Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘላቂነት ያለው ጥልቅ ተሐድሶ ለዘላቂ ልማት

0 954

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዘላቂነት ያለው ጥልቅ ተሐድሶ ለዘላቂ ልማት

ይልቃል ፍርዱ

 

የጥልቅ ተሀድሶው ንቅናቄ ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ በምን መልክ እየሄደ ነው የሚለው ጥያቄ ሰፊ የመነጋገሪያ ርእስ ከሆነ ውሎ አድሮአል፡፡ ይሄንን በጥልቀት ማየትና መፈተሸ ተሀድሶውን ከሚመራው አካል በሰፊው ይጠበቃል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የጥልቀታዊው መታደስ እንቅስቃሴ በስፋት በሀገር ደረጃ የቀጠለ ሲሆን ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

በሀገር ደረጃ እየተካሄደ ያለው የተሀድሶ ለውጥ መንግስታዊ ተቋማትን የሲቪል ሰራተኛውንና የኢህአዴግን ድርጅታዊ መዋቅርና አባላቱንም በአጠቃላይ ያቀፈና ያሣተፈ በመሆኑ ሰፊ የማጥራት ስራዎች ተሰርተዋል፤ እንቅስቃሴው ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎችም የመሸፈነ ነው፡፡ በዚህም መሰረት አሁን ያለው ሀገራዊ ስእል በንጽጽር ከቀደመው ሁኔታ ጋር ሲመዘን ተሀድሶው የተሻለ ለውጦችን ማስመዝገብ ችሎአል፡፡

በአገር ደረጃ በሙስና ላይ የተጀመረው ትግል ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶአል፡፡  የሚጠበቀው ተጠናክሮ መቀጠሉ ብቻ ነው፡፡ እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ተንሰራፍቶ የቆየው ሙስና በመንግስትና በሕዝብ ንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት መግለጽ ከሚቻለውም በላይ የገዘፈ ነው፡፡

መንግስታዊ ተቋማትና ድርጅቶች የከተማና የክልል መስተዳድሮች የመሬት ይዞታ የኮንስትራክሽን ዘርፉና ሌሎችም የከፋና አስደንጋጭ ዘረፋ ተካሂዶባቸዋል፡፡ እስከአሁን በተጠርጣሪነት በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ውጭ ከሕዝብ በሚገኘው ጥቆማና ተጨባጭ ማስረጃ መሰረት በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙት ተጠያቂ መሆን ባለባቸው ደረጃ ተጠያቂ እየሆኑ ነው፡፡

በሕዝብና በመንግስት ሀብት መቀለድም ሆነ መጫወት የሚያስከትለው ከፍተኛ ተጠያቂነት አለ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሙሰኞችን የማሸሽና የመደበቅ፣  ለእነርሱም ጥብቅና ቆሞ የመከራከር ሁኔታዎች እየታዩ ሲሆን ይህ አካሄድ ከሀገርና ከሕዝብ በተቃራኒ በመቆም ጸረ ሀገርና ጸረ ሕዝብ አቋም መያዝ ማለት ነው፡፡

ግለሰቦችን በማሰርና በሕግ ተጠያቂ በማድረግ የሚመጣ ለውጥ የለም በሚል ሽፋን ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጡ ለማድረግ የሚሰጥ አይረቤ ምንያት ነው፡፡ ግለሰቦች ሕግን ተላልፈው የመንግስትና የሕዝብን ሀብት ዘርፈው እስከተገኙ ድረስ በየትኛውም ደረጃ ቢሆን ከሕግ ተጠያቂነት ሊድኑ ወይንም ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ ለነዚህ ሽፋንና ከለላ የሚሰጥ ግለሰብም ሆነ የመንግስት ኃላፊ የወንጀል ድርጊቱ ተባባሪ እንደሆነ ተደርጎ ነው በሕጉ የሚታየው፡፡

ይህ ደግሞ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሕጋዊ ሽፋን እንዲያገኝ የማድረግን ያህል የሚሰራ መሰረታዊ ስህተት ነው። በእርግጥ ሁኔታውን መለወጥ የሚቻለው ደረጃ በደረጃና በሂደት መሆኑ ቢታወቅም ይህም እስኪሆን ድረስ ግለሰቦች በሰሩት ስራ አይጠየቁም የሚል ሕግ በየትኛውም የአለም ከፍል የለም። ዋናውና ትልቁ ቁም ነገር ግልጽነትና ተጠያቂነት በየደረጃው እንዲሰፍን በሕጋዊነት መልኩ እንዲቀጥል ማድረጉ ላይ ነው፡፡

መንግስትና ሕዝብ አምኖ በኃላፊነት ያስቀመጣቸው ሰዎች በእንዲህ አይነት ከፍተኛ የሆነ የእምነት ማጉደል ላይ ሲገኙ ሕዝብንም መንግስትንም ያስደነግጣል፡፡ በሕግ ይጠየቁ ዘንድም ግድ ይላል፡፡ እምነት ማጉደል አደራ በላነት የመንግስትና የሕዝብን ሀብት መዝረፍ በየትኛውም ሀገር ሕግ ያስጠይቃል፡፡

የተሀድሶው መሪና የንቅናቄውም ባለቤት ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ በመላው ሀገሪቱ ሰፊ የተሀድሶ ንቅናቄዎች ተደርገዋል፡፡ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ በሙስና በኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው በተገኙ በተለያየ ደረጃ በነበሩ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዶአል፡፡ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መንግስትና ሕዝብን በማታለል ሲሰሩ የነበሩ የመንግስት ሲቪል ሰርቪስ አባላት በሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ ተጋልጠዋል፤ ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡ በሙስና ውስጥ የተገኙና በሕዝብ የተጋለጡ ታስረዋል፤ ፍርድ ቤትም ቀርበዋል፤ ንብረታቸው ታግዶአል፡፡ ቀደም ሲል አቃቤ ሕግ በማስረጃ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ካደረጋቸው የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት መስሪያቤቶች ኃላፊዎችና የበታች ሰራተኞች ሌላ የማጣራት ሂደቱ በመቀጠል ላይ ይገኛል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ፊቼ ከተማ አስተዳደር ሕገ ወጥ ንግድ በማንቀሳቀስ ማግኘት የነበረብኝን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተውኛል ባላቸው የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስተዳደሩ አስታወቋል፡፡ ከአስተዳደሩ ንግድ እና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ ቀረጥ እና ግብር ሳይከፍሉ በሕገወጥ መንገድ የሚነግዱ ከ1ሺህ 6ዐዐ በላይ ግለሰቦች እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ ሕገወጥ ነጋዴዎቹ በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደራቸውም ሌላ ባለፈው በጀት ዓመት መንግሥት ከግብር ማግኘት የነበረበትን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲያጣ ማድረጋቸውን ጽሕፈት ቤቱ ለመገናኛ ብዙሀን ገልጾአል፡፡ ይሄም በሀገር ላይ የሚፈጸመው ሙስና አንደኛው ማሳያ ነው፡፡

ሕገወጥ ነጋዴዎቹ በከተማዋ ከግብርና ቀረጥ ለመሸሽ አመቺ ጊዜ እየጠበቁ በመፈራረቅ እንደሚንቀሳቀሱ ያመለከተው ጽሕፈት ቤቱ  አብዛኞዎቹ ሕገወጥ ነጋዴዎች  በአዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ በቤት ውስጥ የመገልገያ ቁሳቁሶች፣ በወተት ማሰባሰብና ማከፋፈል፣ በሴራሚክ ችርቻሮ፣ በአሸዋና ጠጠር ንግድ ስራ . . . የተሰማሩ መሆናቸው ተገልጾአል፡፡ ይሄም ከመንግስት ካዝና በመስረቅ ሕዝብ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎትና ልማት እንዳያገኝ ማድረግ ርህራሄ የጎደለው ሙስና ነው፡፡

በሌላም በኩል በትግራይ ክልል ከቀረጥ ነጻ የገባ ከ809 ሺህ በላይ ኩንታል ብረታብረት የት እንደገባ እንደማይታወቅ የክልሉ ከተማ ልማት ንግድና ኢንዳስትሪ ቢሮ ለዋልታ አንፎርሜሽን ማእከል በአመቱ መገባደጃ አካባቢ መግለጻቸው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሀገራዊ አደጋ እንደሆነና የሕዝብና የሀገርን ልማት ምን ያህል እየጎዳ እንደሆነ በገሀድ የሚያሳይ ነው፡፡ ለሚያስበው ሰው 809 ሺህ ኩንታል ብረት ትግራይ ክልል ከገባ በኋላ መቸም ክንፍ አውጥቶ አይበርም፡፡ ዘረፋው አስደናቂም አስገራሚም አይነት ሙስና ነው፡፡

የቢሮው የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት የኢንቨስትመንት ቡድን አስተባባሪ አቶ ለይኩን አብርሐ ለዋልታ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት ባለሐብቶችን ለማበረታታት የተለያዩ ድጋፍ በመፍቀድ ተጠቃሚዎች እያደረገ ቢሆንም አንዳንድ ባለሐብቶች ማበረታቻውን ላልተፈቀደ ዓላማ እያዋሉት ስለመሆኑ ከሕብረተሰቡ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ባለሀብቶቹን ለማበረታታት ሲል ልዩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ባለሀብት የተባሉት ደግሞ ወደሌላ የሙስና ስራ (አየር በአየር ንግድ) ይገባሉ። ይህም መንግስትና ሕዝብ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም በማሳጣት ለራሳቸው ያውሉታል ማለት ነው፡፡

በዚህም መሰረት በሆቴል ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚ ከሆኑ 184 ባለሐብቶች ውስጥ 181 ባለሐብቶች ከሚያስፈልጋቸው በላይ ትርፍ መውሰዳቸውን በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ኃላፊው የገለጹ ሲሆን ይህ በበኩሉ መንግስትንም ሕዝብንም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ ተረጋግጧል፡፡

የተካሄደው ጥናት ውጤት የሚያሳየው በፕላኑ መሰረት ለ184ቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራዎች የሚያስፈልገው የብረታብረት መጠን 182ሺህ 906 ነጥብ 2 ኩንታል ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባለሐብቶቹ ከቀረጥ ነፃ ያስገቡት የብረታብረት መጠን ከ498 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውና 982ሺህ 654 ነጥብ 8 ኩንታል ብረታብረት መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ከዚሁም ውስጥ ለግንባታ ስራ የዋለው  140ሺህ 548 ነጥብ 7 ኩንታል ብቻ ሲሆን በመጋዝን የተገኘው ደግሞ 16ሺህ 216 ነጥብ 62 ኩንታል ብረታብረት መሆኑ መረጋገጡን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ባለሐብቶቹ ሊፈቀድላቸው ከሚገባው በላይ 406ሚሊዮን 454ሺህ 785 ብር ግምት ያለው 800 ሺህ 555 ነጥብ 4 ኩንታል ብረታብረት በማስገባት መውሰዳቸውን አቶ ለይኩን የገለጹ ሲሆን ለዚህም ቀጣይ የማጥራት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ ቀሪ ሶስት ባለሐብቶች ግን ከጠየቁት መጠን በታች የግንባታ ብረታብረት ከመውሰዳቸውም ባሻገር ላስገቡትም ቀረጥ ጨምረው መክፈላቸውን የዳሰሳ ጥናቱ ማመልከቱን ተናግረዋል፡፡  በተመሳሳይም በትግራይ ክልል ከ2008 ዓመተ ምሕረት በፊት ፍቃድ ከተሰጣቸው ባለሐብቶች ውስጥ በተደረገው ክትትል 78ቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰርቴፊኬት ወስደው በልማት ስራዎች ላይ በወቅቱ ያልተሰማሩ፤ የ78ቱ ፈቃዳቸው መሰረዙን አቶ ለይኩን ገልጸዋል፡፡ ሙስና በተወሰነ ቦታ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ተንሰራፍቶ የሚገኝ ስለሆነ በጥልቀታዊው ተሀድሶ አማካኝነት በስፋት የሚዘምትበት አሳሳቢ ሀገራዊ ጉዳይ ነው የሚባለው፡፡

የተሀድሶው ውጤት የሆነው ሙሰኞችን  በሕግ ተጠያቂ አድርጎ በማስረጃ የማቅረቡ ስራ በስፋት የቀጠለ ሲሆን የአዲስ  አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና በመጠርጠር  በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን  በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩ የሥራ  ኃላፊዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት  መታየቱ ቀጥሎአል፡፡ ወደፊትም የመሳሳቡና የመጓተቱ ሁኔታ ስለሚኖር በርካታ ሰዎች ሊታሰሩ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመሬት አስተዳደር፤ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ፤ ጽዳትና ውበት አስተዳደር ኤጀንሲ፤ ጉምሩክ፤ ባሕር ትራንዚት፤ ንግድ መርከብ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፤ እንዲሁም በተለያዩ መንግስታዊ ድርጅቶ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይሄ እርምጃና የተደረሰበት ደረጃ የጥልቅ ተሀድሶው ውጤት ነው፡፡

ማስረጃዎቹ በእጅጉ አስገራሚ ናቸው፡፡ ስነምግባር ምን ያህል እንደወረደ፤ የት ላይ እንደተደረሰም ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ በዚህም መሰረት ተጠርጣሪዎቹ በወረዳ አንድ አዳሪ ሰፈር፣ የቤት ቁጥር 620 እና 621 የተለያዩ ቤቶች መሆናቸውን እያወቁ ከአሰራር ውጪ ካልተያዙ ተጠርጣሪ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር፥ የ621 ቤት ነዋሪ ሕይወታቸው ማለፉን እያወቁ ካርታ አዘጋጅተው ለሌላ ግለሰብ በመስጠት ወንጀል የተጠረጠሩም ይገኙበታል፡፡ ሌላም ብዙ ብዙ ጉድ የሚያሰኙ የሙሰኞችና የኪራይ ሰብሳቢዎች ተግባራት ገና ይጋለጣሉ፡፡ ጥልቅ ተሀድሶው በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡

ባጠቃላይ፣ በጥልቅ ተሃድሶው አማካኝነት ባለፈው ዓመት በተካሄደው ትግል የስርዓቱ ዋነኛ አደጋዎች የነበሩትን የትምክህትና የጠባብነት አመለካከትና ተግባራት እየነቀሱ በመምጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ የጥልቅ ተሃድሶው የመንግሥት አመራሩና ሲቪል ሰርቫንቱን ለበለጠ ትግል እንዲነሳሱ ያደረገ ሲሆን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትና የወለዳቸው ልዩ ልዩ ችግሮች በዘለቄታው ሊፈቱ እንደሚችሉ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ አሳድሮአል፡፡ መነቃቃትም ፈጥሮአል፡፡ ይህ እንዳይኮላሽም አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ መደረግበ አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy