Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እያደገ ነው!

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.


የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እያደገ ነው!

                                                        ታዬ ከበደ

ፌዴራሊዝም ጥቂቶችን ሳይሆን አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ነው። ዜጎች በሥርዓቱ ውስጥ በሰሩት ልማታዊ ተግባር ልክ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ይጠቀማሉ። ፌዴራሊዝም የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የኑሮ ሁኔታ በመለወጥ ተጠቃሚነታቸውን ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገና ከነገ ወዲያ እያሳደገ በመሄድ ረገድ ኢትዮጵያ ዋነኛ ማሳያ ናት።

ከድህረ-ደርግ ውድቀት በኋላ የተረጋጋች እና ህዝቦቿም አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት መስርተው እርስ በርሳቸው እየተከባበሩ በፈጠሩት ፈጣን ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበትን ሀገር ለመገንባት እጅግ የመረረ ትግልን መጠየቁ አይዘነጋም፡፡ ታዲያ ይህን ሃቅ የማይቀበሉና ጥቅማቸው የተነካባቸው ፅንፈኞች ትናንትም ነበሩ፣ዛሬም አሉ።  

እርግጥ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሀገራችን የተቀዳጃቸውን ድሎች በርካታ ቢሆኑም የቀድሞውን ስርዓት የሚናፍቁ ሃይሎች ዛሬም የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕለት በመጣ ቁጥር በቁጭት የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም። ሆኖም ትርጉም የለውም።

አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት እንደተደመሰሰ ለሌላ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ ተራማጅ የሆኑ፣ ፌዴራሊዝም ወሳኝ ለዘመናት ደም አፍሳሽ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ያመኑ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የመኖራቸው ያህል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሁለት ጽንፍ ጫፍ ላይ የወጡ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ።

አንደኛው በወቅቱ አስራ ሰባት የታጠቁ የብሔር ድርጅቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮች መፍትሄ መገነጣጠል ነው ብለው ያምኑ የነበሩ እና ለዚህም እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች እንደነበሩ ያለፈው ድርሳናቸው ያወሳል፡፡ሁለተኛው አዲሱን የሀገሪቱ መፍትሔ እና ፍቱን መድኃኒት የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት ግንባታ እንደ መበታተን አደጋ በመመልከት ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን “በእኛ እናውቅልሃለን” የፖለቲካ እሽክርክሪት በማጦዝ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡

ታዲያ በወቅቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በሰከነ ብስለት በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊት ሀገርን ለመመስረት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ከባድ ትግል ማካሄድ ግድ ብሎ እንደ ነበርና ውጤቱም በተራማጅ ሃይሎች አሸናፊነት እልባት እንደተሰጠው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ በኋላም ቢሆን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሀገሪቱ ለመግለጽ በሚያስቸግር መልኩ ከባድ ፈተናዎች እንደገና ከፊት ለፊቷ ተደቀነባት፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች የላቀ ስፍራ የያዘው እና የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት የሆነው “ድህነትን” የመዋጋት ዘመቻ ነው፡፡ ይህ ጠላት ዓይኑን አፍጥጦ የመጣ ጋሬጣ ሆኖባታል፡፡

ታዲያ ይህ የጋራ ጠላት የሚደመስሰው በመንግስትና በህዝብ የተባበረ ክንድ በመሆኑ፤ ችግሩን ለመቅረፍ በቅድሚያ መንግስት የመሪነት ሚናውን በመወጣት ህዝቡን በአስተሳሰብ ደረጃ በድህነት ላይ ድል እንዲቀዳጅ የማድረግ ኃላፊነን በሚገባ ለመውጣት ነበር ቆርጦ ወደ ትግበራ ለመግባት የተዘጋጀው፡፡

በወቅቱ ‘ድህነትን የመታገል ታላቅ ጉዞ እንዴት ሊከናወን ይቸላል?፣ ይህንን የጋራ ጠላት ተዋግቶ ለማሸነፍ መሰረታዊ የሚባሉ ቁልፍ ጉዳዮችስ ምንድናቸው? ወዘተ’ የሚሉ ዋና ዋና ተግባራትን መለየት በእጅጉ ወሳኝ ነበር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ግን በቅድሚያ የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነው ህገ – መንግስት ማጽደቅ ግድ አለ፡፡

ምንም እንኳን የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን ህገ – መንግስት ለማጽደቅ መንግስት መድረኩን ክፍት ቢያደርገውም ፤ አንዳንድ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች ሁኔታውን በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ ይሁንና ስልጣን ከህዝብ የሚመነጭ እንደሆነ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግስት ለእነዚህ ወገኖች ማስተማሩን አላቋረጠም፡፡ እናም ስልጣን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደሆነም በተደጋጋሚ በህዝቡ ዘንድ የማስረጽ ስራን አከናወነ፡፡    

እንደሚታወቀው ሁሉ ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥትን ለመከተል ከሚያስገድዱ ምከንያቶች አንዱ የማንነት ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠት ነው፡፡ በመሆኑም ከፍ ብሎ ከተገለፁት የማንነት አያያዝ መንገዶች የተሻለ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን ያጣመረ ሥርዓት በመሆኑ በርካታ ማንነቶች ባሏቸው ሀገራት ለማንነቶች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው ሥልጣን ያጐናጽፋል፡፡

እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ ሰፊ ቦታ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ሁሉም ፌዴሬሽኖች ተመሣሣይ አወቃቀር ስለማይከተሉ በማንነቶች ላይ የተመሠረተ አወቃቀር የሌላቸው ፌዴሬሽኖች ተጨማሪ የቋንቋና ሌሎች የፖሊሲ እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቅድመ ፌዴራል ሥርዓት ዘመን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እሥር ቤት የነበረች ሀገር ናት፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ  ሕገ መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ኃይማኖቶች እኩል መሆናቸውንና አብሮ ለመኖር ያላቸውን ተስፋ በፌዴሬሽኑ ሰንደቅ ዓላማ መሃል በተቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የሚንፀባረቅ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች እኩል እውቅና የተሰጣቸው ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልልም የሥራ ቋንቋ የመምረጥ መብት አለው፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጐ ይገኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብቱ የተረጋገጠ መሆኑም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠለ መብታቸው መጠበቁን፣ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መበት አለው፡፡ እንዲሁም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት የተረጋገጠለት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡

ከዚህም ጋር ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ መስኮች ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸውንና ከዚህ በፊት በነበረው ልዩነት ምክንያት የተፈጠረባቸውን ጫና ለመቅረፍ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተደንግጓል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት መሆኑን ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረትም የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለ23 ዓመታት መረጋገጥ ችሏል፡፡ ይህ ተጠቃሚነታቸው ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy