Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሥርአቱ መገለጫ ስኬቶች እንጂ ግጭቶች አይደሉም

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሥርአቱ መገለጫ ስኬቶች እንጂ ግጭቶች አይደሉም

ብ. ነጋሽ

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት ተግባራዊ በሆነባቸው ያለፉ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ገደማ ከዚያ ቀደም ለዘመናት ሲናፈቁ የኖሩ ውጤቶች ተገኝተዋል። በሃገሪቱ ለዘመናት የኖረው አሃዳዊ ሥርአት የሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው ያላቸውን መብቶችና ነጻነቶች – በቀንቋ የመንግስት አገልግሎት የማግኘት፣ በቋንቋ መማር፣ ባህልን ማሳደግ፣ ታሪክን መንከባከብና ማጥናት፣ በተወካዮች አማካኝነት መተዳደር ወዘተ ተነፍጎ ነበር። በተለይ በዘውዳዊ ሥርአት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በገዛ መሬቱ ላይ ሰርቶ የሚገብር፣ በራሱ ምርትና ጉልበት ላይ የማዘዝ መብት ያልነበረው ጪሰኛ እንዲሆን በመደረጉ አንድ ሰው ሊደኸይ የሚችለውን ያህል ደሃ ሆኖ እንዲኖር አድርጓል።

በህዝቦች ትግል ዘውዳዊው ሥርአት ከተወገደ በኋላ የህዝብን ሥልጣን የመነተፈው ወታደራዊ ደርግ፣ መሬት ለባለሃገሩ አርሶ አደር እንዲሰጥ ቢያደርግም የአርሶ አደሩ ኑሮ ግን በገባር ጭሰኝነት ከነበረበት ድህነት ፈቀቅ ማለት አልቻለም። ይህ የሆነው አርሶ አደሩ የመሬት ባለቤት እንዲሆን ቢደረግም በመሬቱ ላይ ሰርቶ ያገኘው ምርት ላይ የባለቤትነት መብት እንዳይኖረው በመደረጉ ነበር። ወታደራዊው ደርግ በከተማ ውስጥ ሊቀሰቀስበት የሚችለውን ተቃውሞ ለማፈን ለከተሜ ሸማቾች እህል በዝቅተኛ ዋጋ ያቀርብ ነበር። ገበያው ከሚፈቅደው በታች በዝቅተኛ ዋጋ ለከተሜዎች የሚቀርበው ምርት ከአርሶ አደሮች የሚሰበሰብ ነው። የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም፣ የመሬቱን ለምነት ሁኔታ፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ ወዘተ ከግምት ሳይገባ አርሶ አደሩ እጅግ በዝቅተኛ ዋጋ (ከማምረቻ ወጪ በታች) የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት ለተባለ መንግስታዊ ተቋም ለማቅረብ በአይነትና በመጠን ኮታ ይጣልበት ነበር።

በዚህ ሁኔታ አርሶ አደሩ የቤተሰቡን ፍጆታ እንኳን ማሟላት የሚያስችል ምርት አይተርፈውም ነበር። አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት በአይነትና በመጠን የተጣለበትን ኮታ ማሟላት ስለማይችል ከብቶቹን ሸጦ ከገበያ በውድ ዋጋ ገዝቶ ከስሮ ለእርሻ ሰብል ገበያ የሚያስረክብባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ ምርታማነቱን ማሳደግ የሚያስችል ምንም አይነት ድጋፍ አይደረግም ነበር። ይህ ሁኔታ አርሶ አደሩን የደሃ ደሃ አድርጎት ነበር።

በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ በአንድ በኩል ዜጎች – ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሊገሰሱ የማይገባቸውን በቋንቋቸው የመጠቀም፣ እውነተኛ ታሪካቸውን የማወቅና የመንከባከብ፣ በቋንቋ የመማር መብት ተነፍገው በሃገራቸው ባይተዋር ሲደረጉ በሌላ በኩል በመሬታቸውና በምርታቸው ላይ ያላቸውን የባለቤትነት መብት ተነፍገው በአሰከፊ ድህነት ውስጥ ለመኖር የተገደዱበት ነበር። ብሄራዊ ጭቆናውና ድህነቱን መሸከም ያቃታቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ የህይወት መስዋዕትነትነትን በጠየቀ መራራ ትግል ብሄራዊ መብትና ነጻነታቸውን ነፍጎ በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር እንዲሆኑ፣ በአስከፊ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደረጋቸውን አሃዳዊ ሥርአት ዳግም ላይመለስ አስወገዱት። ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በራሳቸው ፍቃድ በአንድነት የሚኖሩበትን ፌደራላዊ ሥርአት መስርትዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሁን በብሄራዊ ማንነታቸው ያሏቸው መብቶችና ነጻነቶች ተረጋግጠውላቸዋል። የሃገሪቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች በመሆናቸው በገዛ ሃገራቸው ባይተዋርነት አይሰማቸውም፤ አሁን በዜግነታቸው የሚኮሩ ባለሃገሮች ለመሆን በቅተዋል። ይህ ፌደራላዊ ሥርአቱ ካስገኛቸው ሁሉ የላቀው የሁሉም ስኬቶች መሰረት የሆነ ፖለቲካዊ ስኬት ነው።

ፌደራላዊ ሥርአትና ዴሞክራሲ የማይነጣጣሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የኢፌዴሪ ሥርአት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በወኪሎቻቻው አማካኝነት በክልላቸው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት፣ በፌደራል መንግስቱ ውስጥም የሚወከሉበትን እድል አስገኝቷል። በፌደራላዊ ሥርአቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተገዢዎች ሳይሆኑ የመንግስት ሥልጣን ምንጭና ባለቤቶች ናቸው። ሥልጣን በውክልና የመስጠትና የማንሳት መብት ባለቤቶች ናቸው። መንግስት የወኪሎቹን መብትና ነጻነት፣ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠብቅ በህዝብ ውክልና የተቀመጠ አካል ነው። በመሆኑም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በማቃለል የተሻለ ህይወት መኖር ወደሚችሉበት ደረጃ ማሸጋጋር የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ሆኗል።

የኢፌዴሪ መንግስትና ክልላዊ መንግስታት ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ለዘመናት በህዝቡ ላይ ተጭኖ የኖረውን ከባድና ስር የሰደደ የድህነት ሸክም ማቃለል ቀዳሚ አጀንዳቸው ያደረጉትም ለዚህ ነው። የኢፌዴሪ መንግስት የሃገሪቱና የህዝቡ ጠላትና አደጋ ድህነት ብቻ ነው የሚል አቋም ይዟል። በዚህ መነሻነት በተደረገው ርብርብ ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ እድገት የህዝቡን ኑሮ ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋጋር ባስቻለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተገልጿል።

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰው ሃይል የተሰማራበት ግብርና በሃገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ግብርና የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው። ይህ ምሰሶ ግን በገጠር የሚኖረውን አርሶ አደር እንኳን በወጉ መኖር በማያስችል ሁኔታ ደካማ ነበር። እናም በገጠር በአርሶ አደርነት የሚኖረውንና ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሃገሪቱን ህዝብ ከድህነት ለማውጣትና አጠቃላይ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚገኘበት አዘቅት ለመሳብ ገጠር፣ ግብርና እና አርሶ አደር ላይ ማተኮር የግድ ነበር። አብዛኛውን የሃገሪቱን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግና የካፒታል ክምችት በመፍጠር የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ሽቅብ መሳብና ትራንስፎርም ማድረግ የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ይህ ብቻ ነበር።

በዚህ መሰረት፣ መንግስት ግብርና መር የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲና ፖሊሲውን ማስፈጸሚያ እቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ጀመረ። በሃብት እጥረት ተሸብቦ በድህነት ቀለበት አዙሪት ውስጥ ለመኖር ተገዶ የነበረው አርሶ አደር ምርታማነቱን ማሳደግ የሚያስችለው ግብአት በብድር የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻቸ። ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ አዲስ ከተዋወቀው ምርታማነትን የሚያሳድግ ግብአት አጠቃቀም ጋር የሚያስተዋውቁና የተሻለ የእርሻ ስልትን የሚያሰለጥኑ የግብርና ልማት ባለሞያዎች በአረሶ አደሩ መንደር ተሰማሩ። በዚህ ሁኔታ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ማደግ ጀመረ። ከዚህ ጋር የአርሶ አደሩም ገቢ ማደግ፣ ኑሮውም በሚያድገው ገቢው ልክ መሻሻል ጀመረ።

አሁን በብዙ ሚሊየን ብር የሚለካ ሃብት ያፈሩ አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል። የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ ካሚዮን ያላቸው፣ በከተማ የሚከራይ ቤት የሰሩ፣ ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት ያላቸው፣ ለእግራቸው የቤት መኪናና ሞተር ሳይክል ያላቸው አርሶ አደሮች ቁጥር ቀላል አይደለም። አሁን አብዛኛው አርሶ አደር የከብት በረቱንና የጢስ ቤቱን ከመኖሪያ ቤቱ ለይቷል። በጸሃይ ሃይል የሚሰራ ኤሌትሪክ ተጠቃሚዎች ቁጥርም በርካታ ነው። አሁን በአንድ አርሶ አደር ቤት ቢያንስ አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ አለ። ሬዲዮና ቴሌቪዥን ያላቸውም በርካቶች ናቸው። የተሟላ የስራ፣ የክትና የሌሊት ልብስ የሌለው አርሶ አደር ማግኘት አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ምንም ያልነበራቸው አሁን በብዙ ሚሊየን ብር የሚለካ ሃብት አፍርተው ወደ ኢንቨስተርነት የተሸጋገሩም አሉ።

አሁን ሁሉም የአርሶ አደር ልጆች በአቅራቢያቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እድል አግኝተዋል። ሁሉም የወረዳ ከተሞች የሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች አሏቸው። በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ በክልል መንግስታት የሚተዳደሩ 1 ሺህ 3 መቶ ገደማ የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠናኛ ኮሌጆች አሉ። የጤና አገልግሎት ተቋማት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆን በሚችሉበት ርቀት ላይ ተቋቁመዋል። የገጠር መንገድ መሰረተ ልማትም በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢዎች ተዳርሷል። በማህበራዊ ልማትና በመሰረተ ልማት መስፋፋት ረገድ አሁንም የሚቀር መሆኑ ባይካድም፣ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ብቻ ቀደም ሲል ከነበረው በብዙ እጥፍ እድገት ታይቷል።

እንግዲህ እነዚህ ከላይ ለማሳያነት ያህል የተገለጹት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶች የፌደራላዊ ሥርአቱ ውጤቶች ናቸው። እነዚህን ስኬቶች ሆን ብሎ ለመካድ ለሚፈልግ ካልሆነ በስተቀር፣ በግልጽ የሚታዩና ገለልተኛ ተቋማትም ምስክርነታቸውን የሰጡበት ነው። እነዚህን ገሃድ የፌደራላዊ ሥርአቶች ስኬቶች መቀበል የሚከብዳቸው ቡድኖች በሌላ በኩል ጥቃቅን ችግሮችን፣ ለምሳሌ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ያለአግባብ በማጋነን የፌደራላዊ ሥርአቱ ችግሮች አድርገው ለመቅረብ ሲሞክሩ ይታያሉ።

እርግጥ ነው፤ በየወቅቱ ከማንነት፣ ከአስተዳደር አከላላል፣ ከድንበርና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች፣ አልፎ አልፎም ግጭቶች አጋጥመዋል። እነዚህ ችግሮች ግን በማንኛውም ፌደራላዊ ሥርአት በሚከተል ሃገር የሚያጋጥሙ፣ አብዛኞቹ መብትና ነጻነቶች በህገመንግስት ከመረጋጋጣቸው የመነጩ ናቸው። በአሃዳዊ ሥርአቶች ዘመን ዜጎች በይፋ የማንነት ጥያቄ ሊያነሱ አይችሉም። በየትኛው አስተዳደር መካለል እንዳለባቸው የመምረጥም መብት የላቸውም። በመሆኑም ጥያቄዎቹን በይፋ ሊያነሱና አለመገባበቶች ሊፈጠሩ አይችሉም። የማምነታቸው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ የሚያስችላቸው ብቸኛ አማራጭ የነጻነት የትጥቅ ትግል ማካሄድ ብቻ ነበር። ይህ በሃገራችን በተጨባጭ ታይቷል። ቅድመ 1983 ዓ/ም የእርስ በርስ ጦርነት የሃገሪቱ ገጽታ ለመሆን በቅቶ እንደነበረ ልብ ይሏል።

በአጠቃላይ ፌደራላዊ ስርአቱ በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ ያልነበሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ አስችሏል። ችግሮች ቢፈጠሩም መቆጣጣሪያ ወደሌለው ግጭት ሳይቀየሩ መፍታት የሚያስችል ህገመንግስታዊ መንገድ አለ። በመሆኑም የፌደራላዊ ስርአቱ መገለጫዎች ስኬቶች ናቸው እንጂ ግጭቶች አይደሉም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy