Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ ያተረፈ ማህበራዊ ልማት

0 391

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ ያተረፈ ማህበራዊ ልማት

ስሜነህ

ሃገራችን በአፍሪካ የንግድ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሏት እድሎች እየተፈጠሩ መሆኑን ብዙዎች እያመኑ፤ ምስክርነታቸውንም እየሰጡ ይገኛሉ። ይህም እምነት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መሆኑን የተመለከተ እና የውጭ ሃገር ባለሃብቶች በሃገሪቱ ለሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ስራ የሃገሪቱ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን የተመለከቱ እና ዴሞክራሲያዊም ልማታዊም ከመሆናችን ጋር የተያያዙ ናቸው። እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል።  

በኢትዮጵያ የመጣው ይህ እድገት በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ በውጭና በመንግሥት በኩል በተከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት አማካኝነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና እንደምትቀጥል፤ ከስድስት በመቶ በላይም ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን እንደምትገፋበት የሚያመላክቱት መረጃዎች ከመንግስት ብቻ የተገኙ ሳይሆን አለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የምጣኔ ሃብት፣ የምርምር እና የጥናት ማእከሎችም ያረጋገጡት እውነታ ነው ።

በሃገሪቱ እየታየ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እድገት የተለያዩ የውጭ ባለሃብቶችን ትኩረት እንዲስብ ካስቻሉ እና ከላይ ከተመለከቱት በርካታ ምክንያቶች በተጨማሪነት እና ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ውጤት የሆነው የመሰረተ ልማት እድገታችን ነው።

ሃገሪቱ ፈርጣማ ኢኮኖሚ ይኖራት ዘንድ በተለይ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርት፣ በኃይድሮ ፓወር፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በመሳሰሉት ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን ማግኘት ግድ ይላታል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በአስተማማኝነት የሚቀጥለውና ሃገሪቱም መለወጥ የምትችለው፣ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግና ማስተናገድ ሲቻል ብቻ ስለሆነ፡፡

በ2016 አፍሪካ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የቀነሰ ሲሆን የኢትዮጵያ 46 በመቶ ጨምሯል። ይህን የገለጸው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ድርጅት ነው። ድርጅቱ የአውሮፓውያኑን የ2017 ኢንቨስትመንት ትንበያን በተመለከተ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው  ሪፖርት እንዳመለከተው ያለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ማለትም ከጥር ወር 2008 እስከ ታህሳስ ወር 2009 ድረስ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መጠን ያለው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝታለች። ወደ አፍሪካ የፈሰሰው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን በ3 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ተቀባይ ሆና የቆየችው እና በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችው አንጎላ 2016 ላይ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን አሽቆልቁሏል። በአህጉሪቱ ትልቁን ኢኮኖሚ የያዙት ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያም በዚሁ ዓመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ግኝታቸው ቀንሷል። ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጠንካራ እድገት የታየበት እና ከዚህ ቀደም ያላየችው ነው ብሏል ተመድ በሪፖርቱ።

በ2016 የምስራቅ አፍሪካ 7.1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝቷል። ከዚህ ውስጥ ግማሹ የሚሆነውን የወሰደችው ኢትዮጵያ፤ በአጠቃላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከቀደመው ዓመት በ46 በመቶ እድገት አሳይቷል። ይህም አፈፃፀሟ በዓለም ላይ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ከሚገኙ አገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ የምታገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን እድገት የተቀጣጠለው አገሪቱ በመሰረተ ልማት እና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያዋለችው ያለው መዋዕለ ንዋይ ነው ይላል የተመድ ሪፖርት።

እንደ ሪፖርቱ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ በሚገኙ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቢያ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ነገር ግን አገራት የኢንቨስትመንት አማራጫቸውን ዓይነት አስፍተው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ባደረጉት ጥረት እየተሳካላቸው ነው ብሎም ኢትዮጵያን በምሳሌነት አስቀምጧል።  

በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች ያሉ ሲሆን፤ የሃገሪቱ የተረጋጋ ፖለቲካና ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ሰፊ የሰው ኃይልና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ በዋናነት የሚጠቀሱት ናቸው። ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲን የምትከተል በመሆኗ በኢነርጂው ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉም ሰፊ እድል አለ። በተለይ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ሃገራችን የሄደችባቸው ስኬታማ ርቀቶች የአለም የገንዘብ ተቋማትን አመኔታ እንድታገኝና የበለጠ እንድትተጋ የሚያስችላትን እድል ፈጥሮላታል።

በዚሁ መነሻም አገራችን ለህዝቦች በፍትሃዊነት የምታቀርበውን የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ለሚሰሩ ስራዎች ማስፈፀሚያ የሚውል 700 ሚሊዮን ዶላር በቅርቡ ከዓለም ባንክ ድጋፍ ያገኘች ሲሆን፤ በተጓዳኝ  ለገጠር የምግብ ዋስትና ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ 600 ሚሊዮን ዶላር በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር አግኝታለች። ይህም የሚያሳየው በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላት አመኔታ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት ጉዟችን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለማዳረስ በመቻሉ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ተቋማት ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችና 3ሺ 300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ27 ሚሊዩን በላይ ተማሪዎችን ማስተናገድ ተችሏል። በዚህም ታሪካችንን በልማታዊ አቅጣጫ መርተን መሰረታዊ ለውጥን ማምጣታችን ለሌላው ዓለም ምሳሌ መሆን የምንችልበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። የአንደኛ ደረጃ ተሳትፎን ከ96 በመቶ በላይ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኩልም በጥቂት አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን ስርጭት በማስፋፋት ተሳትፎውን ከ43 በመቶ በላይ ለማድረስ ተችሏል፤ በመሰናዶ ትምህርት ፕሮግራም ከግማሽ ሚሊዩን በላይ ተማሪዎችም በመማር ላይ ሲሆኑ በየዓመቱ ለከፍተኛ ትምህርት ተገቢውን ማለፊያ እያስመዘገቡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ወደ ሁለት መቶ ሺህ መድረሱን ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ድንቅ ውጤት ያስመዘገብንበትና በገንዘብ ተቋማቱ አመኔታን ያተረፈልን የጤናው መስክ ነው። የጤና ፖሊሲያችን በዋናነት በሽታን በመከላከል ላይ የሚያተኮር ቢሆንም ከዚሁ ጐን ለጐን መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን የማስፋፋቱም ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎችን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለማስፋፋት በተደረገዉ የተቀናጀ ርብርብ በ1983 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 153 ብቻ የነበረው የጤና ጣቢያዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ3ሺ 500 በላይ ደርሷል። ለ25ሺ ህዝብ አንድ የጤና ጣቢያ ለማዳረስ የተያዘውን ግብ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን የሚገልጹት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃዎች፤ የጤና ተቋማቱን አገልግሎት የማሻሻልና ግብአቶችን የማሟላት ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ያረጋግጣሉ።

በ1996 ዓ.ም ተቀርፆ ሥራ ላይ የዋለው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻልና በሽታን በመከላከሉ ስራ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክቷል። በመላ ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ የተሰማሩ ከ39ሺ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ባለቤትነት በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጐችን ለመፍጠር የተነደፈውን ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። በሁሉም የአገራችን የገጠር ቀበሌዎች ቢያንስ አንድ የጤና ኬላ የተገነባ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16ሺ 251 የሚበልጡ ጤና ኬላዎች ለህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የሆስፒታል አገልግሎት ለማሻሻልም የሃገራችን አቅም በፈቀደ መጠን ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በ1983 ዓ.ም 72 ብቻ የነበረው የሆስፒታሎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በግሉ ዘርፍና በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሰሩትን ሳይጨምር የመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ ቁጥራቸው በአራት እጥፍ አድጎ ከ310 በላይ ደርሷል።

ከላይ በተመለከተው መልኩ ሃገራችን ከአለም ባንክ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ በድጋፍና በብድር መልክ ልታገኝ የቻለችው መንግስት ትምህርትን፣ ጤናን፣ ግብርና፣ ንፁህ ውሃን እና የገጠር መንገድን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ እያደረገ ያለው መጠነ ሰፊ የልማት ጥረት እና በዚህም እየተገኘ ያለው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን በባንኩ መስፈርቶች መሠረት ማረጋገጥ በመቻሏ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለሆነም በዚህ ባለመዘናጋት ከዚህ ለበለጠ ድጋፍና እርዳታ በገንዘብ ተቋማት ዘንድ አመኔታን ሊያተርፉ በሚያስችል አግባብ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ እና ከኪራይ ሰብሳቢነት በጸዳ መልክ መፈጸም ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy