Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከግጭት አትራፊው ማን ይሆን? (ክፍል አንድ)

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከግጭት አትራፊው ማን ይሆን?

(ክፍል አንድ)

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢትዮጵያ ህዝቦች የህይወትና የአካል ጉዳት የጠየቀውን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ዜጎቿ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሰፈነባት አገር መፍጠር ችለዋል፡፡  የምልአተ ህዝቡ የትግሉ ውጤት ደግሞ አምባገነኑን የደርግ ሥርዓት በማስወገድ ዋናው ጠላታቸው ከሆነው ድህነት ፊት ለፊት በመግጠም የድላቸውን ውጤት ማጣጣም ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡

ገጠርን ከከተማ ያስተሳሰሩ ሰፋፊ የመሠረተ ልማትና የማህበራዊ ግልጋሎት አውታሮችን ግዙፍ ሃብት በመመደብ ልማትን ማፋጠንና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውና የማህበራዊ ተቋማት መስፋፋታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ስትገለፅበት ከነበረው የድህነትና ኋላ ቀርነት ተምሣሌትነት ቀስ በቀስ  እያላቀቃት ይገኛል፡፡

በመጀመሪያው አምስት ዓመታት የተተገበረው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ታሳቢ ያደረጉ ሁኔታዎች የተመቻቹበት ሲሆን የዕቅዱን የሁለተኛ ምዕራፍ ለመተግበርም ሌላ ዕቅድ ተነድፎና የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቅቆ ወደተግባር ከተገባ ሦስተኛ ዓመት ተጀምሯል።  

በዚህ ዕቅድ መጠናቀቂያ ዘመን አገሪቱ ወደ ዝቅተኛው የመካከለኛ ገቢ ላይ ትደርሳለች ተብሎ ይገመታል። ይህም በ2017 ዓ.ም ትደርስበታለች ለተባለው የመካከለኛ ኢኮኖሚ የእድገት ደረጃ መደላድል ይፈጥራል፡፡

በዚህ አመርቂ ጉዞ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህዝቦች የድል ታሪክ ግን አሁንም  ዋነኛ ጠላቶች ከፊት ለፊቱ ተጋርጠውበት ይገኛሉ፡፡ ድህነት ዋነኛ አጀንዳ ነው። ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ በከተሞች ከባድ ፈተና እየሆነ መምጣቱ የሚደበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ሀዝቦችም በእያንዳንዷ የድህነት ማስወገድ ጉዟቸው ውስጥ ጉልበታቸውን ወደኋላ የሚጎትተውን አካል በጠላትነት ፈርጀው በጠላታቸው ላይ የተባበረ ክንዳቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በ5ኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝቡን ሙሉ ይሁንታ አግኝቶ መንግሥት የመሠረተው በኢሕአዴግና አጋሮቹ  የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፤ በህዝቡ የተቀናጀ የፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ወደኋላ የሚጎትቱ አመለካከቶችና ተግባራትን ለማስወገድና የህዝቡን የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለመምራት አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በአጀንዳው ዙሪያም ህዝቡ በሙሉ አቅሙ ለመሳተፍ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡

በዚህ ወቅት የህዝቡንና የመንግሥትን ትግል ለማኮላሸት ታጥቀው የተነሱ ፀረ ሠላምና ጥገኛ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ርብርብ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ርብርባቸው ዳገት የማይወጣና የመጨረሻ መፍጨርጨር መሆኑ የታወቀ ቢሆንም የተወሰኑ አካላትን አሳስተው ወደ ችግር መክተታቸው አልቀረም።

በተለይ እስካሁን ድረስ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ በነበረው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ሂደት ሁለት ቦታ ረግጠው የነበሩ አካላት በየጊዜው ከየተቀበሩበት ሁሉ ሳይቀር ነፍስ ዘርተው እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡ አሁን ግን ህዝብና መንግሥት አንድ ሆነው የመረረ ትግል ለማድረግ እንደወሰኑ ገብቷቸዋል፡፡ ይህ የተደራጀ የህዝብና የመንግሥት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደማይለቃቸውና እንደሚጠራርጋቸው ሲገነዘቡ ያልሞት ባይ ተጋድሏቸውን ሞክረዋል፡፡  

በ1999 ዓ.ም በወጣው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ስትራቴጂ ላይ በፀረ ድህነት ትግል ውስጥ ከሚገጥሙ ፈተናዎች አንዱ በኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ውሰጥ የሚደበቁ ትምክህትና ጠባብነት መሆናቸው በግልፅ ተቀምጧል፡፡

በመፅሐፉ ገፅ 84 ላይ “ህዝቡ ከኪራይ ሰብሳቢነት ተጠቃሚ ባይሆንም ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ተፅዕኖ ውጭ ስለማይሆን ለመንግሥትና ለኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ባለህ ቀረቤታ ፍርፋሪ ይገኛል የሚል እምነት እንዲይዝ በሚያደርጉ ኃይሎች አስተሳሰብ ሥር እንዲወድቅ ስለሚደረግ በአካባቢ፣ በኃይማኖት፣ በብሄር ወዘተ…ላንተ ቆመናል በሚሉ አካላት አዝማሚያ ይኖረዋል” ይላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ውይይት በተካሄደበት አንድ መድረክ ላይ እንዲህ ብለው ነበር። “ካሁን በኋላ ሃሳባችንን እዚህ ጨርሰን እንውጣ፡፡ ውይይቱን ጨርሰን ስንወጣ የአካባቢና አብሮ አደጋችን እንዳይጠቃብን የሚለውን አሰተሳሰብ ማቆም አለብን” የሚለው ቁርጠኝነት የተሞላበት ንግግር ተጠቃሽ ነው።

አሁን ባለንበት ወሣኝ ወቅት ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትን የማድረቅና መልካም አስተዳደር የማስፈን ትግል ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ እዚህ ላይ ኢሕአዴግ ዕድለኛ ሊያሰኘው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ህዝቡ እያንዳንዷን ክፍተት ለይቶ የመናገር ድፍረቱ በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ህዝቡ በግልፅ እንዲናገር ህገ መንግሥቱ ያጎናፀፈው መብት ቢሆንም እንዲናገር ያስገደደው ግን ለአገሪቷ ልማት ካለው ቀናኢነት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በየደረጃው በሚታዩ መድረኮች በህዝቡ የሚስተዋለው ግልፅ አቋም በፍርፋሪ ሳይሆን በሥራና ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ ብቻ የአገራችን እድገት እንደሚረጋገጥ ግልፅ አቋም መያዙን ነው፡፡ ይህ እንደ ኢሕአዴግ ላለ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የያዘ ድርጅት የህዝብን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ አገር ለመምራት ስለሚረዳ ዕድለኛ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ግን ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሉ ያለ የሌለ አቅሙን በመጠቀም መሸሸጊያ ለማግኘት እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡ ለዓመታት ህዝብ ከህዝብ የማለያየት አጀንዳ ሲያራምዱ የቆዩ፣ በመካከላቸው ከፍተኛ ቅራኔ ያላቸው ትምክህተኛና ጠባብ ኃይሎች ሳይቀሩ አንድ ግንባር ላይ የተሰለፉበት ሁኔታ የመፈጠሩ ጉዳይ ለዚህ ሁነኛ ማሣያ ነው፡፡ ሰሞኑን ከኦሮሚያ እና ከኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት ከማሣያዎቹ አንዱ ነው፡፡   

መንግሥትና ህዝብ በያዙት ቁርጠኛ አቋም የተደናገጡና በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ ሆኖ የነበሩ አካላት በትግሉ ሂደት ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ በመሆኑ ከወዲሁ ትግሉ እንዳይፋፋም ሳንካ በመሆን የመንግሥት ትኩረት ለማስለወጥ ሆን ብለው ያቀነባበሩት አጀንዳ ነው።

ከዚም በተጨማሪም ግርግሩን ተጠቅመው መንግሥትን በኃይል በመገልበጥ ሥልጣን ለመያዝ ምኞት ያላቸው ጠባብና የትምክህት ኃይሎች ሴራቸውን ጎንጉነዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተለይ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ግብ የሌለው ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡

በተለይ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ኃይሎች የጠባብነትና የትምክህት ያልተሳካ ጋብቻ በመፍጠር በህዝብ አመኔታ ወደሥልጣን መውጣት ሲያቅታቸው የመጨረሻ ዕድላቸው በዚህ አመፅ ለማሳካት የሚሞክሩ ናቸው፡፡

እነዚህ ኃይሎች በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ከሥልጣን ከማውረድና ጥምር መንግሥት ከመመሥረት ጉዳይ ፍፁም የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፡፡  የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ዓይነት ነገር ካልሆነ፡፡ ዋና መንደርደሪያቸው በየትኛውም መልኩ ሥልጣን በመያዝ አገሪቷን ለኒዮሊበራል ኃይሉ አሳልፎ በመስጠት የራሳቸውን የግልና የቡድን ጥቅም ማደለብ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢዎች አጀንዳ ለህዝቡ ምንም ጥቅም ባይሰጥም ህዝቡ በአካባቢና በኃይማኖት ወይም በሌላ ስሜት ሰለባ በማድረግ እነሱ ወደ ቀረፁት አጀንዳ በማስገባት መጠቀሚያ ለማድረግ በየጊዜው ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በሚቀይሱት መሰሪ አጀንዳ የሚወድመው ንብረትና ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች መኖራቸው እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም ተሳክቶላቸው ግን አያውቅም፡፡

ሁሌም አንግበው የሚይዙት አጀንዳ የህዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ ወደፊትም ቢሆን ይሳካላቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳው ግጭት በዚህ ቅኝት የሚታይ ነው፡፡

መንግሥት የማረጋጋት ሥራውን እያከናወነ ለችግሩ ተጠያቂ የሚሆኑ ኃይሎችን ለህዝብ በማጋለጥ ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የሀሳቡ ጠንሳሽና አራማጆች በየምሽጋቸው ተደብቀው አይቀሯትም፡፡ ህዝቡም እየጠየቀ ያለው ዋጋቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዲያገኙ ነው፡፡

የነዚህ የጠባብ ኃይሎች ዋና ዓላማ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ትግሉን ለመጥለፍ ነውና ከማረጋጋት ሥራው ማግስት መንግሥት ህዝብን አሳትፎ እነዚህን ኃይሎች የማጋለጥ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ተግባርም ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የልማቱን እንቅፋቶች ለመጠራረግ ተዘጋጅቷል፡፡ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር ቢኖር መቼውንም ቢሆን ከልማት ጉዟችን እንደማያስቆሙን ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy