Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የምንዛሪ ማስተካከያውና የሃገሪቱ የወጪ ንግድ

0 343

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የምንዛሪ ማስተካከያውና የሃገሪቱ የወጪ ንግድ

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ሰሞኑን የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ እንዲቀንስ ወስኗል። የምንዛሪ ቅነሳ (devaluation) ቋሚና ከፊል ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ባለባቸው ሃገራት መንግስት ሆን ብሎ የሚያሳልፈው የሀገሩ ገንዘብ ከዋና ዋና የውጭ ገንዘቦች ጋር በንጽጽር ያለውን ዋጋ የመቀነስ ውሣኔ ነው። ኢትዮጵያ ከ1985 ዓ/ም በፊት ቋሚ የውጭ ምንዛሪ ተመን ነበራት። ከዚያ ወዲህ ደግሞ ከፊል ገበያን ተከትሎ የሚለዋወጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአትን የምትከተል ሃገር ነች።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የብር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ላይ ሶስት ግዜ ማስተካከያ አድርጋለች። ይህም በ1985 ዓ/ም መጀመሪያ ላይ 2 ብር 7 ሳንቲም ሆኖ በቋሚነት የተያዘውን የ 1 ዶላር  የብር ምንዛሪ ተመን በ140 በመቶ ያህል በመቀነስ 5 ብር እንዲሆን ተወስኖ ነበር። ከዚህ በኋላ በ2002 ዓ/ም 13 ብር ከ30 ሳንቲም የነበረውን የ1 ዶላር የምንዛሪ ተመን በ16 በመቶ ገደማ በመቀነስ 16 ብር ከ70 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኖ እንደነበረ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ 23 ብር ከ40 ሳንቲም የነበረውን የ 1 ዶላር የምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ በመቀነስ 26 ብር ከ90 ሳንቲም እንዲሆን ተደረጓል።

የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ማድረግ ያስፈለገው የብር ዋጋ ከውጭ ሃገራት ገንዘብ ጋር ሲወዳደር መሆን በማይገባው መጠን ውድ በመሆኑ ነው። ይህ ማለት፣ የኢትዮጵያን ምርት ወደውጭ የሚልክ ነጋዴ በውጭ ምንዛሪ – በዶላር የሚያገኘውን ገቢ ወደሃገር ቤት አስገብቶ በብር ሲመነዝረው፣ ወደውጭ የላከውን ምርት ሃገር ውስጥ ሸጦት ቢሆን ኖሮ ከሚያገኘው አንሶ ይገኛል ማለት ነው። ለምሳሌ የዶላር የምንዛሪ ተመን 23 ብር ሆኖ፣ ወደውጭ የሚላክ አንድ ኪሎ ቡና 4 ዶላር ያወጣል ብለን እንውሰድ። ይሄው ቡና በሃገር ውስጥ 100 ብር ይሸጣል ብለን እናስብ። ቡና ላኪ ነጋዴው በዚህ የምንዛሪ ተመን ቡናውን ወደውጭ ቢልከው በብር የሚያገኘው ገንዘብ 92 ብር ብቻ። ይህ በብር የተገኘ ገንዘብ ወደውጭ የላከውን ቡና ሃገር ውስጥ ሸጦት ቢሆን ኖሮ ከሚያገኘው 100 ብር በ8 ብር ያነሰ ነው። ይህ ሁኔታ ሲኖር  የብር ዋጋ ውድ ሆኗል ይባላል።

የብር ዋጋ ውድ በሆነበት ሁኔታ ላኪዎች ምርታቸውን ወደውጭ መላክ አይፈልጉም። ያንኑ ምርት ሃገር ውስጥ መሸጥን ይመርጣሉ። በሌላ በኩል ከውጭ ምርትን ማስገባት አትራፊ ይሆናል። ይህ ሁኔታ የሃገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲያሽቆለቁል፤ በሌላ በኩል ወደሃገር ውስጥ ማስገባት እንዲበረታታ በማድረግ የወጪና የገቢ ንግድን ሚዛን ያዛባል። ይሄኔ የውጭ የምንዛሪ ተመንን ማስተካከል የግድ ይሆናል።

አሁን የሚነሳው ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካካያ ማደረግ የግድ በሚል ሁኔታ የብር ዋጋ ውድ ሆኗል ወይ? የሚል ነው። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ይህን የሚያመለክቱ እውነታዎች ታይተዋል። ለምሳሌ ቡና ላኪዎች ለወጪ ንግድ የተዘጋጀውን ቡና ሃገር ውስጥ ሸጡት ተብሎ በህገወጥነት ሲከሰሱ በተደጋጋሚ ሰምተናል። ይህ ብቻ አይደለም። በለሚ የኢንደስትሪ ፓርክ የቆዳ ውጤቶችን – ጫማ ለውጭ ገበያ ለመላክ ዓላማ የተቋቋሙ አምራቾች፣  ምርታቸውን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ለሃገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው በተጨባጭ ታይቷል። አምራቾቹ ይህን ማድረግ የሚያስችላቸው ህጋዊ ስምምነት ስለሌላቸው፣ ሆን ብለው ምርታቸውን ከወጪ ንግድ ምርት የጥራት ደረጃ በታች በማደረግ ለሃገር ውስጥ ገበያ ሲያቀርቡ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ተባብሶ አብዛኛውን ምርታቸውን ሆን ብለው ከደረጃ በታች ወደማድረግ ሲሸጋገሩ፣ መንግስት ከደረጃ በታች የሆኑት ምርቶች ለሃገር ውስጥ ገበያ ከመቅረብ ይልቅ እንዲቃጠሉ የሚል የአሰራር ደንብ ማውጣቱ ይታወቃል። ይህ የሆነው የብር ዋጋ መሆን ከሚገባው በላይ ውድ ስለሆነ ነው። በህጋዊ መንገድ ወደውጭ መውጣት የሚገባቸው ሌሎች ምርቶችም፣ ለምሳሌ ወርቅ በኮንትሮባንድ ከሃገር የሚወጣበት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱም ይህንኑ ያመለክታል።

ይህ ሁኔታ በተለይ ከ2005 ዓ/ም ወዲህ ለታየው የወጪ ንግድ ማሽቆልቆልና የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ መቀነስ አንዱ ምክንያት መሆኑ ይታመንበታል። በመሆኑም የሃገሪቱን የወጪ ንግድ እንዲያሰራራ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያ ማድረግ ተገቢ ነው። በተከታታይ ለአምስት ዓመታት እያሽቆለቆለ የሄደውን የወጪ ንግድና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሽቆልቆል ለመከላከል የሚያስችል ብቸኛው እርምጃ እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት።

መንግስትም በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደቆየው፣ የወጪ ንግድ እንዲያሽቆለቁል ያደረጉት ምክንያቶች፤ ኢትዮጵያ የምትልካቸው የግብርና ምርቶቸ ዋጋ በውጭ ገበያ ላይ መቀነስ፣ ሃገሪቱ ወደውጭ የምትልካቸው ምርቶች በግብርና ላይ የተመሰረቱና ውስን መሆን፣ የግብርና ምርቶች ላይ ምንም እሴት ሳይጨምሩ መላክ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ኪራይ ሰብሳቢነትትም የወጪ ንግዱ እንዲያሽቆለቁል በማደረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

እነዚህ የወጪ ንግዱ ላይ ተጽእኖ ያሳደሩት ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ፣ የብር ምንዛሪ ተመን ላይ የሚደረግ ማስተካካያ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም። የምንዛሪ ማስተካከያው የብር ውድ መሆን ያሳደረውን ተጽእኖ ያህል ብቻ ነው የሚያግዘው። እናም የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ለሁሉም ማነቆዎች መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል። ይህ ካልተደረገ የምንዛሪ ቅነሳ ማስተካካያው ብቻ ለውጥ አያመጣም። የምንዛሪ ማስተካከያ ተደርጎ የወጪ ንግዱ መሆን በሚገባው ልክ ወይም ጉልህ በሆነ መጠን የማይሻሻል ከሆነ ጉዳቱ ሊያመዝን የሚችልበት እድል አለ። የጉዳቱ ምንጭ የብር የምንዛሪ ተመን ማስተካካያ በገንዘብ ግሽበት ወይም በዋጋ ንረት ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ነው።

የብር የውጭ ምንዛሪ ላይ የተደረገው የ15 በመቶ ማስተካከያ ሃገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ሸቀጦች ዋጋ በ15 በመቶ እንዲያሻቅብ ያደርጋል። የሃገሪቱ የውጪ ንግድ ሚዛን ወደገቢ ንግድ ስለሚያጋድል የዋጋ ጭማሪው አብዛኞቹ ገበያ ላይ የሚገኙ ምርቶች ላይ የሚያርፍ መሆኑም አይቀሬ ነው። በሃገር ውስጥ የሚመረቱትም የኢንደስትሪ ምርቶችም ቢሆኑ በከፊል ግብአታቸው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ፣ በሚጠቀሙት ግብአት  ልክ ዋጋቸው ማሻቀቡ አይቀርም። በተለይ የሃገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ ከውጭ በሚገባ ነዳጅ የሚሸፈን በመሆኑ ነዳጅ የሃገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ በሚጨምረው እሴት ልክ ዋጋው ያሻቅባል። ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ በሃገሪቱ ድንገተኛ እመርታዊ የዋጋ ንረት ሊያስከትል ይችላል።

እናም የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ፣ ከወጪ ንግድ የሚገኘውንም ገቢ ለማሻሻል የተወሰደው የምንዛሪ ማስተካከያ እርምጃ፣ የወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ካሳደሩ ምክንያቶች ለአንዱ ብቻ ማለትም ከብር ውድነት ለመነጨው ብቻ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ሁሉንም የወጪ ንግድ ተጽእኖዎች መቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። ይህ ሲሆን በቻ ነው የወጪ ንግዱ በሚፈለገው ልክ የሚያንሰራራው፣ የሃገሪቱን አጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት በማፋጠን የህዝቡን የመግዛት  አቅም መደገፍ የሚቻለው። አለበለዚያ የዋጋ ንረት ተጽእኖው ብቻ ነው የሚተርፈን።

ከዚህ በተጨማሪ የምንዛሪ ማስተካከያው ከሚስከትለውን የዋጋ ንረት መቆጣጠር የሚያስችሉ ስርአቶችን መዘርጋት ያስፈልጋል። የምንዛሪ ማስተካከያው የሚያስከትለው የዋጋ ንረት ተጽእኖ የሚያሳድረው ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ብቻ በመሆኑ መቋቋም የሚያስችላቸውን መላዎችን የማበጀት ጉዳይም ቢታሰብበት መልካም ነው።

በአጠቃላይ፤ የውጪ ንግዱ እንዲጎለብት ለማድረግ ከምንዛሪ ማስተካከያው ጋር ሌሎችም በወጪ ንግዱ ላይ ተጽእኖ ያሳደሩ ችግሮች መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል። አለበለዚያ የወጪ ንግዱን ላይ የሚገኘው መሻሻል የምንዛሪ ማስተካከያው ከሚያስከትለው የዋጋ ንረት ጫና ጋር አልመጣጣን ብሎ ጉዳቱ ብቻ ይተርፈናል። እርግጥ መንግስት ከምንዛሪ ተመን ማስተካከያ እርምጃ አስቀድሞ ሌሎቹን የወጪ ንግድ ተጽእኖዎችን ስለለየና በአግባቡ ስሰለተረዳ፣ እርምጃ ለመውሰድም ስለተዘጋጀ የሚፈለገው ውጤት ይገኛል የሚል ተስፋ አለን።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy