Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አማራጭ የሌለው ምርጫ

0 354

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አማራጭ የሌለው ምርጫ

ብ. ነጋሽ

ላለፉት ሀያስድስት ዓመታት እየሰለለ ቢመጣም አንድ ይዘቱ ሳይለወጥ የሚሰማ ቀረርቶ አለ። ኢትዮጵያ በብሄር ተከፋፈለች፣ አንድነቷ ጠፋ፣ ፌደራላዊ ሥርአቱ የሃገሪቱን አንድነትና ህልው አደጋ ላይ ይጥላል ወዘተ የሚል ቀረርቶ። በተለይ የማንነት፣ የአስተዳደር፣ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች በተነሱ ቁጥር፣ የሰለለው የአሃዳዊ ስርአት ናፋቂዎች ድምጽ ከዚያም፣ ከዚህም ይሰማል። ለምሳሌ ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል የተቀሰቀሰውን አለመግባባት መነሻ በማደረግ ያንቀላፋው ሁሉ ነቅቶ፣ ፌደራላዊ ሥርአቱን የችግር ምንጭ አድርጎ በመኮነን የአሃዳዊ ሥርአትን አስፈላጊነት እየሰበከ ይገኛል። አንዳንዶች ደግሞ ሃገሪቱ ካሁን በኋላ ወደአሃዳዊ ሥርአት ልትመለስ አትችልም፣ ፌደራላዊ ሥርአት ያስፈልጋታል ይሉና፣ የፌደራሉን አወቃቀር ግን በወንዝ፣ በተራራ፣ በሸለቆ ወዘተ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ይላሉ። አንዳንዶቹ ስልጡን መሆን የሚዳዳቸው አወቃቀሩ ዜግነትን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት ይላሉ። የሁለቱም መድረሻ አንድ ነው፤ በዜግነት ሽፋን ብሄራዊ ማንነትን ጨፍልቆ አሃዳዊ ሥርአት መመስረት።

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው የአሃዳዊ ሥርአት ነው፣ ዜግነትን መሰረት ያደረገ በወንዝ፣ ተራራ . . . የተዋቀረ ፌደራላዊ ሥርአት ነው የሚስማማት የሚሉት ግለሰቦችና ቡድኖች አንድ የረሱት ነገር አለ። ይህም ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር መሆኗን፤ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውጭ ትርጉም የሌላት መሆኗንና፣ እነዚህ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመብትና የነጻነት እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አንስተው የነበረ መሆኑን ነው።

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው አሃዳዊ ሥርአት ነው፤ ፌደራሊዝሙ በተፈጥሯዊ መልከዓምድር ላይ ተመስርቶ መዋቀር አለበት የሚሉ ወገኖች የሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎት ምንድነው? የሚለውን ማሰብ አይፈልጉም ወይም ረስተውታል።

አሁን ኢትዮጵያ የምንላት ምድር ላይ የነበረውንና ያለውን በሰዎች ፍላጎት ሊለወጥ የማይችል እውነታ እንመለከት። በቅድሚያ ይህች ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር በየራሳቸው መልከዓምድራዊ ወሰን የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ ወዘተ ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ሃገር ነች።

ይህች ምድር ፈጣሪ ያበጃት አይደለችም። በዚህ ቅርጿ የተፈጠረችና እስካሁን የዘለቀች ሃገርም አይደለችም። በውስጧ የሚኖሩት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በየራሳቸው አስተዳደር ሥር ይተዳደሩ የነበረበትን ዘመን አልፈዋል። ገሚሱ ፊውዳላዊ ነገስታት ወይም ሱልጣኖች ነበሯቸው። የተቀሩት ደግሞ በህዝብ ውክልና በተሰየመ ሸንጎ በጋራ አመራር (collective leadership) የሚተዳደሩ ነበሩ። አሁን ዓለም ከደረሰበት ዴሞክራሲ ጋር ተቀራራቢ ባህሪ ያለው የህዝብ ውክልና የአስተዳደር ሥርአት ያላቸውም ነበሩ።

አሁን በዚህች ሃገር ውስጥ የሚኖሩት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደየተፈጥሯዊ አካባቢያቸው፣ በእርስ በርስ ግንኙነታቸው ውስጥ እንዳለፉበት አጋጣሚ ወዘተ አንዱ ከሌላው የሚለይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ የዚህ ትስስር መገለጫ የሆነ ባህል አላቸው። እንደሚገኙበት መልከዓመድር አዋሳኝነትና ታሪካዊ አጋጣሚ አንዱ የሌላውን ባህል የተጋሩበት ሁኔታ አለ። በተለያየ ታሪካዊ አጋጣሚ አንድ ሁለቱ በአንድ የአስተዳደር ሥርአት ሥር የወደቁበት፣ መልሰው የተለያዩበት፣ እንደገና ደግሞ የተገናኙበት እውነታም አለ።

ያም ሆነ ይህ፣ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በአንድ የመንግሥት ሥርአት ሥር መተዳዳር የጀመረችው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ነው። በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት። እርግጥ ከዚያ ቀደም ይህች ኢትዮጵያ የምትባለውን ምድር አንድ አድርጎ የመግዛት ፍላጎት የነበራቸውና የሞከሩም ይኖራሉ። ተሳክቶላቸው አንድ ሃገር አድርገው መግዛት የቻሉት ግን ዳግማዊ ምኒሊክ ናቸው። አንድ አድርገው የገዙት በሃይል፣ በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በዲፖሎማሲ ስልት ነው፤ በማባበል። በተለይ የአሃዳዊ ሥርአት ደጋፊዎችና ተስፈኞች ይህን እውነት መቀበል አይፈልጉም፤ ሲሰሙት ይበሳጫሉ። በደፈናው አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ለሦስት ሺህ ዘመን በአንድ የመንግስት ሥርአት ሥር ስትተዳደር የኖረች ሃገር መሆኗን እንድንቀበል ነው የሚፈልጉት። ይህን ምንም ሳንጠይቅ ልክ እንደሃይማኖት ቀኖና እንድንቀበለው ነው የሚፈልጉት።

በዳግማዊ ንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በአንድ የመንግሥት ሥርአት ሥር እንዲተዳደሩ ሲደረግ ለማንነታቸው እውቅና አልተሰጠም። በየሚኖሩበት ወሰን ውስጥ የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ በፈቀደላቸው የመንግስት ሥርአት መተዳደር የሚችሉበት ዕድል አልተሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ማንነት በአንድ ብሄራዊ ማንነት – የዜግነት መለያ የተደረገ ብሄራዊ ማንነት ሥር በመጨፍለቅ አሃዳዊ ሃገር የመፍጠር ስትራቴጂ ነበር የተከተሉት። ልብ በሉ፤ ችግሩ ያለው አንድነቱ ላይ ሳይሆን፤ አንድነቱ የተፈጠረበት መንገድ ላይ ነው። የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የተስፋፊ ነገስታትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የመሬት አንድነት ነበር የተፈጠረው።

ዘውዳዊው ሥርአት ይህን ስትራቴጂ ለማስፈጸም የከፋፍለህ ግዛ ስልትን ተከትሏል። አንድ ማንነት ያለው በአንድ መልከዓምድር ውስጥ የሚኖር ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነ ቦታ ተበጣጥሶ እንዲዋቀር ተደርጓል። ሁለትና ከዚያ በላይ የተለያየ ማንነት – ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ ወዘተ ያላቸው በአንድ መዋቅር ሥር እንዲጨፈለቁ ተደረጓል። በዚህ ሁኔታ ጠቅላይ ግዛት፣ አውራጃ . . . እየተባለ የተዋቀረው የህዝብን ማንነት፣ መብት፣ ጥቅምና ፍላጎት መሰረት ያላደረገ የአስተዳደር አወቃቀር በገዢነት ለፊውዳል መሳፍንትና መኳንንት ተሰጠ።

ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምረው በየደረጃው ለሚገኙት ገዢ መሳፍንትና መኳንንት ግዛትህ ነው ተብሎ ለተሰጣቸው መሬት እንጂ በላዩ ላይ ለሚኖረው ህዝብ ዋጋ አልሰጡትም። ህዝቡ ዘለዓለም ዘር ማንዘሩ የኖረበት መሬት ላይ የባለቤትነት መብት የሌለው የንጉሠ ነገሥቱን፣ መሳፍንትና መኳንነቱን ጥቅም የሚያሟላ ገባር ተደረገ።

በተለይ ነገሥታቱ የእኛ ማንነት ነው ከሚሉት ብሄራዊ ማንነትና ቋንቋ ውጭ ያሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊ ማንነታቸውም ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ተደረገ። ሰብአዊ ማንነታቸው ዝቅ በመደረጉ፣ የማንነታቸው መገለጫ የሆኑት ቋንቋ፣ ባህልና ወግ፣ ታሪክ ወዘተ ተንቋሸሹ። ከነገሥታቱ ማንነት የተለዩ ብሄራዊ ማንነቶች የሚያሳፍሩ እንዲሆኑ ተደረገ።

ይህ አሁንም በህይወት ያሉ ኢትዮጵያውያን ያለፉበት የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። ይህን እውነት መረዳት ጥልቅ የታሪክ ምርምር አይጠይቅም። አፍንጫችን ሥር ያለ እውነት ነው። ይህን ተጨባጭ ዕውነታ ያልተረዳና ያልተቀበለ የአሁኗን ኢትዮጵያ ማወቅም መምራትም አይችልም።

እንግዲህ፤ መሬታቸው ተጠንጥቆ ለመሳፍንቱ፣ ለመኳንነቱና ሌሎች ሹመኞች ገባርነት የተዳረጉ፣ ብሄራዊ ማንነታቸው በህግ እውቅና የተነፈገ፣ በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት ማግኘት እንዳይችሉ፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳያስተምሩ፣ ባህላቸውን እንዳያስተዋውቁና እንዳያጎለብቱ፣ ታሪካቸውን እንዳይንከባከቡ የተደረጉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህ ጭቆና ከላያችን መነሳት አለበት የሚል ጥያቄ አንስተዋል። የመሬታቸው ባለቤት እንዲሆኑ፣ በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲያስተምሩ፣ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ታሪካቸውን እንዲንከባከቡ፣ በወኪሎቻቸው አማካኝነት እንዲተዳደሩ ነበር የጠየቁት። የብሄር ጥያቄ ማለት ይህ ነው።

ይህ ጭቆና የወለደው የብሄራዊ መብትና ነጻነት ጥያቄ ግን በቀላሉ ምላሽ ማግኘት አልቻለም። ጭቆናው ምላሽ ማጣቱ የብሄራዊ መብትና ነጻነት ጥያቄ ባነሱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና በአሃዳዊው ሥርአት መሃከል ቅራኔ ፈጠረ። ይህ ቅራኔ እያደረ ተካሮ የትጥቅ ትግል ወለደ። ከ1983 ዓ/ም በፊት በሃገሪቱ  በብሄር የተደራጁ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የነበሩ ከሃያ በላይ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ያደረጋቸው ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው። የመጨረሻው አሃዳዊ ሥርአት – ወታደራዊው ደርግ ከሥልጣን የተወገደው በዚህ በየአቅጣጫው በተከፈተ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የነጻነት የትጥቅ ትግል ነው።

ወታደራዊው ደርግ ከተወገደ በኋላ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት የነበረችው ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር መንታ መንገድ ላይ ቆመች። አንደኛው መንገድ ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህዝባቸውን ማስተዳደር የሚያስችላቸውን ነጻ መንግስት መመስረት የሚያስችል አማራጭ ነው።

ሌላኛው የብሄራዊ መብትና ነጻነት ጥያቄዎች – ብሄሮች ብሄረሰቦች በሚኖሩበት መልከዓመድራዊ ወሰን ውስጥ በቋንቋቸው የመንግሥት አገልግሎት የማግኘት፤ ልጆቻቸውን በቋንቋቸው የማስተማር፣ ባህላቸውን የማጎልበት፣ ታሪካቸውን የመንከባከብ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የወሰን ሳይሆን በልዩነት ውስጥ የህዝቦች አንድነት ያለው የመግስት ሥርአት ሥር መኖር የሚያስችል መንገድ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ አዳራሽ ታድመው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ከእነዚህ ከተጋፈጧቸው ሁለት መንገዶች አንዱን መረጡ፤ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ያለው የመንግስት ሥርአት ገንብተው መኖር።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ይህን የመረጡትን ሥርአት ለመገንባት የገቡት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይህ ሥርአት አሁን ያለው ፌደራላዊ ሥርአት ነው። ይህ ሥርአት በመላ ሃገሪቱ ለነጻነት ይካሄድ የነበረውን ጦርነት አስቀርቶ ሰላም አስፍኗል። የሰፈነው ሰላም የህዝቡን ኑሮ በተጨባጭ የቀየረ ልማት ማምጣት አስችሏል። ይህ ራሱን የጃለ ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ጽሁፍ ከዚህ በላይ በዝርዝር አልገባበትም።

ይህን ፌደራላዊ ሥርአት ብናፈረሰው የሚቀረው አማራጭ አንድ ብቻ ነው፤ መለያየት። የአሃዳዊ ሥርአት አማራጭ መሬት ላይ የለም። የአሃዳዊ ሥርአት አማራጭ ያለው በተጨባጭ ሳይሆን በጥቂት ሰዎች አእምሮ ውስጥ ነው።

አሁን በዋናነት በብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተውን ፌደራላዊ ሥርአት በማፍረስ ወደ አሃዳዊ ሥርአት ለመመለስ መፈለግ የሌለን ነገር ለመጨበጥ ከመሞከር አይለይም። ፌደራላዊ ሥርአቱ ከፈረሰ የሚተካው ሁሉም ብሄሮች ነጻ መንግስት የሚመሰርቱበት አማራጭ ብቻ ነው። ፌደራላዊ አወቃቀሩ መልከዓምድራዊ ይሁን የሚለው አማራጭም ከህዝብ – ኢትዮጵያ የምትባለዋን ሃገር ከመሰረቱት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ፍላጎትና ጥያቄ ውጭ ስለሆነ ማረፊያ የለውም። ማረፊያ የሌለው ሥርአት መገንባት ደግሞ አይቻልም።

በአጠቃላይ አሁን ያለው በዋናነት በብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ፌራላዊ ሥርአት በሃገሪቱ የነበረው መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ የወለደው በታሪካዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የመጣ ነው። የሃገሪቱን አንድነት ለማስቀጠል አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy