Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቡድን አሰራር የነገሰበት

0 362

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

… የቡድን አሰራር የነገሰበት

ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

ሰሞኑን የምሰማው  አንዳንድ ነገሮች እንግዳ ሆነውብኛል። አንጋፋና ጉምቱ የድርጅት መስራቾች  ሃላፊነታችንን አንፈልግም አሉ፣ እከሌም በቀጣይ ከድርጅት ወይም ከመንግስት የስራ ሃላፊነት ሊሰናበቱ ነው ወዘተ የሚሉ  ነገሮች ከተለያዩ ሚዲያዎች  በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች እያደመጥን  ነው። ኢህአዴግ የስድስት ሚሊዮን አባላትን ያቀፈ ድርጅት ነው። ከዚያም ባሻገር ኢህአዴግ የ94 ሚሊዮን ህዝቦችን መንግስት  የሚመራ ግዙፍ፣ ጠንካራና ውጤታማ  ፓርቲ ነው።   

 

ኢህአዴግ ጠንካራ ውስጠ ዴሞክራሲያዊ አሰራር የነገሰበት፣ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፣ የቡድን አሰራር የሚከተል፣ ጠንካራ የግምገማ ስርዓት ያለው ፓርቲ ነው።   በድርጅቱ አሰራር   አባላት ወደውና ፈቅደው  ወደ ድርጅት  የሚቀላቀሉበት   እንዲሁም  በፈቀዱና  በመረጡት  ወቅት ድርጅቱን  የሚሰናበቱበት መብትን የተጎናጸፉበት  አሰራር የነገሰበት ነው።  እስካሁን የድርጅቱ መስራቾችን ጨምሮ  በርካታ  አባላት  በማንኛውም ወቅት በፍቃደኝነት አሊያም በግድ  ከድርጅቱ ሲሰናበቱ ተመልክተናል።  

 

ታላቁ መሪ በኢህአዴግ ምስረታና የስኬት ጉዞዎች  ፓርቲው በምርጫ አሸናፊ ሆኖ መንግስት እስኪመሰርት የአንበሳውን ድርሻ እንዳበረከቱ እንኳን የፓርቲው አባላት ይቅርና  ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚስማማበት ጉዳይ ነው። ኢህአዴግን የመሰረቱት  ቡድኖችና ግለሰቦች  ፓርቲው  በግለሰቦች ጥንካሬ ላይ እንዳይንጠላጠል አድርገውታል።  በወቅቱ የነበሩ የፓርቲው መስራቾች  የድርጅቱን  ቀጣይነት ለማረጋገጥ  ሲሉ  በድርጅቱ ውስጥ  የቡድን አሰራር እንዲነግስ  አድርገዋል።   ይህ አሰራር በመዘርጋገቱም  ፓርቲው ውስጥ የግለሰቦች መሄድና መምጣት  ሳቢያ እንቅፋት አልትከሰተም። ይልቁንም ድርጅቱ የቡድን አሰራሩን በማጠናከር  የስኬት ጉዞውን  ተያይዞታል።

 

እስካሁን  ባለው  ሁኔታ እንኳን  በርካታ ትላልቅ አመራሮች ፓርቲውን በተለያየ ምክንያት ለቀዋል። ለአብነት ያህል በ1994 ዓ.ም በርካታ የድርጅቱ  መስራቾች  ፓርቲውን ተሰናብተዋል። ይሁንና ኢህአዴግ  በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ፓርቲ ባለመሆኑ ድርጅቱም ሆነ  አገራችን  በስኬት ላይ ስኬት  መረማመድ  የጀመረችው  በዚያን ወቅት ነበር። በኢህአዴግ  ግለሰቦች  የማይተኩ አይደሉም። ፓርቲው በርካታ ውጤታማ ሰዎች ያሰባሰበ ድርጅት ነው።   

 

ኢህአዴግን በመመስረትም ሆነ የአገራችንን  የለውጥ ጎዳና  በመተለም ረገድ  የታላቁ መሪ አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው። ለአብነት  አገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በመከተል ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ  አበርክተዋል፤ የፌዴራላዊ ስርዓት እንድትከተል  በማድረግ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንድያጎለብቱ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ  አበርክተዋል። በርካታ ውጤታማ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍና ለተግባራዊነታቸውም በመታገል አገራችን ስኬቶችን እንድታስመዘግብ አድርገዋል።

 

እኚህ ታላቅ ሰው  የአገሪቱ  ህዳሴ ፈር ቀዳጅ  ነበሩ።   በድህነትና ጦርነት ትታወቅ የነበረችን አገር በዓለም ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት የምታስመዘግብ አገር እንድትሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ  አበርክተዋል። በስንዴ ልመና  ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ በአገር ደረጃ  በምግብ ሰብል ራሷን እንድትችል እንዲሁም ከፍተኛ ድርቅን  በመቋቋም ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት  እንድታስመዘግብ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ  አበርክተዋል። አገራችን በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ  የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ  መድርኮች ተሰሚነት እንዲኖራት  ትልቅ  ሚና ነበራቸው። አገራችን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀያሽና አራማጅ  እንድትሆን  የበኩላቸውን አስተዋጽዖ  አበርክተዋል።   

 

ይህን ሁሉ  በርካታ  አስተዋጽዖ  ያበረከቱ ታላቅ ሰው  ሲለዩ እንኳን  ድርጅቱ  በስኬት ላይ  በመረማመድ ላይ ነው።  የእሳቸውን ህልፈት ተከትሎ  በርካታ አስተያየት ሰጪዎች  ፓርቲው አበቃለት ሊፈርስ ነው  የሚሉ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ነበር። ይሁንና  እኚህ  ታላቅ  መሪ  ከተሰው ብኋላም  ፓርቲው  የነበረውን ጥንካሬ በማስቀጠል የአገሪቱን  የባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ችሏል።  

 

ታላቁ መሪ ለአገራችን ስኬቶች የአንበሳውን ድርሻ እንዳበረከቱ ሁሉ ድርጅታቸውም  ውስጠ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንዲሁም የፓርቲው አሰራር  በግለሰቦች ጥንካሬ ላይ  እንዳይንጠላጠል ትልቅ አስተዋጽዖ ተጫውተዋል። በመሆኑም በፓርቲው  ውስጥ  የቡድን አሰራር  እንዲነግስ በመደረጉ ፓርቲው በግለሰቦች መሄድና መምጣት ሳቢያ ችግር ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ የለም።  የግለሰቦች መሄድና መምጣት በፓርቲው መሰረታዊ ህይወት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ አያስከትልም ለማለት ነው እንጂ ግለሰቦች  በፓርቲ ውስጥ ምንም አስተዋጽዖ የላቸውም ለማለት እንዳልሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል።  በኢህአዴግ ቤት የቡድን አሰራር ልምድ የዳበረበት፣ እያንዳንዱ ውሳኔ ተመክሮ ተዘከሮ፣ በሃሳብ  ልዕልና  የሚወሰንበት   በመሆኑ የጥቂት ግለሰቦች መሄድ ፓርቲውን ለአደጋ የሚያጋልጠው    አይደለም።    

 

ታላቁ  መሪ አቶ መለስ ዜናዊ  ድርጅታቸውን  በተመለከተ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ እንዳሉት  በኢህአዴግ  ውስጥ የግለሰቦች አስተዋፅዖ የማይናቅ  ቢሆንም ለድርጅቱ  ስኬት ትልቅ ሚና  ያበረከተው  የቡድን ጥንካሬ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። በኢህአዴግ ውስጥ  ግለሰቦች የድርጅቱ ውጤቶች እንጂ ኢህአዴግ የግለሰቦች ውጤት አይደለም። እኔም ብሆን  ይላሉ ታላቁ መሪ የኢህአዴግ ውጤት ነኝ  ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።  ከዚህ መረዳት የሚቻለው  ለኢህአዴግ ጥንካሬ ትልቁ ነገር በድርጅቱ ውስጥ ያለው የቡድን አንድነትና ጥንካሬ እንጂ   በግለሰቦች  ላይ የተንጠለጠለ አይደለም።  

 

ኢህአዴግ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ፓርቲ እንዳልሆነ  ጽንፈኛው  አካልም ቢሆኑ የሚክደው እውነታ አይደለም። ጽንፈኛው ሃይል  ትላንት  ሲሰድባቸው ሲያንጓጥጣቸው  የነበሩ  የኢህአዴግ አባላት  አሁን ላይ እነዚህ አካላት  ስንብት  ጠየቁ  ሲባል ደግሞ ግለሰቦችን ስብዕና በማግገዘፍ   ኢህአዴግ አበቃለት  ሊፈርስ ነው ለማለት ሲዳዳቸው ተመልክተናል።   ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  በኢህአዴግ አሰራር ውስጥ የግለሰቦች   መሄድና መምጣት  ምንም ተጽዕኖ  የለውም  ባይባልም፤ የግለሰቦች መሰናበት  የድርጅቱን  ህልውና ሊፈታተን የሚችል ግን አይደለም። እንደእኔ  እንደኔ በግለሰብ ደረጃ   ለኢህአዴግ እንደታላቁ መሪ  አቶ መለስ ዜናዊ ያለ የገዘፈ ስብዕና  ያለው  ሰው ያለ አይመስለኝም። እሳቸው እንኳን  አልፈው  ኢህአዴግ  በስኬት ጎዳና  በመጓዝ  ላይ ነው። አሁንም ኢህአዴግ የስኬት ጎዳናውን ይቀጥልበታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy