዘጠነኛው እና አስረኛው) ልዩ ትኩረት የተሰጠው በአመለካከት እና በተግባር ለሚገለጽው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ችግር ነው፡፡ መጋቢት 2005 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ዘጠነኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ዋዜማ ከዋልታ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በብዙ የአፍሪካ ሐገራት ሲሆን እንደምናየው፤ ከአቶ መለስ መስዋዕት መሆን በኋላ በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ አደገኛ ቀውስ ሳይፈጠር የፌዴራል ስርዓቱን ማስቀጠል የተቻለው፤ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን በተወሰነ ደረጃ መድፈቅ በመቻሉ ነው›› ብለው ነበር፡፡ ስለዚህ ኪራይ ሰብሳቢነትን መድፈቅ አለመቻል የስርዓት ቀውስ ሊያስከትል የሚችል አደገኛ ችግር ነው፡፡

አቶ ኃይለማርያም በሌላ በኩል ያነሱት አንድ ወሳኝ ነጥብ ነበር፡፡ ‹‹መሠረታዊ ጥያቄው የተለመሰ ቢሆንም፤ በየጊዜው ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች ስለሚያጋጥሙን፤ ለነዚህ ተግዳሮቶች የተተነተነ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል›› ብለው ነበር፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም እንዳሉት፤ ስርዓቱ በጽኑ መሠረት ላይ የቆመ ሆኖ ሳለ፤ አዲሱ የድርጅት አመራር በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ዓለማዊ እና ሐገራዊ ፈተናዎች በደንብ ተንትኖ በመረዳት ከሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ታክቲካዊ ውሳኔዎች እያሳለፈ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም እንዳሉት፤ ነገሮችን በደንብ ተንትኖ በመረዳት ከሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ታክቲካዊ ውሳኔዎችን እያሳለፉ መሄድ ከባድ የቤት ሥራ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የሚሸነፈው ልማታዊ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ በመፍጠር እንደሆነ እና ትግሉም ዓመታትን የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይለማርያም፤ በገጠር የተወሰነ ርቀት ለመሄድ መቻሉን እና በከተሞችም መሻሻል መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ልማታዊ ፖለቲካ-አኮኖሚ የበላይነት ያገኘበት ሁኔታ እንዳልተፈጠረ ግን ተናግረው ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም እንደጠቆሙት፤ ተተኪው አመራር የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ-ኢኮኖሚ የበላይነት ባገኘበት ሁኔታ ትግል የሚያደርግ አመራር በመሆኑ፤ በፈታኝ መድረክ እንደሚገኝ አስረድተው ነበር፡፡ ስለዚህ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ -ኢኮኖሚ የበላይነት ባገኘበት ሁኔታ ኃላፊነቱን የሚወጣው አዲሱ አመራር ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ አመራር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከአለፈው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ አመራሩን ለማስተካከል እርምጃዎች የተወሰዱ እና በጥልቅ ተሃድሶ ሕዝባዊ መድረኮች የተለዩ አንዳንድ ችግሮች መፈታት የጀመሩ ቢሆንም፤ አሁንም ግን የህዝብን እርካታ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄያችን በላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ አሁን በምንገኝበት ለሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች፤ አመራሩ የተተነተነ ምላሽ የመስጠት ብቃቱም እየተፈተነ ይገኛል፡፡

የኢህአዴግ ሊቀመንበር አዲሱ አመራር ከባድ ኃላፊነት እንደተሸከመ ገልጸው፤ ሐገራዊ እና ዓለማዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ አመራር የሚሰጥ ብቁ አመራር መፍጠር እንደሚገባ አስረድተው ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም፤

‹‹…. ይህን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ሙስናን፣ አድሏዊ አሰራርን፣ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነትን፣ የጥቅም ሰንሰለትን በየጊዜው እየበጣጠስን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ …በድርጅታችን ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን በአግባቡ ተንትኖ መረዳት እና በታጋይነት መንፈስ ትግል ማድረግ ያስፈልገናል›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ከዚህም ትግል በአሸናፊነት መውጣት እንደሚቻል ጠቅሰው ነበር፡፡ አሁን ትግሉ ከምን ደረጃ እንደሚገኝ ድርጅቱ ሊያሳውቀን ይገባል፡፡

በአጠቃላይ፤ የድርጅቱ እና የመንግስት ዋናው ፈተና ኪራይ ሰብሳቢነት እና የማስፈፀም አቅም (ክህሎት) ማነስ ነው፡፡ የአመራርን ክህሎት ለማሳደግ ብርቱ ትግል ማድረግ እንደሚገባም ግልጽ ነው፡፡ አመራሩ በታጋይነት መንፈስ የታጀበ እና ከአድርባይነት የፀዳ ትግል ማድረግ ተቻለ፤ ትግሉን በድል ማጠናቀቅ እንደሚቻል እሙን ነው፡፡ ሆኖም ድርጅቱ በዚህ ደረጃ ያለውን ወቅታዊ አቋም ሊያሳውቀን ይገባል፡፡

እንደምናስታውሰው፤ ታሪካዊው 10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የተካሄደው፤ በአምስተኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ማግስት ነበር፡፡ በዚህ ጉባዔ ድርጅቱ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ገምግሞ፤ 2ኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመተግበር ሂደት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ- ኢኮኖሚ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን ገልጾ ነበር፡፡ ጉባዔው በተጠቀሱት ችግሮች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት አካሂዶም ነበር። ‹‹ህዝባዊ አደራን በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን›› በሚል መሪ ቃል በመቀሌ ከተማ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ በርካታ ውሳኔዎችንም አሳልፏል፡፡ ድርጅቱ በጉባኤው ማጠቃለያ ባወጣው ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ፤

በድርጅታችን ኢህአዴግ ተሃድሶ ጠርቶ በወጣው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መሰመራችን በግልፅ እንደተቀመጠው፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በልማታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የመቀየር ጉዳይ የህዳሴ ጉዟችን ዋነኛ አቅጣጫ በማድረግ፣ ባለፉት ዓመታት በተካሄደ ርብርብ፤ በገጠር የልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት እየያዘ የመጣ ቢሆንም፣ በከተሞች አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የበላይነት እየያዘ እንደሚገኝ ጉባኤያችን ገምግሟል።

የብዙዎች ችግሮቻቸን መንስኤና ምንጭ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጋር የተያያዘ መሆኑን የተመለከተው ጉባዔያችን፣ በቀጣይ ዓመታት የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ሆነው የተለዩትን የመሬት፣ የግብር አሰባሰብ፣ የመንግስት ግዢና ኮንትራት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አስምሮበታል። በመሆኑም፣ እኛ የ10ኛ ድጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ተግባራት እንዲጎለበቱ የፀረኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከምን ጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ለመረባረብ ቃል እንገባለን፤ ብሎ ነበር።

በዚህ መሠረት፤በፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል፤ እንዲሁም በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሐብት ልማት ሚኒስቴር ትብብር ሰፊ ጥናት ተካሂዶ፤ጥናቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተዘጋጀ መድረክ ውይይት ተደርጎበት፤ ውይይቱም በቴሌቪዥን ተላልፎ ነበር፡፡ ያ ውይይት፤ መንግስት የመልካም አስተዳደርን እና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ህዝቡ እንዲገነዘብ ያደረገ ውይይት ነበር፡፡ ያ ውይይት የኪራይ ሰብሳቢነትን እና የመልካም አስተዳደርን ጉድለት ለመፍታት የሚያስችል የታጋይነት መንፈስ ለመፍጠር የሚያግዝ ውይይት ነበር፡፡ ያ ውይይት፤ ትግሉ በወሬ የሚቆም አለመሆኑን የሚያመለክት፤ በህዝቡ ዘንድ ተስፋን፤ በኪራይ ሰብሳቢዎች እና ሙሰኞች ዘንድ ደግሞ ተስፋ መቁረጥን ያነገሰ ውይይት ነበር፡፡

መንግስት የሞት ሽረት ትግል ሲጀምር፤ ኪራይ ሰብሳቢዎች እና ሙሰኞች በአጠገባቸው ባገኙት ‹‹ምሽግ›› ዘለው እየገቡ ራቸውን ለመከላከል መሞከራቸው የማይቀር በመሆኑ፤ ትግሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከረረ ሲሄድ ይታያል፡፡

አፍራሽ ኃይሎች በአጠቃላይ ፊታቸውን ወደዚህ ‹‹ምሽግ›› አዞሩ፤ ራሳቸውን ለማዳን እየተገፈታተሩ እና እየተረጋገጡ ዘለው መግባት ጀመሩ፡፡ የተለያየ የፖለቲካ መዝሙር ያላቸው እና በፖለቲካ እምነታቸው ‹‹እሣት እና ጭድ›› ሊባሉ የሚችሉ ኃይሎች ሁሉ ከአንድ ‹‹ምሽግ›› ገቡ፡፡

በፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል፤ እንዲሁም በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሐብት ልማት ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት በቀረበ ጊዜ፤ ‹‹ህዝቡ በየጊዜው ምሬቱን ሲገልጽ የሚሰማው ለምንድነው? ከማማረር ወጥቶ ወደ መቆጣጠር፣ መሳተፍ እና ውጤታማ የሆነ ተጽዕኖ ወይም ጫና በመንግስት ላይ ወደማሳረፍ ያልተንቀሳቀሰው ለምንድነው? ይህን እንዳያደርግ ምን ያዘው? ምን ከለከለው?›› የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫም ተቀምጦ ነበር፡፡

እንደሚታወቀው፤ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን የመጀመሪያ ፊሽካ የነፋው መንግስት ነው፡፡ ስለዚህ፤ መንግስት ራሱን ከችግር አጽድቶ የህዝቡን እንባ ለማበስ ቁርጠኛ ቢሆንም፤ በተጨባጭ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ግን አርኪ መሆን አልቻለም፡፡

የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል አዋጁ መርዶ ሆኖ ያስደነገጣቸው ቡድኖች እና የስርዐቱ ባላንጣዎች የህዝቡን አጀንዳ ነጥቀው የጥያቄውን ውል እያጠፉ፤ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሰላማዊ የተቃውሞ ሂደት ወጥቶ የፀጥታ ሥጋት እንዲሆን እንቅልፍ አጥተው እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡

መንግስት፤መስተካከል የሚገባውን ነገር ለማስተካካል ጥረት እያደረገ ከህዝብ ጋር መምከር ሲጀምር፤የተለያዩ ኃይሎች አጀንዳውን ሰርቀው በየአቅጣጫው እየጎተቱ፤ ችግሩን ከፌደራል ስርዓቱ ጋር በማያያዝ እና ችግሩን ብሔረሰባዊ ቅርጽ በማላበስ የፌደራል አወቃቀሩን ማውገዝ ይዘዋል፡፡

በሌላ በኩል፤ በህዝብ ብሶት ግሎ የተጀመረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደ ደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ ሊወስዳቸው መሆኑን የተረዱት የኢህአዴግን መዝሙር አቀንቃኝ ኪራይ ሰብሳቢዎች እና ሌሎች ሙሰኞች፤ በየጊዜው የሚከሰተው ሁከት ከመጣባቸው አደጋ የማምለጥ ዕድል እንደሚሰጣቸው በማሰብ እሣት በማንደድ እና በማቀጣጠል ተሳታፊ እየሆኑ ይታያሉ፡፡ በቅርቡም በህዝቦች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ ወደ ኋላ የማይሉ አመራሮች መኖራቸውን አይተናል፡፡

እንሚታወቀው፤ ለዘመናት ተሳስረው የኖሩ ህዝቦች በአስተዳደር ወሰን ምክንያት ሊጋጩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የሁሉም ህዝቦቻችን አጀንዳ፤ በሰላምና በአንድነት መኖር፣ ከድህነት መላቀቅና ዕድገታቸውን ማፋጠን ነው፡፡ ሆኖም የኢህአዴግን ፍቅር እየሸጡ ለመጠቀም የሚሞክሩት እና የኢህአዴግን ጥላቻ እየቸረቸሩ ለመኖር የሚፈልጉት ኃይሎች በአንድነት ተሰልፈው ስርዓቱን ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ፡፡

የሕዝቦችን አንድነት ለማዳከም እና ቁርሾን ለማባባስ እየሰሩ ነው፡፡ ግጭት የሕዝቦች ፍላጎት አይደለም፡፡ ተጋብተውና ተዋልደው ድንበር ሳይከልላቸው ለዘመናት በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በሰላምና በአንድነት የኖሩ ህዝቦች በአንድ ምሽት ወሰንን ምክንያት አድርገው ወደ ግጭት የማምራት ፍላጎት እንደማይኖራቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ፤ ከቀውሱ ማትረፍ የሚሹ ወገኖች፤ ጥፋትና ውድመት እያስከተሉ ነው፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ የሚቻለው የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ፤ እንዲሁም የመልካም አስተዳደርን እና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር በማስወገድ በመሆኑ፤ መንግስት በዚህ ረገድ ትግሉን አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል፡፡ ትግሉም የሞት ሽረት በመሆኑ ህዝቡ ሊያግዘው የግድ ነው!

 

  1. አብዲ ሰኢድ says

    በጣም አስተውሎት እና ብስለት የተላበሰ ጽሑፍ ፦ በዚሁ መንፈስ ትንሽ ልጨመርበት እንደሚታወሰዉ የቀድሞው ጠ / ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ከመሞታቸዉ ጥቂት ወራት በፊት በቴሌቪዥን ቀርበው ” ኢህአዴግ በውሰኞች እና ኪራይ ሰብሳቢዎች አንድ እጁ ታስሯል በመሆኑም እነዚህን ሀይሎች ለመታገል በምናደርገው የሞት ሽረት ትግል ህዝቡ ከጎናችን እንዲሰለፍ የሚል ጥሪ አስተላልፈው ነበር ። ይህ ታሪካዊ ጥሪ ከስድስት አመት በኋላ ይተንተን ብንል አንድ ትልቅ መጽሐፍ አይበቃውም ። ምክንያቱም የቀድሞው ጠ /ሚ በህይወት እያሉ ከነበራቸው ተሰሚነትና ክህሎት አለፎ የተበከለዉ ኃይል 50% ከነበር እራሳቸው በሌሉበት ስድስት አመት አንደልቡ የበልጥ ለመንሰራፋትና እራሱን ለመከላከል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውለታል ማለት ነው ። በመሆኑም ይህንን ኃይል መታገል የሞት ሽረት ጉዳይ ቢሆንም ትግሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅና ከላይ ወደ ታች የሚወርድ መሆን ይኖርበታል ። ምክንያቱም ይህ የተበከለ ኃይል በኔትወርክ የተሳሰረና በከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን ላይ የለ በመሆኑ በኔትወርኩ ውስጥ ያሉ የበታቾች ሲያዙ እራሱን ለመከላከል አገርን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚከት እርምጃ ለመውሰድ ወደኀላ የማይል በመሇኑ ነው ። ሰላም

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy