Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ተስፋዎቻችን

0 484

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ተስፋዎቻችን

                                                   ቶሎሳ ኡርጌሳ

መንግስትና ህዝቡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የያዟቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ መዋቅራዊ ሽግግርን ሊያመጡ የሚችሉ መሆናቸው በተደጋጋሚ የተገለፀ ጉዳይ ነው። በተለይም ኢንዱስትሪው የመሪነቱን ሚና ከግብርናው እንዲወስድ እየተደረገ ባለው ጥረት ዘርፉ ወደፊት ተወዳዳሪ ሆኖ የሀገራችንን ምጣኔ ሃብታዊ ግስጋሴ የሚደግፍ ነው።

ኢንዱስትሪው በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ዕውን ከማድረግ አኳያ ሀገራችን የነደፈችውን የልማት ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥተኛ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ሆነ በነባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርታማነት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ እመርታና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በከፍተኛ ደረጃ እንድንንቀሳቀስ ያደርጋል።

እናም በልማት ዕቅዱ ዘመን በኢኮኖሚው ላይ የሚታይ መዋቅራዊ ለውጥን ለማስጀመር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ይህ ለውጥም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ዕውን ይጥላል። ሀገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል ይፈጥራል።

መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም። ሆኖም ይህን አሃዝ በ2012 ዓ.ም ላይ ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታስቧል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ዘርፉ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ከዚህ አኳያ በተጠናቀቁት ሁለት የዕቅዱ ዓመታት የተገኘው ለውጥ አርኪ ነው። የታለመውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ያመላከተ ነው። ይህ ለውጥ የተገኘው ሀገራችን ውስጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሁከት ተፈጥሮ በነበረበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ከዚህ በላይ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻል መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ኢንዱስትሪውን በ2012 ዓ.ም በምንፈልግበት ደረጃ ማድረስ ከቻልን ወደ መጀመሪያ ደረጃ የመካከለኛ ገቢ ለመድረስ ባሰብንበት በ2017 ዓ.ም የዘርፉን እመርታ ወደ 40 በመቶ ለማድረስ ታስቧል። ርግጥ ይህን ግብ ማሳካት ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ በአንድ ወቅት እንዳሉት፤ የምናቅዳቸው ዕቅዶች ወገባችንን የሚያጎብጡን ቢሆኑም እንኳን ቅሉ ጠንክረን ከሰራን የማናሳካበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።  

እናም ወደፊት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚኖረው የሰው ኃይል አሰላለፍና የስራ ፈጠራ የመዋቅራዊ ሽግግሩ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ አይቀርም። አሁን ባለው አሃዝ መሰረት በመካከለኛና በከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተሰማራው የሰው ኃይል ከ350 ሺህ በላይ ይገመታል።

ታዲያ ይህ አሃዝ በሁለተኛው የልማት ዕቅድ እና ከእርሱም ቀጥሎ ባሉት አምስት ዓመታት በአራት እጥፍ ያድጋል። አሃዙ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ያሳያል።

ከዚህ ውስጥ አሁን የምንገኝበት ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ድርሻ የተያዘውን የአስር ዓመት ዕቅድ በግማሽ እንዲሳካ ማድረግ ነው። ይህም ወደ 750 ሺህ ዜጎች በዘርፉ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ያጠቃልላል። ይህ ዕውን ከሆነም አሁን ያለውን የሰው ኃይል ስራ ፈጠራን የሚፈጥር ነው።

ይህን ውጥን ለማሳካት ርብርብ ማድረጉ የግድ ነው። ዘርፉ በተለይ ወጣቶችንና ሴቶችን የሚያሳትፍና በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የዕቅዱን ገቢራዊነት ማረጋገጥ መቻሉ አጠያያቂ አይሆንም።

ርግጥ መንግስት የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከወዲሁ እያከናወና ያለውና በዕቅድ ደረጃ የያዛቸው የተለያያዩ የተጠቃሚነት ማዕቀፎች በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሃቁን የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ሁኔታም በቀሪው የልማት ዕቅዱ ዓመታት ተጠናክረው ከቀጠሉ ስኬቱን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ናቸው።

ርግጥ በዘርፉ የተጠቀሱትን ስኬቶች እውን ለማድረግ በሁለት ዘርፎች (ማለትም ለጥቃቅንና አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች) የተሰጠው ትኩረት የመዋቅራዊ ሽግግሩ ሁነኛ አመላካች ናቸው። በሁለቱም ዘርፎች ውስጥ ኤክስፖርት መር የኢንዱስትሪ አቅጣጫን ለመከተልና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ለመዋቅራዊ ሽግግሩ የራሱን ሚና ይጫወታል።  

እንደሚታወቀው በሀገራችን ውስጥ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰረቱ ይህን ያህል የሚያስመካ አይደለም። ግና በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉት ተግባሮች መደሰረቱን እያሰፉት ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን ሀገራችን በዘርፉ ለውጥ እንድታመጣ በዋነኛነት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና ማጎልበት አለባት።

በተለይም በማደግ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ባለሃብት የለውጡ ተሳታፊ እንዲሆን እንዲሁም በተመረጡ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተግባሩ እንዲከናወን ማድረግ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖራቸው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳታፊነት የማይናቅ ቦታ ይኖረዋል። ይህም የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ሚና አለው። በአሁኑ ወቅት የውጭ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተሳትፈው እያሳዩት ያለው ለውጥ አበረታች ነው።

ርግጥ በአሁኑ ወቅት ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው። ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዲሁም በአፈፃፀማቸው ጥሩ ስምና ዝና ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎች በመመልመልና የማግባባት ስራ በማከናወን የዘርፉን ዕድገት እንዲያሳድጉም እየተደረገ ነው። ባለሃብቶቹን ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች ላይ በማሰማራት ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ ጥቱ ቀጥሏል። ውጤትም እየተገኘበት ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶች ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ውስጥ እንዲካተቱ ስታደርግ፤ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቦታ ሳትሰጥ አለመሆኑን መረዳት የሚገባ ይመስለኛል። አዎ! የሀገር ውስጥ ልማታዊ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በዘርፉ እንዲያፈሱ እየተደረገ ነው።

በተለይም ባለሃብቶቹ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተመልምለው በቂ ድጋፍና ማበረታቻ እየተሰጣቸው በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገቢ ምርቶችን በሚተኩ ዘርፎች ጭምር እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው። ስራቸው ለሌሎች ሀገር በቀል ልማታዊ ባለሃብቶች አርአያ እንዲሆንና ባለሃብቶቹም ተስበው ወደ ተመሳሳይ ሀገራዊ ስራ እንዲገቡ ማበረታቻ እየተሰጣቸው ነው።

እነዚህ ተጠቃሽ እውነታዎች ተጠቃለው ሲታዩ ሀገራችን ለማሳካት ያቀደችውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያሳልጡ ተስፋዎቻችን ናቸው። እነዚህ ተስፋዎቻችን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ሲያመጡ የህዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣሉ። ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ደግሞ ኢትዮጵያ አሳካዋለሁ ያለችውን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ የመድረስ ራዕይን እውን ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy