Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴያችን ፍቱን መድሃኒት

0 265

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴያችን ፍቱን መድሃኒት

                                                     ዘአማን በላይ

መንግስትና ህዝብ እያካሄዱት ያለው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በጊዜያዊነት የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ሀገራችን አሳካዋለው ብላ በትልምነት የያዘችውን ህዳሴያችንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑን እያመላከተ ነው። በእስካሁኑ ሂደት ጥልቅ ተሃድሶው ህዳሴያችንን ለማረጋገጥ ፍቱን መድሃኒት መሆኑን እያረጋገጠ ነው።

በሀገራችን ውስጥ ያለውን የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስርዓትን ለማረጋገጥ የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያጠያይቅ አይደለም። ችግሮች ተጠራቅመው ህዝብን ለብሶት የሚያጋልጡ ከሆኑ በተጀመሩት ሁለንተናዊ ለውጦች ላይ የበኩላቸውን አሉታዊ ሚና ማሳረፋቸው አይቀርም። ዜጎች በረባ ባልረባው ጉዳይ የሚጨቃጨቁ ከሆነ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እንዲፈጠሩ የሚፈልጓቸውን የለውጥ ተግባሮችን እውን ሊያደርጉ አይችሉም። እናም ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስትም ይሁን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ግዴታ መወጣት ማድረግ ይኖርበታል።

ይህን እገዛ ለማድረግ የህዳሴያችን ፍቱን መድሃኒት ሆኖ የተገኘውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ይበልጥ በማጠናከር የለውጥ ሂደቱ በተጨማጭ ሁኔታ እንዲታገዝ ማድረግ ይገባል። እንደሚታወቀው የተሃድሶው ሂደት በቀጥታ ፊት ለፊት መንግስትንና ህዝቡን የሚያገናኝ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ከዋነኛ ተዋናዩ ማግኘት ያስቻለ ነው። ያሉት ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶው በግልፅ ተለይተዋል። የችግሮቹን ትክክለኛ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ ለማወቅ፣ አውቆም ለመረዳትና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት አሁንም ጥልቅ ተሃድሶው ወደ ህብተሰቡ ውስጥ ተጠናክሮ መዝለቅ አለበት።

ሁሉም ነገር በተሃድሶው የአንድ ወቅት ሁኔታ ይፈታል እያልኩ አይደለም። የተሃድሶ ጊዜን ይጠይቃል። ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት የችግሮቹ መንስኤ የሆኑት ጉዳዩች መጣራት አለባቸው። አንዳንዶቹ መንስኤዎች ምናልባትም ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው። ምናልባትም ህዝቡ እንደ ችግር ሳይሆን ‘በይሁንታ’ ይዟቸው የመጡ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ ይህን መሰል ችግሮችን ለመፍታት ዘለግ ያለ ጊዜ መጠየቁ አይቀርም። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ችግሮች ዘለግ ያሉ ጊዜያትን ስለሚጠይቁ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ይገባል እያልኩ አይደለም—ይልቁንም ችግሮቹ መሰረታዊ እንዳይሆኑ ለመቀነስ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል እያልኩ እንጂ።

ምንም እንኳን በተሃድሶው ሂደት ወቅት ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሹ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ብቅ ማለታቸው የሚታወቅ ቢሆንም፤ እነዚህ ሃይሎች እያንዳንዱን የተሃድሶ እንቅስቃሴ ለማጣጣል የተለያዩ እጅና እግር የሌላቸውን የቅጥፈት ሰበዞችን ለመምዘዝ ቢሞክሩም ተሃድሶው በየጊዜውና በተያዘለት አቅጣጫ መሰረት ግለቱን እየጨመረ እየሄደ ነው።

ያም ሆኖ ሂደቱን ለማጨናገፍ እነዚህ ኃይሎች የማይቧጥጡት ነገር የለም። እነዚህ ሁከት መፍጠር መደበኛ ስራቸው የሆኑ ኃይሎች በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ ከመንዛር እስከ ተጨባጩንና ውጤት ያመጣውን ተሃድሶ “የይስሙላ ነው” እስከማለት ደርሰዋል። ዳሩ ግን ህዝቡ ራሱ የጥልቅ ተሃድሶው ባለቤት በመሆኑ ያራመዱትን አሉባልታ ሊያዳምጥ አልፈለገም። ወደፊትም አያዳምጥም።

የተሃድሶው ባለቤት የሆነውና በአሁኑ ወቅት ወደ ጠያቂነት የተሸጋገረው የሀገራችን ህዝብ ‘እውነት ብትቀጥንም አትበጠስም’ እንደሚባለው መንግስት ዛሬም ሆነ ነገ እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው የተሃድሶ እንስቃሴ ውጤት እንደሚያመጣ ያውቃል። ይህ እውነታም የሁከትና የትርምስ ኃይሎቹ የሀገራችንን ዕድገት እንዲሁም ብልፅግና የማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ኃይሎች እንጂ ከየትኛውም ብሔርና ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑንም ተገንዝቧል። ይህ ግንዛቤውም የእነዚህን ሃይሎች ፍላጎት መና ያስቀረ ነው ማለት ይቻላል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ለህዝብ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ህዝቡም በማንኛውም ተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ በማንኛውም ወቅት ከቦታው የማንሳት መብት እንዳለው ያስቀምጣል። መነሻው የህዝብ የስልጣን ሉዓላዊነት መከበር ነው።

ህዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ሿሚና ሻሪ የሚሆነው እርሱ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ስልጣን የሚመነጨው ከህዝብ እንጂ ከማንም አይደለም። ተሿሚው በህዝብ በጎ ፈቃድ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥና የሚነሳ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ተሿሚው በራሱ ፈቃድ አይደለም ስልጣን ላይ የተቀመጠው። ጥሩ ሲሰራ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት፣ ሲደክምም ድክመቱን የሚያሳየውና ከዚያ በላይም በገሃድ በምዝበራ ውስጥ ገብቶ ሲገኝ ካለበት ቦታ የሚያነሳው ህዝብ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ፈላጭና ቆራጩ ህዝብ እንጂ ባለስልጣን አይደለም። ሊሆንም አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ባለፉት ስርዓቶች እንዲቀር ያደረጉት ነው።

እናም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ያላመነበትና ያልመከረበት ነገር አይከናወንም። ሰሞነኛው የፀረ ሙስናው ጉዳይ በጥልቅ ተሃድሶው ጅማሮ ወቅት መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚዋጋ የገባው ቃል አንዱ ክፍል ነው ማለት ይቻላል። ህዝቡም ቢሆን ይህ የመንግስትን ቃል በተግባር ተተርጉሞ ማየት ይፈልግ ነበር።

የኪራይ ሰብሳቢነትን የፖለቲካል ኢኮኖሚ በአንድ ጊዜ መናድ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነቱን እንዳይዝ ሁሌም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ኪራይ ሰብሳቢነት በገነነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ልማታዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ መንገድን መገንባት አይቻልም። ኪራይ ሰብሳቢነት ማነቆ ይሆናል። እናም ተግባሩንና አስተሳሰቡን ሁሌም መድፈቅ ያስፈልጋል።

በተለይም እንደ እኛ ሀገር ልማት የህልውናው ጉዳይ በሆነ ሀገር ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢነት ልማታዊ አስተሳሰብን ካሸነፈ ችግሩ እጅግ የበረታ ይሆናል። ማንኛውም ዜጋ በሰራው ስራ ልክ ተጠቃሚ አይሆንም። የ“እንጠቃቀም” የትስስር ሰንሰለት ገቢራዊ እየሆነ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ሊኖር አይችልም። ይህም በግለሰብ ከፍ ሲልም በሀገር ላይ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። እናም የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ከስር ከስሩ እየተከታተሉ ማምከን የግድ ይላል።

ቀደም ሲል በመግቢያዬ አካባቢ ለመጠቆም እንደሞከርኩት አንዳንድ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡና ማህበረሰቡ ቅቡል ያደረጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ማህበረሰባችን ዛሬም ድረስ እንደ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፣ በምስጋና የሚኖሩ የሰማይ መላዕክት ናቸው…ወዘተ.” ዓይነት የተሳሳቱና ከምድራዊው አሰራር ጋር የማይሄዱ አባባሎችንና አስተሳሰቦችን የሚያራምድ በመሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ በአንድ ጊዜ ለመናድ ከባድ ሊያደርገው ይችላል። ሆኖም ተከታተይ ትምህርት በመስጠትና የመንግስትን ትክክለኛ አሰራር ከተጠያቂነት ጋር አዛምዶ በጥልቀት በማሳየት ችግሩን በሂደት ለመቅረፍ ይቻላል።

ርግጥ በአሁኑ ወቅት በህዝቡ ውስጥ ‘ለምን፣ እንዴት?’ የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እየተነሱ ነው። እነዚህ ጥያቄዎች ጥልቅ ተሃድሶውን ይበልጥ ለማጥለቅ የሚረዱ ናቸው። የህዝቡን የባለቤትነት ስሜት በከፍተኛ ደረጃም የሚያልቁ ጭምር። ይህ መንፈስ እጅግ እየጎለበተ ከሄደ ህዝብና መንግስት ‘የሀገራችንን ህዳሴ እውን እናደርጋለን’ በማለት ያቀዱትን አይቀሬ ትልም በቅርቡ እውን ሊያደርጉት ይችላሉ። ለዚህም ነው— በዚህ ፅሑፍ ላይ ርዕስ ላይ የጥልቅ ተሃድሶውን እንቅስቃሴ የህዳሴያችን ፍቱን መድሃኒት ያልኩት።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy