Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቆመም ፕሮጀክት ይሁን የሚበተን ሰራተኛ የለንም!

0 469

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቆመም ፕሮጀክት ይሁን የሚበተን ሰራተኛ የለንም!

ዳዊት ምትኩ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ጽንፈኞች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው እንደቆመ በማስመሰል ውዥንብር ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። ይሁን እንጂ ግንባታው እንዳልቆመና ስራውም በምዕራፎች ተከፈፋፍሎ እየተካሄደ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ በማንኛውም ፕሮጀክት ውስጥ አንደኛውን ምዕራፍ ስራቸውን ያጠናቀቁ ባለሙያዎች ከፕሮጀክቱ ለቀው መሄዳቸው የተለመደ አሰራር ነው። አገራችን በርካታ ፕሮጀክቶችን የምትገነባ አገር እንደመሆኗ መጠን ወደ ባለሙያዎች ወደ ሌላኛው ፕሮጀክት ይዛወራሉ እንጂ ልምድ ያዳበሩ ባለሙያዎችን የምትበትን ምንም ዓይነት ምክንያት የላትም።

እንደ እውነቱ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ግድቡ ለ24 ሰዓት ግንባታው እየተካሄደ ነው። አሁን ያለበት ደረጃም 60 በመቶ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ግድብ በህዝባችን አንጠራ ሃብት የሚገነባ በመሆኑ የሚቆምበት ምክንያት የለም።

እርግጥም ‘ግድቡ ግንባታው ቆሟል’ የሚለው ዲስኩር ነጭ ውሸት ነው። እንደሚታወቀው የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ለዘመናት በውሃው የመጠቀም መብቱ ተነፍጎ የቆየው መላው የሀገራችን ህዝብ በገንዘቡም ይሁን በጉልበቱ እንዲሁም ቦንድ በመግዛት የግድቡ ስራን ከዳር ለማድረስ ቃል የገባው በማንም ጎትጓችነት አይደለም። በራሱ ፍላጎት የሀገሩን ልማት አሳድጎ እርሱም ተጠቃሚ ለመሆን እንጂ።

እናም ግድቡ አሁን ከሚገኝበት 60 በመቶ ግንባታ ላይ እንዲደርሰና ፍፃሜውም ዕውን እንዲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በስራ ላይ ይገኛሉ። ይህን ስራቸውን ለ24 ሰዓት እያከናወኑ ነው። የተቋረጠም ይሁን የሚቋረጥ ነገር የለም።

እርግጥም ገና ከጅምሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲወጠንና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ ላይ ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋይ ሲያኖሩ፤ “መሐንዲሱም እኛው፣ ግንበኛውም እኛው፣ የገንዘብ ምንጩም እኛው፣..የራሳችን ታሪካዊ አሻራ የሚያርፍበት ፊርማችን ነው።…” በማለት የተናገሩት እንዲሁ አይደለም። የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው የተፈጥሮ ሃብት በመልማት ለዘመናት አንገታቸውን ሲያስደፋ የነበረውን ድህነትን ለመቅረፍ ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ስለሚገነዘቡ ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ለፓርላማ እንደተናገሩት፤ ግብፆች የህዳሴውን ግድብ ለማስቆም ሶስት መንገዶችን በአማራጭነት ሊጠቀሙ ይሞክራሉ።

አንደኛው ሀገራችን ለግንባታው የሚሆን ገንዘብ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ  ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ ተፅዕኖ ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው በወታደራዊ ጥቃት ለማስፈራራት መሞከር ነው። ሶስተኛው ደግሞ የውስጥ ተጋላጭነታችንን ተጠቅመው የሀገራችንን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ሃይሎች በነጭ ለባሽነት በመጠቀም የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል መሞከር ነው።

እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመጽዎችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ – ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የይቻላል መርህን በተግባር ማዋል ያስቻለ ብሎም ከራስ አልፎ በሚደረገው ሽያጭ የህዝቡን ውለታ በዕድገት የሚመልስ በመሆኑ ታሪካዊነቱን የጎላ ያደርገዋል፡፡ ግና የምናድገው ለብቻችን አይደለም።

እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ መኖርን፣ ማደግንና መበልጸግን ከማንም በላይ የምንቀበልና የማንነታችን መገለጫም ነው። ልክ እንደ ሌሎች “ለብቻችን” ብለን አናውቅም። እናም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታችን ትኩረትም ማንንም ለመጉዳት ያለመ እንዳልሆነ ማንኛውም አካል ሊያውቅ ይገባል፡፡ አብሮ መብላትና ተያይዞ ማደግ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት መለያ ባህሪ እንደሆነም ጭምር፡፡

ሀገራችን በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊው የእኩልነትና የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ላደረገው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊነት በግምባር ቀደምትነት የተሰለፈችውም ለዚሁ ነው፡፡ መላው ዜጎቿም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እያበረከቱ የሚገኙት ደግሞ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡

ግድቡ ለእኛ የላቀ ፋይዳ ስላለው ትናንት የነበረው አቋማችን ዛሬም ሊንጋደድ አይችልም። አቋማችን የትናንቱ ነው። ግድቡ ሀገራችን የተያያዘችውን የፀረ- ድህነት ትግል ከግብ በማድረስ ለህዳሴው ጉዞ ስኬት የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አያጠያይቅም፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌትሪክ ሽፋን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፤ ለዘመናት መብራት ለራቀው የገጠሩ ህዝባችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ እናም ከዚህ በመነሳት ግድቡ ተቋረጠ የሚለው ሟርት መሰረተ ቢስ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡

እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም— በድህነት አለንጋ መገረፉ ማብቃት እንዳለበት በማመናቸው እንጂ፡፡

ለስኬታማነቱ ህዝባዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ሲነሱም የማንንም ጉትጎታ ያለመሻታቸው ለድህነት ካላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የመነጨ መሆኑም ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ እናም ይህ አቋማችን መቼም አይቀየርም። አይለወጥም። የትናንቱም ሆነ የዛሬው ብሎም የነገም አቋማችን አንድ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ ዋነኛ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ትውልድ ደግሞ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚያምን ነው። የትውልዱ ይህ አስተሳሰብ በመንግስታችን ፖሊሲም ላይ ዕውን እየሆነ ነው። የየትኛውንም ወገን ጥቅም ሳንነካ በጋራ ተጠቃሚነት ብሎት ሁሉም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበትን መንገድ የሚከተል ነው። እናም ትውልዳችን ይህን ፍትሐዊና ትክክለኛ አቋሙን የሚቀይርበት አንዳችም ዓይነት ምክንያት የለም።

ይህ አቋምም ሀገራችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንድታምንና የምታካሂዳቸውን ማናቸውንም ፕሮጀክቶች ከዚህ አኳያ እንድትቃኛቸው አድርጓል። ስለሆነም በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ይህን ዕውነታ መሰረት አድርጎ የሚከናወን በመሆኑ፤ ይህ የሀገራችን አቋም መቼም ቢሆን የሚቀየር አይሆንም። ይህን አቋም ያየዘች አገር ደግሞ የህዝቦቿን የማደግ ፍላጎት ለማስቆም እንደ ህዳሴው ግድብ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ታቆማለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy