Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመሰረተ ልማት ግንባታ

0 1,173

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመሰረተ ልማት ግንባታ

ዘላቂ ለሆነ የፌደራላዊ ስርአት ግንባታ

ስሜነህ

በመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት የተዘረጋው ስርአት ዘመናዊ ኢኮኖሚ በተለይም ዘመናዊ የገበያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የሸቀጦች ዝውውርና የሰዎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሁኔታ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል። የአንድን ዘመናዊ የገበያ ኢኮኖሚ ቅልጥፍናና የውድድር ብቃት ከሚወስኑት ነገሮች አንዱ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ቅልጥፍናና ውጤታማነት ነው። ሸቀጦችንና ሰዎችን በፍጥነት በገፍና በዝቅተኛ ወጪ ለማዘዋወር የሚችል የትራንስፖርት አገልግሎት ያለው ኢኮኖሚ በገበያ በብቃት መወዳደር የሚችል ሲሆን ይህንን ማድረግ ያልቻለ ኢኮኖሚ ደግሞ መወዳደር የማይችል እንደሆነ የኢኮኖሚው ዘርፍ ልሂቃኖች ያሰምራሉ።  

በዚሁ አግባብ በ1994 የወጣው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጉዳዮች ፖሊሲ የአገራችንን ህዝቦች ብዝሃነት እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ጠንካራና የበለጸገ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ በመሰረተ ልማት ሁሉንም የአገራችንን አካባቢዎች ማስተሳሰር ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አስምሮበታል። በእነዚህና በሌሎችም የመንግስት ሰነዶች የትራንስፖርት ዘርፍ የአገሪቱ የኢኮኖሚ የደም ስር ተደርጎ በመወሰዱ በአገራችን ባለፉት አመታት ፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በአራቱም አቅጣጫ ተከናውኗል፤ እየተከናወነም ነው። በዚህም በተለያዩ የአገራችን ብሄሮችና ብሄረሰቦች መካከል መተዋወቅ፣ መግባባትና መቀራረብን ፈጥሯል። ከአገር ውስጥ ግንኙነት አልፎ ክፍለ-አህጉራዊና አህጉራዊ ትስስሮችን መፍጠር የሚያስችል መልካም እድልም ተፈጥሯል። በአጭር አመታት ውስጥ ግዙፍ የትራንስፖርት አውታር መሰረተ ልማት መገንባት በመቻሉ ባሳለፍነው አመት የተከሰተውን ከባድ የድርቅ አደጋ ከወደብ ደራሽ እህልና አልሚ ምግብ በሚሊዮን ቶን በማጓጓዝ ለወገኖቻችን በወቅቱ ደርሶ መታደግ ተችሏል።

አሁን ያለው ስርአተ መንግስት ዜጎቹን ከድህነት ወጥመድ ለማላቀቅ የሚያስችል የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የሚቻለው በቅድሚያ በመሰረተ-ልማቶች ዝርጋታ፤ በተለይም በትራንስፖርት መሰረተ-ልማቶች ግንባታ ትርጉም ያለው ስራ ሲሰራ ብቻ መሆኑን በማመን ላለፉት 26 ዓመታት ሰፊ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን ደረጃ በደረጃ እያቀደ ሲተገብር ቆይቷል፡፡  

ድህነትን ለማጥፋት የሚያስችል ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋትና ህዝቡን ተደራሽ ለማድረግ የመንገድ መሰረተ ልማት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በተጨማሪም ከተማውን ከምርት አካባቢዎች፣ የግብርና አካባቢዎችን ደግሞ ከገበያ ስፍራዎች ጋር በማገናኘት የአርሶ አደሩንም ሆነ የከተማ ነዋሪውን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንገድ ወሳኝ ነው፡፡ በአገራችን ህዝቦች መካከል መቀራረብ፣  ያላቸውን በህገ-መንግስታችን የተቀመጠውን ራዕያቸውን ለማሳካት እንዲችሉ የመንገድ መሰረተ ልማት መስፋፋት የማይተካ ሚና አለው፡፡ ይህን የተገነዘበው መንግስት  ትክክለኛ የመንገድ ልማት ፖሊሲ በመቅረፅና ተገቢውን በጀት በመመደብ ላለፉት 26 አመታት ተግባራዊ ያደረጋቸው የመንገድ ልማት ፕሮግራሞች ለተገኘው ውጤት ዋነኛው ምክንያት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በተለይ ከ1989 ዓ.ም እስከ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማብቂያ ድረስ አራት የመንገድ ልማት ፕሮግራሞች በመንግስት ተቀርፀው ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ አራት ፕሮግራሞችም ከ118ሺ 550 ኪ.ሜ በላይ የሚረዝሙ አዳዲስ የአስፋልት፣ የጠጠር፣ የገጠርና የወረዳ መንገዶች ግንባታና የመንገዶች ከባድ ጥገና ስራዎች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል። በዚህም በ1983 ማብቂያ ላይ የነበረውን 19ሺ 017 ኪ.ሜ መንገድን በ6 እጥፍ በማሳደግ የሀገራችንን አጠቃላይ የመንገዶች እርዝመት 110ሺ 414 ኪ.ሜ ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህም መንግስት አጠቃላይ ህዝቡን በማሳተፍ በ100 አመታት የተገነባውን መንገድ 6 እጥፍ በ26 አመታት ውስጥ ለመገንባት ችሏል፡፡

በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው በአስፋልት ደረጃ ከተገነቡት መንገዶች መካከልም ሀገራችንን ከጎረቤት ሀገራት ወደቦች ጋር የሚያገኛኙት መንገዶች ይገኙበታል። በዚህም ሀገራችንን ከሰሜን ሶማሌ ላንድ፣ ከሱዳንና ከጅቡቲ ጋር የሚያገኛኙ መንገዶች ግንባታቸው የተጠናቀቀ ሲሆን ከኬንያ ጋር የሚያገናሰኘን መንገድም ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪ አዲስ አበባን ከክልል ዋና ከተሞች እና ከሌሎች ትላልቅ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ነባር የጠጠር መንገዶች በአስፋልት ደረጃ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡

በተለይ በገጠር የሚኖረው ህዝብ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ውስጥ ተካቶ የተተገበረውን ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽ ፕሮግራም እቅድ ሲተገበር የገጠር ቀበሌዎችን ክረምት ከበጋ በሚያስኬድ መንገድ በአቅራቢያ ከሚገኝ መንገድ ጋር ማገናኘት ተችሏል። ይህ ፕሮግራም በዋናነት የገጠሩን ነዋሪ ጉልበት መሰረት በማድረግ በአነስተኛ ወጪና የግንባታ መሳሪያዎች ተከናውኖ በአጭር ግዜ ውስጥ ከፍተኛ ርዝመት ያለው መንገድ ለመገንባት ያስቻለ ፕሮግራም ነው፡፡  

በነዚህ 26 ዓመታት የተተገበሩት የመንገድ መሰረተ-ልማት ፕሮግራሞች ኢኮኖሚው በሁለት አሀዝ እንዲያድግ ያስቻሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለሀገራችን ህዝቦች በርካታ ጠቀሜታዎችን አስገኝተዋል፡፡ የጤናንና የትምህርት አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት በተለይም የጤና ኬላዎችንና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ቅርበት ለመገንባትና ተደራሽ ለማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የገጠሩ ነዋሪ ክረምት ከበጋ ከሚያስኬድ መንገድ ላይ ለመድረስ በአማካይ ይወስድበት የነበረውን ግዜ በ1984 ዓ.ም ከነበረበት ከ10.2 ሰዓት ወደ ወደ 1.3 ሰዓት ለማሳጠር መቻሉን ከባለስልጣኑ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንዲሁም አርሶ አደሩን የግብርና ግብአቶችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያስቻሉት ሲሆን ትርፍ የግብርና ምርቶቹንም በቀላሉ ለገበያ በማቅረብ በተወዳዳሪ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችለውታል፡፡

በሌላ በኩል የሃገራችን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሄዱን ተከትሎ በአንድ ግዜ በርካታ ጭነት ለማጓጓዝ የሚያስችል የትራንስፖርት አይነትን መጠቀም የግድ የሚል መሆኑ አያከራክርም። ይህን በአግባቡ የተገነዘበ የሚመስለው መንግስት ለሃገራችን አዲስ የሆነውን ዘመናዊ የባቡር ኔትዎርክ ለመገንባት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ በአምስት ኮሪደሮችና በሰባት መስመሮች በጠቅላላው የ2ሺ 741 ኪሎ ሜትር ሀገራዊ የባቡር ኔትወርክ ግንባታ ለማካሔድ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት አዲስ-አበባን ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኘው የባቡር ሀዲድ የኢትዮጵያ ክፍል የሆነው አዲስ አበባ/ሰበታ-መኢሶ-ደወሌ (656 ኪ.ሜ)የባቡር ሀዲድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ይታወቃል፡፡  

ከሀገራዊ የባቡር ኔትዎርክ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የህዝብ ትራንስፖርት እጥረትን በተወሰነ ደረጃ እንዲያቃልል ታስቦ በሁለት አቅጣጫዎች የተገነባው የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ ይህ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ለተጠቃሚዎች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለሃገራችን ዘመናዊ የከተማ ትራንስፖርትን ያስተዋወቀና ለከተማችንም የዘመናዊነት ገፅታ የሰጠ የመሰረተ-ልማት ዘርፍ ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት በዋና ዋና ከተሞች ዙሪያ ብቻ ታጥሮ በዓመት ከ10 አስከ 20 የማይበልጡ ከተሞች ላይ በማተኮር ሲሰራ  የቆየውን ኢፍትሃዊ የሃይል አቅርቦትና ስርጭት አስተዳደሩን ከመሰረቱ በመለወጥ በዓመት 1,ዐዐዐ የሚደርሱ ከተሞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማድረግ መቻሉ ሌላኛውና ስለፌደራላዊ ስርአቱ ግንባታ ሊጠቀስ የሚገባው የመሰረተ ልማት ዘርፍ ነው። በ2007 መጨረሻ ከ5ሺ 617 በላይ የገጠር ከተሞችና ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ሆነዋል። በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን መጨረሻ 1ዐ,ዐዐዐ ከተሞችንና የገጠር መንደሮችን በማገናኘት የኤሌክትሪክ ሽፋኑን በ1984 ከነበረበት10 በመቶ በአሁኑ ወቅት 90 ከመቶ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ ለመሆኑ ሀውሃ ከነፋስና ከጂኦተርማል ሃይል ለማመንጨት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶቻችን እማኝ ይሆናሉ፡፡

የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታም በተመሳሳይ ስለፌደራላዊ ስርአቱ ጽናት ሊጠቀስ ይገባዋል። የገጠር ልማት ስራውን በቴከኖሎጂ ከመምራት አኳያ የስኩል ኔትና ወረዳ ኔት አገልግሎቶች በሁሉም አካባቢዎች በመስፋፋታቸው በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች ለተመዘገበው ስኬት ዘርፉ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። የሰለጠነው አለም ቴክኖሎጂ የደረሰባቸውን የሽያጭ ማሽኖች፣ ፖስ፣ ሞባይል ባንኪንግና ሌሎችንም ዘመናዊ አገልግሎች በከተሞች የተዘረጋ ሲሆን በገጠር ከከተማው መሰረታዊ ልዩነት በሌለው መልኩ አገልግሎቱ ተደራሽ በመደረግ ላይ ይገኛል። ችሎቶች ስብሰባዎች በቴሌኮንፈረንስ መስጠት በመጀመራቸው የመንግስት አገልግሎትን በቅልጥፍናና በዝቅተኛ ወጪ ለህዝቡ ማቅረብ ተችሏል፤ በዚህም ህዝቡ የሚያነሳቸውን የአገልግሎት ፍጥነት መጓደል ቅሬታዎች ማርካት ተችሏል። አብዛኞቹ በአገራችን በየደረጃው የሚገኙ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት መረጃን በሰነድ ለሰልጣኝ ከማቅረብ በተጨማሪ እና በተለዋጭ መልኩ ኦንላይን አገልግሎቱን መስጠት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።  

በሌሎችም የመሰረተ ልማት ዘርፎች የመጠጥ ውሃ፣ የሃይል እና የመስኖ ልማት እንዲሁም የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች የአገራችን ህዝቦችን በፍትሃዊነት ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አመላካች ይሆናሉ። በጥቅሉ የአገራችንን ህዝቦች ብዝሃነት እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ጠንካራና የበለጸገ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ በመሰረተ ልማት ሁሉንም የአገራችንን አካባቢዎች ማስተሳሰር መቻሉ የፌደራላዊ ስርአቱን በማይናወጽ አለት ላይ መሰረት እንዲጥል አስችሎታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy