Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአብሮነት እሴቶቻችን ይጠናከሩ!

0 340

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአብሮነት እሴቶቻችን ይጠናከሩ!

ዳዊት ምትኩ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት እንደ ቀውስ በመመልከት ቀውሱን ለበጎ ስራ ልንጠቀምበት ወደሚችል መልካም አጋጣሚ መቀየር ይቻላል። የህዝቦች የጋራ ፍላጎት ሰላምና ልማት ብቻ ነው። ከግጭት ተጠቃሚ ወገን ሊኖር አይችልም። ለዘመናት አብረው ይኖሩ የነበሩት ህዝቦች የአብሮነት እሴቶቻቸውን ጠብቀው መጓዝ ይኖርባቸዋል። ችግሩ የሁለቱ ክልሎች ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ የመፍትሔው አካል ይኖርታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውና የሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት በህገ መንግስቱ መሰረት በክልሎቹና በፌዴራል መንግስቱ አማካኝነት እልባት እየተሰጠው ነው።

ምንም እንኳን ስርዓቱ ከተመሠረተ ወዲህ በተለያዩ ወቅቶች በተወሰኑ አካባቢዎች በጎሳዎች መካከልና በአንዳንድ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች መኖራቸው አይካድም። እነዚህ ግጭቶች ፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠራቸው አልነበሩም። በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ግጭት መኖሩ ነባራዊ ሃቅ ነው።

ከእኛ ሀገር አንፃር የሚከሰቱት ግጭቶች ግን አንዳንዶቹ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የጎሣ ግጭቶች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከልምድ ጉድለት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ይህንን ተንተርሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ሁከቶች ናቸው።

ርግጥ የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት የግጭቶች ምክንያት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብትና እንዲያብብ ላለፉት 26 ዓመታት በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ተግባራቶችን ሲያከናውን የነበረና በዚህም አበረታች ውጤት ያመጣ በመሆኑ ነው።

ያም ሆኖ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የሚፃረሩ ተግባራትን ጠንክሮ ማስወገድ ይገባል። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሀገራችን ህዝቦች እሴት እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። ይህ እሴት የሀገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዩጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ርግጥ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ማንነት ተደፍቆ ሊመጣ አይችልም። ተከብሮ እንጂ። ባለፉት 26 ዓመታትም ሁሉም ማህበረሰብ በራሱ ቋንቋ የመናገር መብቱ የተጠበቀለት በዚሁ ፅንሰ ሃሳብ መነሻነት ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል። ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ስለሆነ ነው።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል። በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው። ዛሬም የትምክትና የጠባብነት ፈተናዎች በሀገራችን ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው ግን አይቀርም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይህ እሴት ይበልጥ እንዲያብብ ምቹ ሁኔታዎችን ስለፈጠረ ነው።

በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሴት ውስጥ የራስ ማንነትን ማወቅ፣ የሌሎችን ማንነት ማወቅ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና አካባቢን ማልማት ወሳኝ ጉዳዩች ናቸው። ማንነትን ከማወቅ አኳያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ያስፈልጋል። የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መለየትንም እንዲሁ። የሌሎችን ማንነት በማወቅ ረገድም፣ ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም መለየት ያስፈልጋል።

እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን ያካትታል። አካባቢን ከማልማት አኳያም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ከባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን የሚያካትት ነው።

ሀገሪቱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዕውን መሆንና ማበብ የታገለ ድርጅትና እንዲሁም እሳቤውን በመርህ በፅናት በማስፈፀም ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው። ምንም እንኳን በርካታ ህዝቦች ያሉት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይገባልም።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲከብር በአንፃሩ ደግሞ  መከበርን ያተርፋል።

ርግጥ ያለፈው ታሪክ አንድን ህዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል። ይህ አስተሳሰብ ግን ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት አይደለም። ሊሆንም አይችልም። አንድ ህዝብ ሌላውን የሚበድልበት ምንም ዓይነት መነሻ ሊኖረው ስለማይችል ነው።

እንደሚታወቀው የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ይሞክራሉ። ሆን ብለውም አንዱን ከሌላው ጋር ለማጋጨት እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል። ይህ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም።

በዘመናት አብሮነት ቆይታው ተቻችለው የኖሩ ህዝቦች በምንም ዓይነት ሁኔታ አብሮነታቸው ሊፈታ አይችልም። የዛሬን ሳይሆን የትናንትንና የነገን ህይወታቸውን ይመለከታሉ። እናም ጊዜያዊ ችግር አብሮነትን የማያበላሽ በመሆኑ ለዘላቂ ህይወት በጋራ ተሳስቦ መኖር ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊሙም ይሁን ክርስቲያኑ አሊያም የሌላ እምነት ተከታዩ አብሮ የሚጋራቸው እሴቶች ያሉት ነው። በህዝቦች መካከል መለያየት የለም። ሊኖርም አይችልም። የተፋለሱና ትክከል ያልሆኑ አስተሳሰቦች ኢትዮጵያዊ አይደሉም።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ ያላቸው እንጂ በሰበብ አስባቡ የሚናቆሩ አይደሉም።

መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሐዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ እንጂ የጋራ እሴቶቻቸውን የሚንዱ አይደሉም። በመሆኑም የአብሮነት እሴቶቻቸውን አሁን ካለው በላይ ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ይህን የአብሮነት እሴቶቻችን ለማጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy