Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እድገት በየፈርጁ

0 346

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እድገት በየፈርጁ

                                                            መዝገቡ ዋኘው

 

አለም አቀፍ ተቋማት በተለመደው መልኩ ስለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ የሚሰጡትን አስተያየት በስፋት ቀጥለዋል፡፡ ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል ሀገራችን ብዙ ርቀት ተጉዛለች፡፡ ከተሰራው በላይ ገና ብዙም ይቀረናል፡፡ ግዙፍ የሚታዩና የሚጨበጡ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ የመሰረተ ልማት እድገትና መስፋፋት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን በከተሞችና በገጠር በስፋት የማስፋፋት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

 

ትምህርት ቤቶችን፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን፤ እንዲሁም የጤና አገልግሎቶችን ከከተማ እስከ ገጠር የማስፋፋት፤ ድልድዮችን የመስራት፤ በከተሞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የማስፋፋትና ሕዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ፤ የመተላለፊያ ችግር በነበረባቸው ኮሪደሮች የዘመናዊ ድልድዮችና የታላላቅ ግድቦች ግንባታ በማድረግ ከዚህ በፊት የነበረውን የኃይል ማመንጫ አቅም በማሳደግ ረገድም ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ ግቤን፣ ኦሞን፣ የአባይን ግድብን የመሳሰሉ ታላላቅ ግንባታዎች ለመስራትና ለመገንባት የበቃች ሀገር ነች፡፡ በከተሞች መስፋፋትና ማደግ መሰረታዊና ስርነቀል ለውጦችን አስመዝግባለች፡፡ በግብርናው መስክ ቀድሞ የነበረውን ኋላቀር አስተራረስ በመለወጥ ዘመናዊ ግብርና በአርሶ አደሩና በአርብቶ አደሩ ውስጥ እንዲሰርጽ ሰፊ የማስተማር ስራዎች በባለሙያዎች ለአመታት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን አሁንም ቀጥሎአል፡፡

 

የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ለውጥ ለመከላከል የሚያስችል ሰፊ ስራም የተሰራበት ነው፡፡ ድርቅን በመከላከልና የተፈጥሮ የአየር ንብረትን በመጠበቅ ረገድ ሰፊ ለውጦችን ማስመዝገብ ችለናል፡፡ የተራቆቱ፣ በውሀ መሸርሸር የተጎዱ መሬቶችን የማከምና እንደገናም በብሔራዊ ደረጃ በተያዘው ችግን ተከላ ፕሮግራም መሰረት በየአመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በማፍላትና በመላው ሀገሪቱ የማከፋፋልና የመትከል  ፕሮግራም በየአመቱ የሚካሄድ ሲሆን ይህም የተመዘገቡ ከፍተኛ ለውጦችን አስገኝቶአል፡፡

 

በሀገር ደረጃ የደን ሽፋን መጠናችን አድጎአል፡፡ ባዶ የነበሩና የተራቆቱ መሬቶችን በተለያዩ ተክሎችና ደኖች መሸፈን ተችሎአል፡፡ በዚህም ምክንያት ምንጭ ማመንጨት ችለዋል፡፡ ጠፍተውና ተሰውረው የነበሩ የዱር እንሰሳትና አእዋፋት ወደየቦታቸው መመለስ ጀምረዋል፤ መሬቶችን ከፍተኛ ዝናብን ተከትሎ ከሚመጣውን የመሬት መሸርሸር መታደግ፤ የውሀ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የጥልቅ ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ በማድረግ በተለያዩ ክልሎች ሰፊ ስራዎችን በመስራት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሎአል፡፡

 

ወንዞቻችን በተለይም ምንም ጥቅም ሳይሰጡ ለዘመናት ሲፈሱ የነበሩትን በመጥለፍና ለልማት እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ሰፊ ሰራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ቀድሞ በአርብቶ አደርነት ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩና ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው ለከብቶቻቸው መኖና ውሀ ፍለጋ ሲዞሩ የነበሩትን ወገኖች በአንድ ቦታ እንዲሰፍሩ በማድረግ የማሕበራዊ አገልግሎቶች፣ የትምሕርት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃና የመሳሰሉት ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

 

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በመስኖ ልማትም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መልክ በሁሉም ክልሎች የመስኖ ልማትን የማስፋፋትና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች በስፋት በእቅድና ተይዘው እየተሰራባቸው ይገኛል፡፡ ይህም በሀገር ደረጃ ዝናብን ብቻ ከመጠበቅና የዝናብ ጥገኛ ከመሆን በመላቀቅ በየትኛውም ወቅት ዘርቶ ማምረት የሚቻልበትን፤ በተለይም ለመሰረታዊ ፍጆታ የሚውሉ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ተጠቃሚ ለማደረግ የሚያስችላቸው ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡

 

ሀገራችን ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንም በመገንባት በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንዱስትሪ መናሀሪያ እንደምትሆን አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሀን በስፋት እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም የሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ በቀዳሚ ምሳሌነት እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ በተለያዩ መስኮች የሚታዩት ጉልሕ እድገቶች ሀገራችን በከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የምትገኝ መሆንዋን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እነዚህንም ምስክርነቶች የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀንና ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥተዋል፡፡

 

በ2010 አ.ም የኢትዮጵያ አማካኝ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 9 በመቶ እንደሚያድግ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ በድረገጹ ገልጾአል፤ በሚ/ር ሁሊዮ እስኮላኖ የሚመራው የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ልኡካን ቡድን ከመስከረም 3 እስከ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በነበረው ቆይታ ከኢትዮጵያ ጋር በ2017 በአንቀጽ 15 የምክክር ውይይት ማድረጉን ቡድኑ በኢትዮጵያ መንግስት የ2010 በጀት፣ የበጀት ጉድለት፣ የገንዘብ ፖሊሲዎችን በማለሳለስ ጉዳይ እና በብር ዋጋ፤ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መደራደሩን ድረገጹ ዘግቧል፡፡ በ2016 ዓ.ም የአለም ኢኮኖሚ ከፍተኛ መቀዛቀዝ ውስጥ የገባ ቢሆንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጫናውን ለመቋቋም መብቃቱን በውይይቱ ተሳተፊ የነበሩት የአይ.ኤም.ኤፍ ከፍተኛ ባለስልጣናት መመስከራቸውን ድረገጹ አስታውቋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለማሰለስ መቀጠሉን በዚህም በ2016/17 አመት ውስጥ የአገሪቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በአማካኝ በዘጠኝ በመቶ እንደሚያድግ ባለስልጣናቱ ማሳወቃቸውን በድርጅቱ ድረገጽ ላይ የሰፈረው ሪፖርት የገለጸ ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት የተሰጠ ትልቅ ምስክርነት ነው፡፡  

 

በተገኘው የእድገትና የልማት ለውጥ ውስጥ የተለያዩ የውጭ ኢንቨስተሮች በብዛት ወደሀገራችን በመግባት በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ማድረግ መቻላቸው የራሱን ከፍተኛ ሚና ተጫውቶአል፡፡ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ረገድም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

 

የሕንድ ካቢኔ በኢትዮጵያና በሕንድ መካከል በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንና ሚድያ ዘርፍ ትብብር ለማድረግ የቀረበውን የውሳኔ ኃሳብ ማጽደቁን ኒውኬራላ ድረገጽ ከሰሞኑ  ዘግቧል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኔርሜንድራ ሞዲ ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር በኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፎች በሰፊው በትብብር ለመስራት የሚያስችላትን የትብብር ኃሳብ የሁለቱም ምክር ቤት አባላት በተገኙበት የካቢኔ ስብሰባ ማጽደቃቸውን ዘገባው ገልጾአል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንና  ሚዲያን ፍላጎት በማሳደግና አቅርቦቱን በማሻሻል ረገድ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ዘላቂ ወዳጅነትና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ መናገራቸውን ድረገጹ አስነብቦአል፡፡

 

የቻይናው ዜና ወኪል ቺንዋ በበኩሉ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የቻይና ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ማስታወቁን ዘግቧል፡፡ የቻይና ቱሪስቶች ቁጥር ባለፉት አመታት እየጨመረ መምጣቱን ዘገባው ገልጾ እ.ኤ.አ 2012 ዓ.ም 35ሺ383 የነበረው የቻይና ጎብኚዎች ቁጥር እ.ኤ.አ 2015 ወደ 41ሺ660 ማደጉን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያ አቶ ካሳሁን አያሌው መናገራቸውን ጠቅሶአል፡፡

የቻይና ጎብኚዎች ቁጥር ከአሜሪካና ከእንግሊዝ ከሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ቢያንስም ጎብኚዎቹ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ብዙ ወጪ በማውጣት ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሆናቸውን ባለሙያው መምሰከራቸውን የዜና አውታሩ በድረገጹ አስነብቧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 እና 2016 ኢትዮጵያ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የነበረች ቢሆንም የቻይና ቱሪስቶች ቁጥር ከምእራባውያን አንፃር ከፍተኛ እንደነበር ዘገባው ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ከብራዚሉ አየር መንገድ ጋር የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ማድረጉን ዘ ጋርድያን በድረገጹ አስነብቦአል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከብራዚሉ አየር መንገድ ጋር የተፈራረመው በደንበኞች አገልግሎትና በበረራ መስመሮች ዙሪያ በጋራ አብሮ ለመስራት የሚያስችለው ስምምነት መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡

ሮይተርስን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያና የአለም ባንክ የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የድጋፍና ብድር ስምምነት መፈራረማቸውን በዘገባቸው አስታውቀዋል፡፡ የአለም ባንክ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምትተገብረው የሴፍቲ ኔት መርሐ ግብር የሚውል የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድርና ድጋፍ ማቅረቡን የጠቆሙት ዘገባዎቹ ከአጠቃላይ ገንዘቡ 700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በብድር የተገኝ ሲሆን 600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላሩ ደግሞ በድጋፍ የተሰጠ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ስምምነቱን የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሐም ተከስተና በምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያና የሁለቱ ሱዳኖች የአለም ባንክ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ መፈራረማቸውን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል፡፡ የአለም ባንክ የአሁኑ የገንዘብ ድጋፍ ለድርቅ አደጋ የሚሰጠውን ምላሽ በመደገፉ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ባንኩ መግለጹን ዘገባዎቹ ያስረዳሉ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy