Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተቃውሞ ሰልፉ ስለምን?

0 441

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተቃውሞ ሰልፉ ስለምን?

                                                                                          ይልቃል ፍርዱ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊያ ወሰን አካባቢ የተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋትና የሕዝቦችን በብዛት መፈናቀል ተከትሎ ውጥረቱን በማርገብ ሰላማዊ እልባት ለማስገኘት በመንግስትና በክልሎቹ በኩል ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች መነሻቸው ምንድነው፤ በማን ይመራሉ፤ አስተባባሪዎቹስ እነማን ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች በብዛት በሕዝቡ ውሰጥ እየተነሱ ባሉበት በአሁኑ ሰአት “ቄሮ ቢሊሱማ” የሚባል የወጣቶች ድርጅት በድረገጹ ንቅናቄውን የምመራው እኔ ነኝ ሲል አስታውቆ ኃላፊነቱን ወስዶአል፡፡

ሁከቱና ብጥብጡ አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ በሚገኝበት ሁኔታ ውስጥ ለምን ይህ ሆነ፤ መነሻ ምክንያቱሰ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ መፍትሔም ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ማበጀት ተገቢ ነው፡፡ የመፍትሔው የመጀመሪያው ደረጃ ሰፊ  የውይይት መድረኮችን በተለያዩ ደረጃዎች በስፋት ማዘጋጀት ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በአለፈው አመታት ከተነሳው ሁከትና ብጥብጥ አንፃር ሁኔታውን ወደ ሰላም የመለሰው የሕዝቡ ከፍተኛና ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው፡፡ አሁን መፍትሄው የሚገኘው ከሕዝቡ ጋር በመምከር ነው፡፡

አዲስ የተተካው ወጣት ትውልድ በእድሜው ገና ለጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስሜታዊነት ከመነሳት ባሻገር የጠለቀ ሀገራዊ ግንዛቤ ያለው አይደለም፡፡ ይህም በቀላሉ በማንኛውም የአክራሪ ፖለቲከኞች ተራ ቅስቀሳ በስሜት ተሞልቶ እንዲነሳ፣ እንዲጠለፍና ለጥፋት እንዲሰማራ ያደርገዋል፡፡ ይህን ሁኔታ መቆጣጠር ከመንግስት የሚጠበቅ ቢሆንም የሕዝቡ ድጋፍና ትብብርም ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡

ይህ ለሀገርም ለሕዝብም የማይበጅ ሀገርን የማፍረስና ሰላምዋን የማናጋት ተግባር አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት፤ ከጥፋት በስተቀር ምንም አይነት ትርፍ የሌለው ነው፡፡ ሀገርን በማውደም ሀገርን ማልማት ከቶውንም አይቻልም፡፡ አትዮጵያን ወደከፋ ሁከትና እልቂት ውስጥ ለመክተት ሲክለፈለፉ የነበሩ በሀገር ውስጥና በውጭም የሚገኙ መሰሪና ጸረ ሕዝብ ኃይሎች በዚህ በተፈጠረው ትርምስ የሀገርን ሰላም ለማናጋት በሚያደርጉት ሩጫ ተሳክቶልናል ብለው አስበው ከሆነ በእጅጉ ተሳስተዋል፡፡ ሕልማቸው መቸም እውን አይሆንም፡፡ ሕዝብ ሀገሩን ከጥፋት ይጠብቃል፡፡

በየግዜው እሳት የሚጭሩ፣ ባሕር ማዶ ሆነው ሕዝቡን ሰላም ለማሳጣት በሕዝብ ልጅ ደምና ሞት ጀግና ሁነው ለመታየት የሚጥሩ ከንቱዎች በሀገር ጥፋት የሚጨፍሩ፣ ለሀገር ተቆርቋሪ፣ አሳቢና ተጨናቂ ከእኛ በላይ የለም በሚል የሚመጻደቁ ሁሉ አንድ አፍታ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡

ሀገሪቱን ወደጥፋት ማእበል በመክተት የእልቂት አውድማ እንደትሆን ለማድረግ በግብጽና በሻእቢያ ቅጠረኝነት ተገዝተው ዶላር ተንተርሰው እየተኙ ሰርቶና ደክሞ ልጁን ባሳደገው ሕዝብ የሚቀልዱ ዋልጌዎች ቀንና ግዜ ፍርድ እንደሚሰጣቸው ግልጽ ነው፡፡ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በሰላማዊ መንገድ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ቆመው ጥፋትን መከላከል ይገባቸዋል፡፡

ዋሽንግተንና ኒውዮርክ ተቀምጦ ማክላላት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭትን ለመለኮስ መራወጥ ፌስቡክንና ማሕበራዊ ድረገፆችን በመጠቀም የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆሰቆስ መቀስቀስ ኃላፊነት የጎደላቸው፣ ስለሀገርና ስለሕዝብ አብሮነት ደንታ የሌላቸው፣ ነገን አሻግረው ለማየት ያልቻሉ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚፈጥሩት መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ በጥላቻ ፖለቲካ ሀገርን ማልማትም ሆነ ማሳደግ አይቻልም፡፡

በሀገር ቤት ላለው ጉዳይ ባለቤቱና ወሳኙ ራሱ ሕዝብ እንጂ የውጭ ተዋናዮች አይደሉም፡፡ ያገባናል ካሉም ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ለሰላምና ለእድገትዋ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው ኢትዮጵያዊነት፤ በሀገርና በሕዝብ ቁስል መነገድ፤ መሳለቅ አይደለም፡፡

ቀለባቸው ከግብጽ መንግስትና ከኤርትራ እየተሰፈረላቸው ለኢትዮጵያ እናስባለን የሚሉ ዋልጌዎች በድርጊታቸው ሊያፍሩ ይገባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ “አሜሪካ መሽጎ ማቅራራት ምን የሚሉት ወግ ነው? አርፋችሁ ሆዳችሁን እየሞላችሁና እያገሳችሁ እዛው ኑሩ፤ ኢትዮጵያን ሰላሟን አትንሱአት፡፡ ሀገር ትጥፋ መአት ይውረድ ትተራመስ የፈለገው መአት ይውረድ የሚል አስተሳሰብ የደከመና የዘቀጠ ነው፡፡” እያላችሁ ነው።

የፈረደባት አሜሪካ ለብዙ የሀገራችን ልጆች ንጹሀን ዜጎች እንጀራ ያወጣች ትልቅ ደረጃም እንዲደርሱ ምክንያት የሆነች ሀገር ብትሆንም የዛኑም ያህል ከሀገርና ከሕዝብ ሰርቆ አጭበርብሮ በስደት ስም ባሕር ማዶ የተሻገረ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌቦች፣ ማጅራት መቺዎችና ካዝና ሰባሪዎች በአሜሪካ መሽገው ድንገቴ ፖለቲከኛ በመሆን በሌሉበት በማያውቁት ጉዳይ ሲቀባጥሩና ሲለፈልፉ ውለው የሚያድሩባት ሀገር ነች፡፡ ስራ ፈቶች፣ የተቃውሞ ፖለቲካን ማደሪያቸው አድርገው የሚያቀረሹባት ሀገር ብትኖር እችው አሜሪካ ነች፡፡

በቀደም እለት አንዱ ከስኳር ፋብሪካ በሚሊዮን ብር ዘርፎ አሜሪካ የገባ ስም አይጠሩ ጋዜጠኛ ከስልጣን ለመሰናበት ጥያቄ ባቀረቡ ባለስልጣኖች ዙሪያ ተጠይቆ ሲዘባርቅና የቆጥ የባጡን ሲቀባጥር አየነው፡፡ ትንሽ ሀፍረት ብሎ ነገር አይነበብበትም፡፡ ይለዋል – ዝም ብሎ እንደአቡጄዲ ጣቃ ይቀደዳል፡፡ አይ አለማፈር አለ የሀገሬ ሰው፡፡ በሌብነት ዘርፎ አሜሪካ የገባው ወራዳ ሌባ ሌላን ሰው ሌባ ብሎ ሲወነጅል ማየት ከዚህ በላይ የተቃውሞ ፖለቲካው ሞቶ ስለመቀበሩ፤ ስለአገር የሚያስብ ሰው ስለመጥፋቱ ምን ምን ማረጋገጫ ይገኛል?

ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእራሱ የሚበጀውን ያውቃል፡፡ በአሜሪካ ከትመው የሚጮሁ የግብጽ ቅጥረኞች ለኢትዮጵያ እንደማይበጁዋት ያውቃል፡፡ እስከግዜው ዶላራችሁን እየመነዘራችሁ ብሉ፤ ጠጡ፤ ጨፍሩ፡፡፡ ከጠላት ያበረ ልጅ መቸም ልጅ መሆን አይችልምና በማርሻል ሲሲ ወይንም በኢሳያስ ስም እየማላችሁ ለሆዳችሁ ስትሉ መኖር መብታችሁ ነው፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያን አታውቁአትም፡፡ እሷም አታውቃችሁም፡፡

እዚሀ ላይ ልታውቁት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ለሀገሪቱ ጥፋትና ውድመት ትልቁ ድርሻ የእናንት መሆኑን ነው፡፡ የስድብ፣ የሀሜት፣ የአሉባልታ ፋብሪካዎች፣ የከፋውና የከረፋው የስም ማጥፋት ዘመቻ ባለቤቶች ናችሁ፡፡ ሕዝብን ከህዝብ በማናከስና በማባላት የሀገር ችግር አይፈታም፡፡ የሀገር ችግር በወሬና አሉባልታ፣ በስም ማጥፋት መፍትሄ አያገኝም፡፡ ለሀገር የሚበጀው ልዩነትን በልዩነት ይዞ በሚያግባቡና በጋራ ለመቆም በሚያስችሉ ሀገራዊ ጉዳች ላይ ተከባብሮና ተቻችሎ፣ ተደማምጦ የሀገርን ሰላም ጠብቆ በጋራ መስራት ብቻ ነው፡፡ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ሰላም የሚበጀውም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡

ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ላይ ሁኖ ወገንን እንደጠላት በመቁጠር የመአት አውርድ ጦርነት ማወጅ የሀገርን ውድመት ከመፈለግ ውጪ ሌላ ምንም አይነት መገለጫ የለውም። በሀገር ጥፋትና በሕዝብ ልጆች ሞትና እልቂት በሀብትና ንብረት ውድመት የተሻለ ነገ አይመጣም፡፡ ለምን ሀገር ትጥፋ፤ ለምንስ ትውደም፤ ለምንስ በመከራ የተገኘ ሀብትና ንብረት ይውደም፤ በሀገር መጥፋትና መውደም የሚገኘውስ ትርፍ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

በእዚህ መንገድ የሚመጣ አንዳችም ትርፍ የለም፤ ቢኖር እንኳ እርም ነው፡፡ በሕዝብና በመንግስት ንብረት ውድመት መፈንጨትና ጥፋትን መናፈቅ ሀገርና ሕዝብን ለማፋጀት መስራት የለየለት የሀገርና የሕዝብ ጠላትነት ነው፡፡ በኦሮሚያ የተከሰተው ባለቤት የሌለው የወጣቶች ሰልፍ በሰላማዊ መንገድ ኃሳባቸውን ገልጸው ተቃውሞአቸውን አሰምተው ከመመለስ አልፎ ጥፋትና ወድመት አስከትሎአል፡፡ ይሄን በዝምታ መቀበል ደግሞ የሚቻል አይደለም፤ የሚጠፋው የሰው ሕይወትና የሚወድመው የሀገርና የሕዝብ ሀብትና ንብረት ነውና፡፡ ሕግ መከበር ስርአትም መኖር የግድ አለበት፡፡

እነዚህ ወገኖች የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ብሎ ነገር ፈፅሞ የሌላቸው፣ ለጥቅም የተገዙና ለሆዳቸው ያደሩ የግብጽና የሻእቢያ ቅጥረኞች በመሆናቸው ሀገር በማፍረስ ድርጊት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ናቸው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የማናከስ አጀንዳቸው ሀገርን እንደ ሀገር ለማጥፋት ከመዝመት የተለየ አይደለም፡፡

ድሕነትን ታግሎ ለማሸነፍ እየታገለ ያለን ሕዝብ ሰርቶ ሀገሩን ለመለወጥ እየተጋ ያለን ሕዝብ መናኛ በሆነ የዘርና የጎሳ ቅስቀሳ አንዱን በአንዱ ላይ እንዲነሳ ማድረግ ከወንጀሎች ሁሉ የከፋው ወንጀል ነው፡፡ ልዩነትን አቻችሎ ተከባብሮ በጋራ በመኖር ለዘመናት የዘለቀውን ሕዝብ ማባላቱና ማናቆሩ ለሀገሪቱ የውጭ ጠላቶች በር ከመክፈት የውጭ ኃይሎች መፈንጪያ እንድትሆን ከማድረግ ውጭ የሚጠቅም ምንም ነገር የለውም፡፡

በኦሮሚያ አካባቢ እየታዩ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎች ይህንኑ ተከትሎ የመጣው ንብረትን በእሳት አያይዞ የማውደም ድርጊት ንጹህ አእምሮ ባለው ማንኛውም ዜጋ  የሚደገፍ ተግባር አይደለም፡፡ ተግባሩ ሀገርንና ሕዝብን ተጎጂዎች ከማድረግ ውጪ ምንም ፋይዳ የለውም።

በአሁኑ ሰአት የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በተሀድሶው እንቅስቃሴ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው እንዳለ ሁኖ ይህንን ለማሰናከል በመንግስት ውሰጥ አድብቶ የሚገኘው ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ተሀድሶውን ለማሰናከል በብርቱ እየተንቀሳቀሰ የተለያዩ የማደናቀፊያ ስልቶችን በመጠቀም ሁከትና ግርግርን እንደማምለጫ መንገድ አድርጎ እየተጠቀመበት ለመሆኑ  አንዱና ዋነኛ ማሳያው የተፈጠረው ሁከትና ግርግር ነው፡፡

በስፋት በኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን በስሜታዊነት በመቀስቀስ ሰልፍ እንዲወጡ፣ ንብረት እንዲያቃጥሉ፣ የብጥብጥና የሁከቱ አድማስ እንዲሰፋ እየተሄደበት ያለው መንገድ ሀገራዊ ሰላምን የማደፍረስና ቀውስ የመፍጠር ሴራ ውጤት ነው፡፡

ወጣቱ በተሰማራበት መስክ ተግቶ ሲሰራ ነው ሀገሩን መሰደግ፤ ራሱንም መለወጥ የሚችለው፡፡ ብዙ ተለፍቶበት የተሰራውን፣ ስንትና ስንት የሀገር ገንዘብ የፈሰሰበትን ልማት በማውደም በማጥፋት ሀገርን ማልማትም ሆነ ማሳደግ አይታሰብም፡፡ የግለሰብ  ዜጎችም ንብረትና ሀብት ሊወድም፣ በእሳት ሊጋይ አይገባውም፡፡ ዘርፈው ያገኙት ነው ቢባል እንኳን ማስረጃው እስካለ ድረስ በሕግ ተጠያቂ በማድረግ መልሶ ለሀገርና ለሕዝብ በሚጠቅም ስራ ላይ ይውላል ይገባል እንጂ ንብረቶቹን ማውደም አይገባም፡፡ ይህን ያደረጉትም ከሕግ ተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡

የሀገራችን ሕዝብ እጅግ ሰላማዊና ሰላሙን ወዳድ ነው፡፡ ሰላሙንና ሀገሩን ነቅቶ የሚጠብቅ፣ መከፋፈልን የማይወድና የማይደግፍም ነው፡፡ የትኛውም አይነት ችግሮች ቢኖሩ በሰከነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ይቻላል በሚለው አስተሳሰብ አጥብቆ የሚያምን ህዝብ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ፡፡ ስርአት ባለው መንገድ ከመሄድ ይልቅ የጥፋት አቅጣጫን መከተል፣ ግጭቶችን ማስፋፋት፣ መልካቸውን ቀይረው በወረርሽኝ መልክ እንዲዛመቱ ማድረግ ወጣቶችን የጥፋት መሳሪያ በማድረግ ለመጠቀም የሚሮጡትን ኃይሎች አጋልጦ ማውጣት ግድ ይላልና ይህንን ደግሞ ህዝቡ ራሱ ያደርገዋል፡፡

የሀገርንና የሕዝብን ሰላም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ በመስጠት መጠበቅ የዜጎች ሁሉ የቅድሚያ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ግርግሩ፣ ሁከቱ፣ ትርምሱ . . . ሀገራዊ ኢኮኖሚውን፣ የሕዝቡንም የእለት ተእለት እንቅስቃሴና መስተጋብር በእጅጉ የሚጎዳ ስለሆነ አይጠቅመንም፤ አይበጀንም፤ ስለዚህም ባሰቸኳይ መቆም አለበት፡፡ የአንዳንድ አገሮች ልምድ እንደሚያሳያው ከእንደዚህ አይነቶች ሁከትና ትርምስ ጀርባ የውስጥ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል ከፍተኛ ሀብትና ንብረት ስለዘረፈ ከዚህ ለመውጣት በማሰብ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመበተን ሰላምና መረጋጋቱ እንዲደፈርስ ቅጥረኞችን ገዝቶ ያሰማራል፡፡ ይህንን መሳይ ሴራ እዚህ እኛስ ጋ ስለመኖር አለመኖሩ ምን ማረጋገጫ አለ?? ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy