Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአገር ፍቅር፣ የአገር መውደድ መገለጫው ምን ይሆን?

0 2,445

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአገር ፍቅር፣ የአገር መውደድ መገለጫው ምን ይሆን?

ወንድይራድ ኃብተየስ

አገር መውደድ ማለት ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡ አገር ማለት ህዝብ፤ ህዝብም ማለት አገር ነው። አገርና ህዝብ የማይነጣጠሉ አንዱ ካአንዱ ትርጉም  የማይኖረው  እጅግ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። አገር መውደድ ማለት ህዝብን መውደድ፣ ህዝብን ማገልገል፣ ለህዝብ መሞት፣ ለህዝብ መጎዳት  ማለት ነው። አዎ አገር ወዳድ ዜጋ ማለት  ራሱን ለብዙሃኑ  ጥቅም አሳልፎ  የሚሰጥ፣ ብዙሃኑም ስለአንዱ የሚገዳቸው  ማለት ነው። ይህ ነው የአገር ፍቅር፤ ይህ ነው የህዝብ ፍቅር ማለት።

የአገር ፍቅር የሚገለጽበት ሁኔታ  ከጊዜው ጋር  የሚለያይ ነው። ለአብነት የጥንት አባቶቻችን አገራቸውን ከውጭ ወራሪ ተከላክለዋል፣ ያ ትውልድ በመባል የሚታወቀው አሁን ላይ በ50ዎቹና በ60ዎቹ ዓመታት የሚገኘው ትውልድ ደግሞ እንደተራራ የገዘፈውን  አምባገነኑን ደርግ በመፋለም ህዝባቸውንና አገራቸውን ነጻ አውጥተዋል፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን አድርገዋል። የአሁኑ ትውልድ አገር ወዳድነት መገለጫ መሆን ያለበት ደግሞ  አገራችን የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ  ማጎልበት እንዲሁም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ማስቀጠል መሆን መቻል ይኖርበታል።     

የአገራችን ህዝቦች በእነዚያ ከፋፋይና ጨቋኝ ስርዓቶች እንኳን ተነጣጥለው አያውቁም። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ትሁን እንጂ በቀድሞ ስርዓቶች አገራችን ብዝሃነትን ማስተናገድ ተስኗት ነበር።  የቀድሞ ስርዓቶች ህዝቦችን በማንነታቸው፣ በዕምነታቸው፣ በባህላቸውና በመሳሰሉት በመከፋፈል አንዱን በማቅረብ ሌላውን በማራቅ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ቢከተሉም ህብረተሰቡ አልተለያየም።

ህብረተሰቡ ገዢ መደቦች በቀደዱላቸው የመለያየት መንገድ አልተጓዙም። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው አገራችን በፋሽስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ሁሉም  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  አገራቸውን   ከውጭ  ወራሪ ሃይሎች   ለመከላከል  ሲሉ  ልዩነታቸውን ወደጎን በማለት  ከጫፍ እስከ ጫፍ በመሰባሰብ በአንድነት ዘምተው ወራሪውን ኃይል አድዋ ላይ አሳፍረው መልሰውታል። የአገራቸውንም ዳር ድንበር በደማቸው አስከብረዋል።  ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት፣ ይህ ነው የአገር ፍቅር! ይህ ድል  ለመላው አፍሪካዊያን  ከዚያም ባሻገር ለመላው ጥቅር ህዝቦች ኩራት ለመሆን በቅቷል። የአድዋ ድል  ለእኛም በራስ የመተማመንና መንፈስ እንድናጎለብት አድርጓል።  

ያ ትውልድ በመባል የሚታወቀው አሁን ላይ በ50ዎቹና በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ትውልድ  ከደርግ ጋር ተዋግቶ በርካቶች ህይወታቸውንና አካላቸውን  መስዋዕት አድርገው  አዲሲቷን ኢትዮጵያ መስርተዋል። ይህ ነው ለሌሎች መኖር፤  ራስን መስዋዕት በማድረግ ሌሎች እንዲጠቀሙ፤ ይህ ነው  ኢትዮጵያዊነት፣ ይህ ነው የአገርና የህዝብ ፍቅር፣ ይህ ነው አገርና ህዝብ መውደድ ማለት!

ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ክቡር ህይወታቸውንና  አካላቸውን ገብረው ህዝቦች በነጻነት፣ በፍትህና በዕኩልነት የምታስተናግድ  አዲሲቷን ኢትዮጵያ መስርተዋል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ  ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የእኔ ናት የሚሏት አገር ለመሆን በቅታለች፤ አዲሲቷ ኢትዮጵ ሁሉም በነጻነትና እኩልነት የሚተዳደሩባት ዴሞክራሲያዊት  ብዝሃነትን ማስተናገድ የምትችል አገር ናት።  

የአዲሱ ትውልድ የአገርና የህዝብ ፍቅር መገለጫ እንደቀድሞ አያቶቹና አባቶቹ በመሞትና በአካል መጉደል አይደለም። እንደዛ ያለ መስዋዕትነት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚያስፈልግ አይደለም።  አዲሲቷ ኢትዮጵያ ህገመንግስታዊነት የሰፈነባት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ሁሉም የእኔ የሚላት አገር ለመሆን በቅታለች። የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት  የህዝቦች  ትስስርና አብሮነት እንዲጎለብት፣ ማንነቶች እንዲከበሩ፣ እኩልነት እንዲሰፍን፣ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ  በማድረጉ  አዲሲቷ ኢትዮጵያ የፈጣን ልማትና  ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተምሳሌት በመሆን ላይ ነች። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ከአዲሱ ትውልድ የምትሻው  የተጀመረው  የዴሞከራሲ ስርዓትን  ማጎልበትና ልማቱን በማፋጠን ህዳሴዋን ማረጋገጥ ነው። የአዲሱ ትውልድ የአገርና የህዝብ  ፍቅር መገለጫው ይህ ነው። ይህ ደግሞ ላብ እንጂ ደም የሚጠይቅ መሰዋዕትነት አይደለም።

ዛሬ በየዘፈኑና በየድርሰቱ  አሊያም በማናቸውም ሃሳብን የመግለጫ ዘዴ ስለአገር ፍቅር የሚገለጸው ሁሉ ቢተገበር በአገራችን መተሳሰብና መረዳዳት ምን ያህል እንደሚጎለብት  መረዳት የሚከብድ አይደለም። በዕርግጥ በርካቶች ይህን  በተግባር አስመስክረዋል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ካላቸው ከፍለው ለተራቡ አብልተዋል፣ ለታረዙ አልብሰዋል፣ ለተቸገሩ ረድተዋል። አዎ ይህ የሚየኮራ ባህላችን ነው። ሁሉም  እወዳታለሁ ለሚላት አገር፣ አሊያም እንወዳቸዋለን ለሚሏቸው ህዝቦች ሁሉ በተግባር በሚከፈል መስዋዕትነት መሆን መቻል አለበት። ከላይ ለማንሳት  እንደተሞከረው በቀድሞዎቹ ጊዜያት አያት ቅድመ አያቶቻችን  በአድዋ ድል  እንዲሁም በቅርብ ታሪካችን ደግሞ ለዕኩልነትና ነጻነት  ሲሉ በከፈሉት መጠነ ሰፊ መስዋዕትነት የአገር ፍቅራቸውን በገቢር ያስመሰከሩ ታጋዮችን ማንሳት ይቻላል።

አዲሱ ትውልድ ለመጪው ትውልድ ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም በሚል ፍጹም አገራዊ እልህና ቁጭት በመነሳሳት በድህነት ላይ ጦርነት ከፍቷል።  የአሁኑ ትውልድ በተለይም  በመጀመሪያውና በሁለተኛው  የዕድገትና  ትራንስፎርሜሽን ዕድገት አገራችን ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች።  ወጣቱ  ትውልድ አገር በመገንባትና ታሪክን በማስቀጠል ረገድ ትልቁን ሃላፊነት  ይሸከማል።  

የአዲሱ ትውልድ ሃላፊነት  የተጀመረውን  የዴሞክራሲ ስርዓት  ማጎልበት እንዲሁም  ልማትን ማስቀጠል ነው።  ይህ ደግሞ ላብ እንጂ ደምን አይጠይቅም።  ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ከወጣቶች ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት “ድህነትን ለማስወገድ ተራራ መውጣት፡ ፋኖ ተሰማራ እያሉ መዘመር አያስፈልግም። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ጥሩ ሞያተኛ፣ ጥሩ ግንበኛ፣ አናፂ መሆን ብቻ የሚጠይቅ ነው። ዴሞክራስያዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው መሆን ያስፈልጋል። ራስን ከተለያዩ ማህበራዊ ግድፈቶች ነፃ ማውጣት ይጠይቃል። የአሁኑ ትውልድ  የአገር ፍቅር መገለጫው  የአገር መውደድ  ማረጋገጫው  ድህነትን መፋለም፣ ድህነትን መዋጋት መሆን መቻል አለበት።

እርግጥ ነው! ከዚህ አንጻር በርካታ ወጣቶች አገርን በሚያሳድጉ  ልዩ ልዩ የልማት መስኮች በመሳተፍ፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወገኖቻቸው በሥራ ፈጠራ፣ በምህንድስና፣ በምርምር፣ በህክምና፣ በጤናና በግብርና ሥራ ወዘተ ተሰማርተው አገርና ህዝብን የሚያኮራ ውጤት በማስመዝገብ  ላይ ናቸው፡፡ በርካታ ወጣቶች ከምንም ተነስተው መንግስትና ህዝብ ባደረጉላቸው  ድጋፍ ውጤታማ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ወጣቶች  መረዳት ያለባቸው  አአንዱና ዋንኛው  ቁም ነገር  ለለውጥ መጀመሪያው ቁጠባን  ማዳበር እንዲሁም  ለስራ ተገቢውን  ክብር መስጠት መሆኑን ነው። ወጣቶች የተገኘውን ስራ በመስራት እንዲሁም  ነገ  አድጋለሁ፣ እቀየራለሁ  በሚል ስሜት  ከሚያገኟት ገቢ ላይ  መቆጠብ ይኖርባቸዋል።      

ወጣቱ ለአገርና ለወገኑ ሊያስብ የሚችለው ራሱን  ከአደጋ መታደግ ሲችል ነው። አሁን ላይ የበርካታ ወጣቶቻችንን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እየነጠቀን ያለው  አንዱ አደጋ ህገወጥ ስደት ነው። በርካታ ወጣቶች  በተራ ደላሎች የተስፋ ቃል  በመደለል  እንዲሁም  በአቋራጭ  የመክበር መጥፎ ስሜት ሳቢያ አገራቸውን በመተው ራሳቸውን ለከፋ የህይወትና የአካል አደጋ በማጋለጥ በህገወጥ መንገድ  በመሰደድ ላይ ናቸው።   ስደት  የአገርና የህዝብ ፍቅር  መገለጫ አይደለም። ህገወጥ ስደት  በምንም ሁኔታ ለችግሮች መፍትሄ  ማምጣት  አይቻልም። +

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy