Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወሰን ሳይሆን የህዝቦች አንድነት ያለው ሥርአት

0 407

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወሰን ሳይሆን የህዝቦች አንድነት ያለው ሥርአት

ኢብሳ ነመራ

በዓለማችን ከ25 በላይ ሃገራት ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ሥርአትን ይከተላሉ። ከትላለቁቹ ሃያላን – አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሩሲያ ጀምሮ ከሳህራ በታች እስካሉት ናይጄሪያና ኢትዮጵያ በዚህ ፌደራላዊ ሥርአት የሚተዳደሩ ሃገራት ናቸው። ፌደራላዊ ሥርአት በሁለት እርከን የተከፋፈሉ መንግስታት የየራሳቸው ስልጣን ኖሯቸው የሚያስተዳድሩበት ሥርአት ነው። አንደኛው እርከን ማዕከላዊው ወይም የፌደራል መንግስቱ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ የክልል ወይም የግዛት መንግስታት ይኖራሉ። ሁለቱም የመንግስት አካላት – የፌደራልና የክልል/ግዛት መንግስታት በህገመንግስት የተደነገገ የየራሳቸው የስልጣን ድርሻ አላቸው። ኢትዮጵያ ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ ላለፉት 23 ዓመታት በዚህ ፌደራላዊ ሥርአት ስትተዳደር ቆይታለች – ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ (ኢፌዴሪ) ህገመንግስት መተዳዳር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ መሆኑ ነው።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 1፣ የኢትዮጵያ መንግስት ስያሜ በሚል ርዕስ ስር፤

`ይህ ህገመንግስት ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አወቃቀር ይደነገጋል። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ በሚል ስም ይጠራል` ይላል።

የህገመንግስቱ አንቀጽ 46 የፌደራል ክልሎች በሚል ርዕስ ስር፤

 

  • የፌደራሉ መንግስት በክልሎች የተዋቀረ ነው
  • ክልሎች የሚዋቀሩት በህዝብ አሰፋፋር፣ ቋንቋና ፍቃድ ላይ በመመስረት ነው

 

ይላል።

አንቀጽ 47 ደግሞ የፌደራል መንግስት አባላት በሚል ርዕስ ስር ክልሎችን ይዘረዝራል። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት፤ የትግራይ ክልል፤ የአፋር ክክል፤ የአማራ ክልል፤ የኦሮሚያ ክልል፤ የሱማሌ ክልል (በኋላ በክልሉ መንግስት ውሳኔ ስያሜው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንዲሆን ተደርጓል)፤ የቤኒሻንጉል/ጉምዝ ክልል፤ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፤ የጋምቤላ ህዝቦች ክልል፤ የሃረሪ ህዝብ ክልል ናቸው።

እነዚህ የፌደራሉ መንግስት አባላት የሆኑት ክልሎች ልክ እንደፌደራል መንግስቱ ሁሉ የህግ አውጪነት፣ ህግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ስልጣን ያላቸው አካላትን ያቀፈ ክልላዊ መንግስት መስርተዋል። የየራሳቸው ህገመንግስትም አላቸው። በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 51 እና 52 የፌደራልና የክክል መንግስታት ስልጣንና ተግባር ተወስኗል።

ሃገራት ፌደራላዊ ስርአት እንዲመሰርቱ የሚያደርጋቸው የየራሳቸው ታሪካዊ ሁኔታዎች አላቸው። አንዳንዶቹ የተለያዩ ሆነው ቆይተው በስምምነት በአንድ መንግስት ስር ለመኖር በመስማማት የተመሰረቱ ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ በልዩነት ውስጥ ያላቸውን አንድነት ለማጽናት የተመሰረቱ ናቸው። ኢትዮጵያም እንዲሁ ፌደራላዊ ሥርአት እንድትመሰርት ያደረጋት የራስዋ ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ አላት።

አሁን ኢትዮጵያ የምንላት ምድር ላይ የሚኖሩ ህዝቦች ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በአሃዳዊ ስርአት ስር ከቆዩ በኋላ ነው ፌደራላዊ ስርአት የመሰረቱት። ፌደራላዊ ስርአቱ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነታቸውን ያጸኑበት ሥርአት ነው።

ኢትዮጵያ የተለያየ ማንነት ቋንቋ፣ ባህልና ወግ፣ ታሪክ፣ ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ነች። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ በኋላ በኃይል ሃገሪቱን አንድ ያደረገው ዘውዳዊ ሥርአት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀድሞ ሲተዳደሩበት የነበረውን የየራሳቸውን ሥርአት አፍርሶ አሃዳዊ ስርአት መሰረተ። በአሃዳዊ ሥርአቱ ውስጥ የተካተቱት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን አስተዳደራዊ ሥርአት ብቻ አልነበረም እንዲያጡ የተደረገው። ማንነታቸው – ቋንቋ፣ ባህልና ታሪካቸው በህግ እውቅና ተነፍጎት ነበር። በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት ማግኘት፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማስተማር፣ ባህላቸውን የማሳደግ፣ እውነተኛ ታሪካቸውን የማውጣትና የመንከባከብ መብት አልነበራቸውም። በመሬታቸው ላይ የነበራቸውን የባለቤትነት መብትም ተነፍገዋል። በገዛ ሃገራቸው የህልውናቸው መሰረት የሆነውን መሬት ተነጥቀው ለገባር ጭሰኝነት ተዳርገዋል።

ይህ ጭቆና የብሄራዊ ነጻነት ትግል እንዲያካሂዱ የሚያስገድድ ነባራዊ ታሪካዊ ሁኔታ ፈጥሯል። ለአንድ ክፍለ ዘመን ባልተደራጀና ወቅታዊ ጉዳዮች መር የሆነ የተበታተነ ትግል ሲያካሂዱ ኖረዋል። ይህ የብሄራዊ ነጻነት ትግል ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ መልክ እየያዘ መጣ። በተለይ ከ1960ዎቹ በኋላ ወደ ተደራጀ የትጥቅ ትግል ተቀይሮ በ1983 ዓ/ም ዘውዳዊውን ሥርአት ተክቶ ሃገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረውን የወታደራዊ ደርግ አሃዳዊ ሥርአት አስወገደ። አሁን ያለው ፌደራላዊ ሥርአት በዚህ አሃዳዊ ሥርአት መቃብር ላይ የተመሰረተ ነው።

ቀደም ሲል የነበረው አሃዳዊ ሥርአት አመሰራረት ዓላማ ወሰን ማስፋት ነበር። ዓላማው የህዝብን – ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ጥቅምና ፍላጎት፣ መብትና ነጻነት ማረጋገጥ ሳይሆን፣ ወሰን በማስፋት መሬት ማግኘት ነበር። ለተስፋፊ ፊውዳላዊ ዘውዳዊ ሥርአት ሃገር ማለት መሬት ነው። በመሬቱ ላይ የሚኖረው ህዝብ የነገስታቱና መሳፍንቱ ተገዢ (subjuect) ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ለፊወዳል ገዢዎች ህዝብ ማለት የራሱንን መሬት እያረሰ የሚገብር ጭሰኞ፣ ጦርነት ሲመጣ የሚሰለፍ ተዋጊ ማለት ነው። ህዝብ መብትና ነጻነት እንዳለው ፍጡር አይወሰድም። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ በሄረሰቦችና ህዝቦች ያካሄዱት ትግል ይህን እውነታ በመቀየር ነጻነታቸውን የማጎናጸፍ ግብ ነበረው።

ወታደራዊው ደርግ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባካሄዱት የነጻነት ትግል ከተወገደ በኋላ፣ ሃገሪቱ የመበታተን ጠርዝ ላይ ደረሰች። ይሁን እንጂ ተገንጥሎ ነጻ ሃገር መመስረት መብትና ነጻነት ወደ ተከበረበት ሥርአት የሚያደርስ ብቸኛ አማራጭ ሳይሆን ከአማራጮች አንዱ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፣ በኃይልም ቢሆን አብረው በኖሩባቸው ዘመናት ያፈሯቸው መልካም የጋራ እሴቶች ላይ ተመስርተው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነትና በመከባባር የሚኖሩበት የጋራ ሥርአት የመመሰረት አማራጭን ለመሞከር ተስማሙ። እዚህ ስምመነት ላይ የደረሱት ያለአንድ የውጭ ኃይል አደራዳሪነት በራሳቸው ፍቃድና ውሳኔ ነበር። የፌደራላዊ ሥርአቱ ጥንስስ ይህ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስምመነት ነው። በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት ለመመስረት ምክንያት የነበረው ታሪካዊ ሁኔታ በአጭሩ ይህን ይመሰላል።

በዚህ አብሮ የመኖር ጥንስስ ሃሳብ መነሻነት፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ወዳለው ሥርዓት የሚያሸጋግራቸው ጊዜያዊ መንግስት መሰረቱ። የሽግግሩ መንግስት አብረው መኖር የሚያስችላቸውን የቃል ኪዳን ሰነድ የሚያዘጋጁበት ወቅት ነበር። በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አብሮ የመኖር የቃል ኪዳን የሆነውን ሰነድ – የኢፌዴሪ ህገመንግስት ቀርጸው አጸደቁ።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ የጠቀስኩት ህገመንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፍቃዳቸው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያለው ፌደራላዊ ሥርአት ለመመሰረት የገቡት ቃልኪዳን ነው። ፌደራላዊ ሥርአቱን ከቀደሙት አሃዳዊ ሥርአቶች የሚለየው ቀዳሚው ባህሪ በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍቃድ የተመሰረተ መሆኑ ነው። ሌላው መለያ ባህሪው በሃገሪቱ የወሰን የመሬት ሳይሆን የህዝቦች አንድነት እንዲኖር ያደረገ መሆኑ ነው።

ፌደራላዊ ሥርአቱ በብሄሮች ፍቃድ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት መፍጠር አስችሏል። ፌደራላዊ ሥርአቱ በሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍቃድ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ያለው በመሆኑ ምንም ውጪያዊ ኃይል ሊያፈርሰው አይችልም። የህዝብ ትስስር ውጤት በመሆኑ በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት በማጽናት የማይናወጥ ሥርአት መመስረት አስችሏል። ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር እንድትኖር ማድረግ የሚያስችል አሁን ካለው በህዝቦች አንድነት ላይ የተመሰረተው ፌደራላዊ ሥርአት የተለየ አማራጭ የለም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy