Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አካባቢያዊ ዴሞክራሲ በአገሪቱ አጠቃላይ

0 368

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አካባቢያዊ ዴሞክራሲ በአገሪቱ አጠቃላይ

የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ላይ ∙∙∙∙

ስሜነህ

በሀገራችን ብዙ እርከኖች ያሉት የመንግሥት ሥርዓት ተዘርግቷል። ሦስት ራሳቸውን የቻሉና ነፃነት ያላቸው የመንግሥት እርከኖች ማለትም የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት እና አካባቢያዊ አስተዳደሮችን የማዋቀር ሥልጣን በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ይህ ልዩነት በእያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮ ውስጥ የሰረፀ አይመስልም። ይህ ደግሞ ካለፈው አሀዳዊ የመንግሥት ሥርዓት የወረስነው እና ልንፋታው አንድ ያቃተን አስተሳሰብ መኖሩን የሚያመላክት ነው። ይህ አስተሳሰብ ማዕከላዊውን ወይም የፌዴራል መንግሥቱን መቆጣጠር ወሳኝ እንደሆነ፤ ይልቁንም የፌዴራል መንግሥቱን መቆጣጠር ከማዕከሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ወዲያውኑ ለመቆጣጠር ያበቃል የሚልና ነባራዊውን እውነታ ያላገናዘበ አስተሳሰብ ነው።

የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መነሻና ማብላያው ከታች የሚገኙት ምክር ቤቶች ቢሆኑም በኛ ሃገር የሚገኙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ብሔራዊ እና/ወይም አገር አቀፍ የሆኑት ማዕከላዊው ወይም ፌዴራል መንግሥቱ ላይ እንጂ ወደነዚህ ምክር ቤቶች ትኩረት ሲያደርጉ አንመለከትም። በእርግጥ በአካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይገጥሙናል የሚሏቸው እና ሲገጥሟቸውም የምንመለከታቸው ለሥራና ለውድድር ምቹ ያልሆኑ የአስተዳደርና የፖለቲካ ጭቆናዎች በርከት ያሉ ናቸው። በየአካባቢው የሚስተዋሉት እነዚህ የተለያዩ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ደግሞ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው። ይሁንና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እነዚህን ሁሉ ጫናዎች መቋቋምን ታሳቢ ያደረገ ተሳትፎ ይጠይቃል።  

በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በከተማና በዞን ደረጃ ያሉ አካባቢያዊ ምክር ቤቶች ወንበሮች ቁጥር ከ600 ሺህ ወደ 3.6 ሚሊዮን እንዲጨምር ያደረገው ማሻሻያ በ2000 ዓ.ም በሥራ ላይ ውሏል። ይህ ማሻሻያ የተደረገው ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ “የሕዝቦችን የፖለቲካ ውክልናና ተሳትፎ ለማሳደግ” ቢሆንም ከላይ በተመለከተው አግባብ ተቃዋሚዎቹ ሲጠቀሙበት አይስተዋልም።  

በመሰረቱ አካባቢያዊ ምክር ቤቶችን ለፖለቲካ ስልጣን መወጣጫ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም። አሁን ህዝብ እየተንጫጫበት ለሚገኘው የመልካም አስተዳደር ችግር አካባቢያዊ ምክር ቤቶች ሁነኛ መፍትሄዎች ናቸው። እነዚህን ምክር ቤቶች ስለፖለቲካ ስልጣን ብቻ ሳይሆን ለቀጥተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ መድረክ እንደሆኑ መውሰድ ብልህነት ነው። ይህ አመለካከት በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ደረጃ መድበለ ፓርቲ አስፈላጊ እንዳልሆነ ያመለክታል። በዚህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ የሃገሪቱን አጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወደፊት ማራመድ አዳጋች ይሆናል። ይልቁንም በየአካባቢው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ተቆጪና ከልካይ በማጣት የበለጠ በህዝቡ ላይ እንዲፈነጩና በዚህም የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቱ ወደኋላ እንዲመለስ ያደርጉታል። የገዢው ፓርቲ ድርጅታዊ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት የቁጥር ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲች በአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ውስጥ የተወሰኑ መቀመጫዎችን እንዲያሸንፉ ለማስቻል ብቻ ሳይሆን፣ ለአካባቢያዊ ዴሞክራሲ ጤናማ ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠርም ነው።

በዚህ አግባብ እና ስለዚሁ የሃገርና የህዝብ ጠቀሜታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነዚህ ምክር ቤቶች እንዲወዳደሩ እና የነቃ ተሳትፎ ለምን እንደማያደርጉ ሲጠየቁ አካባቢያዊ ምርጫዎች ገዥው ፓርቲ የሕዝብ መተማመኛ የሚያገኝባቸው መሣሪያዎች እንጂ በራሳቸው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግባቸው አይደሉም ሲሉ ይተቻሉ። ይህ አተያይ በራሱ ተቃዋሚዎቹ በላኞቹ ምክር ቤትም የሚወዳደሩት ስለስልጣን እንጂ ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት መጎልበት እንዳልሆነ የሚያመላክት ነው።

ይልቁንም ከተቃዋሚ ፓርዎቹ እይታ በተቃራኒ እንደ ኢሕአዴግ ያሉ ግዙፍና ጠንካራ ፓርቲዎችን ለማሸነፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ከመቆጣጠር መጀመር እንዳለባቸውና በዚህም ቀስ በቀስ የፌዴራል መንግሥቱን የመቆጣጠር አቅም መገንባት የሚችሉ መሆኑን የሚመክሩ ጠበብቶች ብዙ ናቸው።

የነዚህ ጠበብቶች ጥናት እንደሚያመለክተው በሃገራችን የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ የፌዴራል መንግሥትን መቆጣጠር በእርግጠኝነት አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ለመቆጣጠር ያስችላል የሚል ስትራቴጂ  እንደሚከተሉ ነው። ያም ሆኖ ግን  ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፌዴራል መንግሥቱን ለመቆጣጠር በማሰብ ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊት፣ ከዚያ በመለስ ያሉ የመንግሥት እርከኖች ላይ በማተኮር ጠንካራ የፖለቲካ መሠረት መፍጠር ያለባቸው መሆኑን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ቁንጮ ናቸው የሚባሉ ሃገራትም ከዚህ ውጭ እንዳልሆኑ ጠቅሰው ይከራከራሉ። ሌሎች ምክንያቶችን እንኳ ትተን የኛን ሃገር ተሞክሮ እንኳ ብንመለከት ኢሕአዴግ የፌዴራል መንግሥቱን የተቆጣጠረው የአካባቢያዊ ምክር ቤቶችን ስለተቆጣጠረ እንጂ የፌደራሉን መንግስት ስለተቆጣጠረ አይደለም።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካባቢያዊ አስተዳደሮችን መቆጣጠራቸው የፖሊሲያቸውን ውጤታማነት ለመፈተሽ፣ የአስተዳደር ልምድ እንዲቀስሙ፣ እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ የሚከለክሏቸው ጨቋኝ አካባቢያዊ ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ በምርጫ ስኬት እንዳያስመዘግቡ እንቅፋት ሆነውብናል የሚሏቸውን ሌሎች ችግሮች ለማስወገድ የሚያስችላቸው የመሆኑን እውነታ እንኳ ስናጤን እየተከተሉት ያለው ስትራቴጂ እንኳንስ ለሃገር እና ህዝብ ለራሳቸውም ጠቃሚ አይሆንም።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር እያደረጉ በሚገኘው ድርድር ይህን ወሳኝ ጉዳይ አጀንዳ አለማድረጋቸው አሳሳቢ እና በድርድራቸው ለማትረፍ የፈለጉት ምን እንደሆነም ግራ የሚያጋባ ነው። ስለሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ምርጫዎች ለመወዳደርና ለማሸነፍ በጣሩበት መጠን እንዲያሸንፉ የሚያስችሉ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ከባቢ ሁኔታዎች አስቀድመው መሟላታቸውን ታሳቢ ያደረገ አጀንዳ ሊቀርጹ በተገባ ነበር። ይህ አለመሆኑ ደግሞ ግባቸውን ከወዲሁ እንድንጠራጠር ያስገድዳል።  

በህዝቡም ዘንድ አካባቢያዊ ዴሞክራሲ በአገሪቱ አጠቃላይ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ላይ ሊጫወት የሚችለው ግዙፍ ሚና ላይ ግንዛቤ ያለ አይመስልም። የበለጠ የሚያሳስበው ደግሞ የችግሮች ሁሉ መፈልፈያ በአካባቢያዊ የአስተዳደር እርከኖች ላይ ሆኖ ሳለ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ አለመያዙ ነው። የአሜሪካን ዴሞክራሲ በጥንቃቄ ያጠኑት ፈረንሣዊው ፈላስፋ አሌክሲስ ዲቶክቪሌ አሜሪካ በዋነኛነት ዴሞክራሲያዊ አገር የሆነችው፣ አካባቢያዊ ዴሞክራሲን በቅድሚያ በማረጋገጧ እንደሆነ ይገልጻሉ። በሌላ በኩል በአገራችን አካባቢያዊ አስተዳደር ሲነሳ ወደ አዕምሮ የሚመጣው ትንሽ ፈላጭ ቆራጭ ሰው ነው። ስለዚህ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በመንግስት፤ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚዎቹ ዘንድ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል። በአካባቢያዊ ዴሞክራሲ ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ሚዲያውም በጥልቀት ሊሰራ ይገባል።

የስራው አጀማመርም  መሆን የሚገባው ማዕከላዊውን መንግሥት የሚመሩ አካላት አካባቢያዊ አስተዳደሮችንና አካባቢያዊ ባለሥልጣናትን እንደ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከመቀበል ሊሆን ይገባዋል። አካባቢያዊ አስተዳደሮች ነፃነት ብቻ ሳይሆን፤ በዴሞክራሲያዊ መርህ የሚመራ አመራር ያላቸው መሆናቸውንም መቀበል ያስፈልጋል። ስለመድበለ ፓርቲ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ  አካባቢያዊ አስተዳደሮች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ ወሳኝና መሰረታዊ መሆኑ ላይ ከተግባባን፤ ስለዚሁ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት ሊወስዷቸው የሚገቡ ወሳኝ እርምጃዎች አሉ። አካባቢያዊ አስተዳደሮች የሁለቱ የመንግሥት እርከኖች አስተዳደራዊ ወኪሎች ሳይሆኑ፣ ራሳቸውን የቻሉ የመንግሥት እርከኖች እንደሆኑ ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። በአገሪቱ አካባቢያዊ ዴሞክራሲ ለማስፈን የአካባቢያዊ አስተዳደሮችን ሥልጣንና ተግባር በግልጽ ማስቀመጥም ሌላኛው ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ነው። ይህ ከሆነ ስለመልካም አስተዳደር ሀገር የሚንጫጫባቸው ጉዳዮችን ጨምሮ ጉራማይሌ የሆኑ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እንቅፋቶችን በማስወገድ የተሻለች እና ሁሉ-አቀፍ በሆነ መልክ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy