Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኦሮሞ ወጣቶች የመጣላችሁንና የመጣባችሁን ለዩ

0 349

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኦሮሞ ወጣቶች የመጣላችሁንና የመጣባችሁን ለዩ

ኢብሳ ነመራ

ኦሮሚያ በ2008 ዓ/ም አብዛኞቹን ወራት በአመዛኙ ወጣቶች የተሳተፉባቸው የተቃወሞ ሰለፎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን እናስታውሳለን። የእነዚህ የተቃውሞ ሰልች መነሻ በተለይ በመሬት ዝርፊያ የተገለጸ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል ነበር። በከተሞች መስፋፋት፣ በመሰረተ ልማት መስፋፋት እንዲሁም በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ምክንያት ከመሬታቸው የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ተገቢውን ማካካሻ አለማግኘት፣ የወጣቶች የልማት ተሳታፊ አለመሆንና በሃገሪቱና በክልሉ ከሚመዘገበው እድገት ተጠቃሚነት ማጣትም ተቃውሞዎቹን የቀሰቀሱ ምክንያቶች ነበሩ።

የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት፣ በእነዚህ ተቃውሞዎች የተነሱትን ጥያቄዎች ተገቢንት ተቀብለዋል። በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳዳር መጓደል ችግር መኖሩን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አስቀድሞ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አቋም የያዘበት ጉዳይ በመሆኑ እንደችግር መቀበል አልከበደውም። በተለይ በ2007 ማብቂያ ላይ በተካሄደው 10 የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓደል የህልውና ጉዳይ መሆኑን፣ የሞት የሽረት ትግል ሊካሄድበት እንደሚገባም ተወስኖ እንደነበረ እናስታውሳለን። ኢህአዴግ በዚህ ድርጅታዊ ጉባአው ባሳለፈው የአቋም መግለጫ፤ 9 ነጥቦችን በያዘው የአቋም መግለጫ በ1ኛው ነጥብ ላይ፤

. . .የብዙዎቹ ችግሮቻችን ዋነኛ መንስኤና ምንጭ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጋር የተያያዘ መሆኑን የተመለከተው ጉባኤያችን በቀጣይ ዓመታት የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ሆነው የተለዩትን የመሬት፣ የግብር ኣሰባሰብ የመንግስት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ስር ነቀል በሆነ ሁኔታ ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አስምሮበታል። በመሆኑም እኛ የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ተግባራት እንዲጎለብቱ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በላቀ ደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ለመረባረብ ቃል እንገባለን። በሚል ተገልጾ ነበር። በተመሳሳይ የአቋም መግለጫው 9ኛው ነጥብ፤

. . . የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ እየተዳከመ ባለመሄዱ ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጣችን የሚፈለገውን ለውጥ ህዝባዊ እርካታ ለመረጋገጥ እንዳልተቻለ፣ ህዝባችንን ቅሬታ ውስጥ የሚያስገቡና የልማታችን እንቅፋት የሆኑ አድሎአዊ አሰራሮች የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት እንዲሁም ሙስናን የመሳሰሉ ብልሹ አሠራሮች እንዳሉ ጉባዔያችን በአጽንኦት አይቷል። በመሆኑም እኛ የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የድርጅታቸን ህዝባዊ መርሆዎችና አሰራሮች እንዲከበሩና የህዝቡን ተሳትፎና ባለቤትነት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን በመያዝና የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፣ በምርጫ ያከበረንና ችግሮቻችን እኛው እንደምንፈታ በማመንና ግልፅ መልእክት በማስተላለፍ በድጋሚ እንድንመራው ፈቃድ የሰጠንን የሀገራችንን አስተዋይና አርቆ አሳቢ ህዝብ፤ በጠንካራ የተቋማት ግንባታ፣ በግልፅነትና ተጠያቅነት ስርዓት ለማገልገል በድርጅታችን ፀንቶ የቆየውን የውስጠ ድርጅት ትግል በማቀጣጠልና ህዝቡን በተደራጀ አግባብ በማሳተፍ በመልካም ኣስተዳደር ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቃል እንገባለን።

በሚል ተገልጿል።

ይህ የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳደርወን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ጨምሮ ኢህአዴግ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መጓድልና የሚያስከትሉት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወዘተ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በ2008 ዓ/ም ሁከቶች ከመቀስቀሳቸው አስቀድሞ ተገንዝቦ እንደነበረ ያመለከታል። ችግሮቹ መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ህዝብን ማስከፋታቸውንም በሚገባ ተረድቶ እንደነበረ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ስጋቱን ገልጾ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ህዝባዊ ንቅናቄ ለመጀመር ሲዘጋጅ ነበር በኦሮሚያ ተቃውሞው ድንገት የፈነዳው። ኦህዴድ/ ኢህአዴግ ህዝብ ለተቃውሞ እንዲወጣ ያደረገው ችግር ትክልል መሆኑን አምኖ ችግሩን ለማስተካካል ዳግም ቃል ገባ። የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግርን በማቃለል የህዝብ እርካታ ለመፍጠር በድርጅቱ ውስጥና በመንግስት ውስጥ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ጀመረ።

አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የተሃድሶው አመራር ነው። የተሃድሶው አመራር በ2009 ዓ/ም ሃላፊነት ከተረከበ በኋላ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመጠራረግ ባደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። በመሬት ወረራ በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን እንዲሁም በኢንቨስትመንት ስም ተይዘው ሳይለሙ ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን ቀድሞ ባለመሬቱ ለነበረው አርሶ አደሮችና ለከተማ ስራ አጦች በመስጠት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። በመሬት ወረራ ውስጥ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ላይ እርምጃ ወስዷል። በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተፈጥሮ የተቸረን የማዕድን ሃብት፣ አንዳችም ተጨማሪ እሴት ሳያክሉበት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ተግባር ሳያከናውኑ እየዛቁ ከበለጸጉ ባለሃብቶች ላይ በመንጠቅ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩበት አድርጓል። በከተሞች መስፋፋትና በልማት ሰበብ ከቦታቸው የሚነሱ አርሶ አደሮች መብቶችን የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል። ተጀምረው ያለአግባብ የተጓተቱና የተቋረጡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተቋማትን ለማስጨረስ የሚቻለውን ያህል ተፍጨርጭሯል። የተሃድሶው አመራር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁሉም የህዝብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምላሽና መፍትሄ ማስገኘት ባይችልም፣ ለህዝብ ጥቅምና እርካታ የቆመ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ለጥያቄዎቹና ለቅሬታዎቹ ምላሽ መስጠቱ አይቀሬ መሆኑን ህዝብ አምኖ እስኪቀበል ደረስ የለውጥና ልማት አመራር መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል። አሁን በህዝቡና በክልሉ መንግስት መሃከል የሚታየው መትማመን ለዚህ አስረጂ ነው።

ይሁን እንጂ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰበቦች እየተፈለጉ ህገወጥ አድማዎችና ሁከቶች እንዲቀሰቀሱ የማድረጉ ሙከራ አልተቋረጠም። በተለይ ነሃሴ፣ 2009 ዓ/ም የነጋዴዎችን የእለት ገቢ ግመታና መነሻ በማድረግ ጃዋር መሃመድ በተባለ ግለሰብ፣ ሃገር ውስጥ ባሰማራቸው ቅጥረኞች አማካኝነት ነጋዴውን በማስፈራራት ሶቆች እንዲዘጉ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ለማድረግ መሞከሩን እናስታውሳለን። ይህ በጥቂት ከተሞች ውስጥ የሃይል እርምጃ በመውሰድ ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረ አድማ በህዝቡ ተቀባይነት ማግኘት ባለመቻሉ በጥቂት አካባቢዎች ተሞክሮ ተቋርጧል። ልብ በሉ፤ ነጋዴው ማህበረሰብ በገቢ ግምቱና ከዚህ በመነሳት የሚወሰንበት ግብር ላይ ቅሬታ ካለው ይግባኝ የሚልበት እስከጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚዘልቅ ስርአት ተቀምጦ ነበር። የተሃድሶው አመራር ደግሞ የነጋዴው ማህበረሰብ ቅሬታ እንዲሰማ የማድረግ ቁርጠኝነቱ ነበረው። ይህን ችላ በማለት የተሞከረው አድማ በኦሮሞ ህዝብ ጉዳት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘትን ዓላማው ያደረገ ነበር።

ሰሞኑን ደግሞ አውዳሚ ሁከቶች እየተቀሰቀሱ ነው። የተሃድሶው አመራር ለኦሮሚያ ህዝብ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን በየአቅጣጫው ጥረት በሚያደርግበትና ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ ባለበት ወቅት፣ በተለይ ለወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በሚማስንበት፣ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘና ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋ ሰጪ በሆነበት ወቅት የተቀሰቀሰ ሁከት መሆኑን ከበፊቱቶቹ ልዩ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ፤ ክልሉ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ድንበርን ሰበብ በማድረግ በኦሮሞዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን እንዲሁም እስከ ግማሽ ሚሊየን የሚደርሱ ኦሮሞዎች ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መፈናቀላቸውን ተከትሎ ኦሮሞዎች ከዳር እስከዳር አንድነታቸውን አጠናክረው ወገኖቻቸውን ለመርዳት በተነሱበት ማግስት የተቀሰቀሰ ሁከት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱት ሰልፎች፣ በህዝብ ሃብት ላይ ውድመትና ግድያዎች የሚፈጸምባቸው ሁከቶች ይፋ ባለቤት የላቸውም። በአውዳሚዎቹ ሁከቶች ላይ የሚሳተፉት ወጣቶች የተሃድሶው አመራር ምላሽ ለመስጠት እየተረባረበ ከሚገኝባቸው የህዝብ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን ጥያቄዎችና ጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ያልተሸፈነ ምንም አጀንዳ የላቸውም። ጥቃት እየሰነዘሩባቸው የሚገኙት ዜጎችም ከመንግስት አስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንጹህ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በኦሮሞዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ተጽእኖ ለመከላከልና ችግሩ በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ እንዲያገኝ ለማድረግ የኦሮሞ ህዝብ ከዳር እስከዳር አንድ ሆኖ ከክልሉ መንግስት የተሃድሶ አመራር ጋር በአንድ አፍ በሚናገርበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑም መታወቅ አለበት። የአደባባይ ተቃዋሚዎቹ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውንና የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ አስመልክቶ የክልሉን መንግስት በድክመት መጠየቅ ወይም መውቀስ የሚያስችላቸው ምንም አጀንዳ የላቸውም። በአጠቃላይ ኣኪዎቹ ምን ይደረግ እንደሚሉ የሚታወቅ ነገር የለም። ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተካሄዱት አውዳሚ የተቃውሞ ሁከቶች በሃገር ሽማግሌዎችና በወጣቶች (ፎሌዎች) የተወገዙት ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ነው።

እና ይህን የሁከት እንቅስቃሴ የሚመራው  ማን ይሆን? አላማውስ ምን ይሆን?

በተለይ ድንበርን ሰበብ በማድረግ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦሮሞዎች ላይ የተፈጸመው በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት በኦሮሞዎች ዘንድ የፈጠረው አንድነት፣ በክልሉ መንግስትና ህዝብ መሃከል የፈጠረው መግባባት ያስደነገጣቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ። ከውጭ ሆኖ ይህን የኦሮሞዎች አንድነት ማፍረስ እንደማይቻል ያውቁታል። እናም ጥቂት የሁከት ተልእኮ አስፈጻሚዎችን አስርጎ በማስገባት የግንዛቤ ጉድለት ያለባቸውን የኦሮሞ ወጣቶች በማነሳሳት የኦሮሞዎችን አንድነት እንዲያፈርሱ የማድረግ ተልእኮ ሰጥተው የቀሰቀሱት ሁከት ነው። በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት በተለይ በመሬት ወራሪዎች፣ የማዕድን ሃብት በመዛቅ ያለአግባብ የበለጸጉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ወስዷል። በቀጣይም የመሬት ወረራ ሊካሄድ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘግቷል። የመሬት ወረራን የመከላከል ጉዳይ የህዝብ የሚሆንበትን ስርአት አመቻችቷል። እንደልብ ሲዘረፍ የነበረው የኦሮሚያ መሬት ካሁን በኋላ የማይቀመስ ሆኗል።

ይህ ብቻ አይደለም። የክልሉ ህዝብና መንግስት ከክልሉ አዋሳኝ አካባቢዎች በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶችን፣ ዶላርን ጨር ከሃገር የሚወጡ የውጭ ምንዛሪዎችንና ምርቶችን አላንቀሳቅስ ብሏል። ይህ ሁኔታ እነዚህን ዘራፊዎች አበሳጭቷል። በመሆኑም በየአካባቢው ሁከት በመቀስቀስ ትኩረቱን መበተንና የቁጥጥር አቅሙን ማዳከም፣ ክልሉ በሁከትና ግርግር የህግ የበላይነት ሊረጋጋጥ የማይችልበት የስጋት ቀጠና እንዲሆን የማድረግ ፍላጎት አላቸው። ይህን ማድረግ የሚያስችለው አይነተኛው መንገድ ደግሞ የዋህ የኦሮሞ ወጣቶችን ለሁከት በማነሳሳት ክልሉን የግርግርና የህግ የበላየነት የማይከበርበት ቀጠና ማድረግ ነው።

የሰሞኑ የግድያና ንብረት የማውደም ተግባር የሚፈጸምበት ሁከት ምንጭና ዓላማ ይሄው ነው። እናም የኦሮሞ ወጣቶች በራሳቸው ላይ የመጡ ቡድኖች መሳሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ አለባቸው። መንግስት ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል የሚሏቸው ጥያቄዎች እንኳን ቢኖሩ፣ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንጂ በስሜታዊነት የሌሎች መሳሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ አለባቸው። የኦሮሞ ወጣቶች የመጣላችሁንና የመጣባችሁን ለዩ።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy