Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌስቡክ ጦረኞች

0 562

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌስቡክ ጦረኞች

(ተንጋለው ቢተፉ . . .)

                                       መዝገቡ ዋኘው

የቃላት ጦርነትና እስጥ አገባ ከሮና ገሮ ሲያበቃና ሲበጠስ ነው ሀገራት ወደ ጦርነት ውስጥ የሚገቡት፡፡ ለዚህም ይመስላል የቻይናው ከሚኒስት መሪ የነበሩት ማኦ ዜዱንግ ጦርነት የፖለቲካ ትግሉ በሌላ መልኩ ቀጣይነት ነው ያሉት፡፡ ማሕበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ የኃሳብ ፍልሚያ የሚካሄድባቸው ከጦርነት ያልተናነሱ አውድማዎች ናቸው፡፡ የማሕበራዊው ሚዲያ ጥይት ባይጮህበትም ከመድፍና ታንክ በላይ በሰው ሕሊና ውስጥ  የሚያጓራ ከሚሳኤልም በላይ ተምዘግዝጎ የሚወነጨፍ፣ የሚጮህና አናዋጭ፤ በስሜታዊነት የሚነዳ ለጥፋትም የሚያነሳሳ ነው፡፡ ፌስቡክ የኃሳብ ፍልሚያና ግብግብ የሚካሄድበት ጎራ መሆኑ በጀ እንጂ ሌላማ ቢሆን የከፋ እልቂትና ውድመት ሊያመጣ ይችል የነበረ የዘመኑ ሚዲያ ነው፡፡

ዛሬ ላይ አለምን ለጦርነት ስጋት እየጋበዛት ያለው በሚዲያ አማካኝነት የሚካሄደው ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ስራና የቃላት ፍልሚያ ነው፡፡ ኃሳብን በኃሳብነቱ በሰላም በስርአትና በጨዋነት መንገድ መግለጽ› ይቻላል፡፡ የፌስ ቡክ ቀጠና ግን ሕግና ስርአት የለውም፡፡ ልቅነት፣ መረንነትና ስርአተ አልበኝነት ሞልቶ የነገሰበት፣ እያንዳንዱ የራሱ አለም ንጉስ የሆነበት፣ የወደደውን የሚክብበት፣ የጠላውን ደግሞ የሚያጠለሽበት ነው፡፡ ዙሪያውን የተጠመደ ፈንጂ ያለ ይመስል በአንዲት ቃል ወይንም ሀረግ የተነሳ ሁሉም ቦታ መልኩን ቀይሮ ፍንዳታ በፍንዳታ ይሆናል፡፡

ማሕበራዊ ድረ ገጽ አዲሱ አይነት ሚዲያ ሲሆን በአብዛኛው በአንድ ጉዳይ ላይ የተዛቡና ስሜትን የሚለዋውጡ መረጃዎች በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመርኩዘው ሆነ  በፈጠራ በሀሰት ፍብረካ የሚሰራጩበት ነው፡፡ ጥላቻን በስፋት የሚያሰራጭ፣ የተሳሳተ መረጃዎችንም ጭምር የማስረጽ በፍጥነቱ በሰከንዶች አለምን መድረስ የሚችልም ነው፡፡

በፌስቡክ ዘመቻዎች በአጭር ቃላት የገዘፈ ስሜትን የሚያደፈርስ መልእክት፤ ክብረ-ነክ የሆኑ የሀሰት ስም ማጥፋት፤ አስነዋሪ ስድብ እንደ ወረደ የሚስተናገድበትም ነው፡፡ ለማንበብ ለሕሊናም ሰቅጣጭና ዘግናኝ የሚሆንበትም አጋጣሚ በዙ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠውን የመነሻ ኃሳብ ምክንያት በማድረግ ሺህ ትርጉም የሚመነዘርበት፤ ቀና ትርጉም የሌለበት፤ ሁሉም ያሻውን የሚፈላሰፍበት፣ የሚያላግጥበት፣ የስድብ ሱስና አራራውን የሚወጣበት፣ የአስተያየት ሰጪው ተክለ ሰውነትና ስብእናው ምን እንደሚመስል ጭምር በገሀድ የሚታይበት ውስጣዊ የባሕርይ ገመናን በአደባባይ በግላጭ አግጥጦና አፍጥጦ  እንዲወጣ የሚያደርግ ነው ፌስቡክ፡፡

ማሕበራዊ ድረገጾች በበለጸጉት ሀገራት የስለላ ተቋሞቻቸው ሰፊ የመረጃ ምንጭ ሲሆኑ በፈለጉት መንገድ ከየትኛውም ግለሰብ አካውንት ጭምር የሚሰበስቡበት ነው፡፡በተለይም አሸባሪዎችን ለመከታተል ይጠቀሙበታል፡፡ የግለሰቦች የግል አካውንቶችም ጭምር ከእይታና ከክትትል ውጪ አይደሉም፡፡ ተፈላጊውንም መረጃ ይሰበስባሉ፡፡

ማሕበራዊ ድረገጾች ለትምሕርት፣ ለእውቀት፣ ለጥናትና ምርምር፣ ለታሪክ፣ ለትኩስ አለም አቀፍ ዜናዎች ወዘተ ፈጣን መረጃዎችን የሚሰጡ፤ የበለጠ እውቀት ለማግኘት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ በእነዚህ ማሀበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት በቀላሉ በሚፈልጉት ርእስ ዙሪያ ሰፊና የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡

ድረ-ገፆቹ ጠቀሜታቸው የጎላ የመሆኑን ያህል አውዳሚና አጥፊ ጎንም አላቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ የወሲብ አፍቃሪና ሰለባ እንዲሆን በማድረግ ተተኪውን ትውልድ ወደጥፋት እንዲምዘገዘግ ያደርጉታል፡፡

በአለማችን ላይ አንድ ሰው ማወቅ ስለሚፈልገው ጉዳይ ኢንተርኔት ውስጥ ገብቶ በጎግል/Google ወይንም በያሁ/Yahoo ሰርች ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ በአሁኑ ሰአት ኢንተርኔት (በተለይም ማሕበራዊ ሚዲያዎች) አለምን ልክ እንደ አንድ መንደር አቀራርበውታል፤ይሁን እንጂ፣ የዛኑም ያህል አደጋነታቸው እየጎላ መጥቶአል፡፡

ፌስቡክን በመሳሰሉ ድረገጾች የእውነተኛም ሆነ የሀሰተኛ ዜና ስርጭቱ የፈጠነና የገዘፈ ነው፡፡ የጥፋት መልእክቶችን በማስተላለፍ፣ ጥላቻ በመዝራት፣ ስም በማጥፋት፣ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨቱም ስራ እንዲሁ ፈጣን ነው፡፡ ለበጎ ስራዎችና ተግባራትም በብዙ መልኩ ይውላል፡፡ አጠቃቀሙ ከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ግለሰቡ እንዲሰማው ከማድረግ ጀምሮ ጥንቃቄንም ይጠይቃል፡፡

ወደእኛ የፌስቡክ አጠቃቀም ታሪክ ስንመለስ በተለይ የኃሳብ ልዩነቶችን በማክበር የተለየ የሚባልን ኃሳብ ስርአት ባለው መልኩ የሚገልጹበት ሳይሆን ፖለቲካዊ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥላቻ ስድብ፣ የማናቆርና ሕዝብን ከሕዝብ የማባላት መረንና ልቅ የወጣና ከጨዋነት በእጅጉ የራቀ ዋልጌና መረን የሆኑ ዘለፋዎች፣ ስድቦች፣ በስፋት የሚስተናገዱበት፣ የሚጻፉበት መድረክ ሆኖ ነው የምናገኘው።

ልክ እንደ ክረምቱ በረዶና ጎርፍ፤ በፌስቡክ የአሉባልታና የስድብ ጋጋታ ይዘንባል፡፡ ከግለሰብ አልፈው ተርፈው ዘር እስከመስደብ ድረስ የተረማመዱ ዋልጌዎች የሚገኙበት መንደር ነው ፌስቡክ፡፡ ጎራው ሲታይ በመንግስት ደጋፊዎችና በተቃዋሚው የተከፈለ ይመስላል፡፡ እውነቱ ግን ይህን የተንቀለቀለ እሳት በኢትዮጰያውያን ስም እየተጠቀመ የሚያቀጣጥለው ትልቁን የማባላትና የማናከስ ስራ እየሰራ ያለው የኤርትራ መንግስት የደሕንነት ተቋም ነው፡፡

ይህ ሚስጥር ያልገባው ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጎሳየ ዘሬ ተሰደበ በሚል የለየለት የስድብ ጦርነት ውስጥ በመግባት አንዱ አደንኛውን ሲሰድብና ሲያንቋሽሽ ይውላል፤ ይህ እጅግ የተለመደ ሆኖአል፡፡ ተከባብሮ የኖረን ሕዝብ በዚህ መልኩ ማናከስ ማባላት ለሀገራችን በፍጹም አይጠቅማትም፡፡ ከዚህ አይነቱ አካሄድ መላቀቅ በመከባበር ሀሳብን መግለጽን ምክንያታዊነትን መከተል መልካም ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብም የራሳችን አኩሪ ባሕልና ጨዋነት ያለን ነን፡፡ በስርአቱ መናገር ማስረዳት የሀሳብ ልዩነትን ማንጸባረቅ ይቻላል፡፡ ስድብ ተወልዶ ያደገበት የተመነደገበትም ሀገር የሆንን ያህል የአስጸያፊ ስድቦች ብቸኛ ባለቤቶች ሆነናል፡፡ የስድብ ፋብሪካ ወደ መሆን የተሸጋገሩትም ብዙ ናቸው፡፡ ቀጣዩና ተተኪው ትውልድ ከዚህ ምን ይማራል? ቢባል መልሱ ምንም ነው፡፡

ፌስቡክም ሆነ ሌሎች ማሕበራዊ ሚዲያዎች በሌሎች አለማት እንደሚታየው ሁሉ ይልቁንም ለሀገርና ለሕዝብ ሰላምና አብሮነት የሚበጁ፤ ከስህተቶች መታረሚያ መውጫ መንገዶችን የሚያሳዩ፤ የድንቅ ሀሳቦች ማንሸራሸሪያ መድረኮች በመሆን ሲያገለግሉ የታያሉ።

ፌስቡክ ሲታሰብ በዚህ መልኩ ምን አይነት ትውልድና ሕብረተሰብ እየተገነባ ነው? የሚለውም ጥያቄ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የመንግስት ደጋፊ ነኝ የሚለውም ሆነ ተቃዋሚው በስድብ፣ በዘለፋ በስም ማጥፋት አልፎም ሕዝብን እስከመዝለፍና መስደብ ድረስ የተረማመዱ የተሸጋገሩ ጸያፍ ምልልሶችን በማድረግ ተጠምደዋል፡፡ ግለሰቦችንና ሕዝብን ያለመለየት ችግር ከባድ መዘዝን ያስከትላል፡፡ ድፍን ሕዝብን መስደብ በምን መስፈርት እንደሚቻል ለማሰብ ይከብዳል፡፡ ማሕበራዊ ሚዲያው ጨርቁን ጥሎ አብዶአል እየተባለ ያለውም በዚህና በዚሁ አሳሳቢ ጉዳይ ምክንያት ነው፡፡

ስንትና ስንት ለራስም ሆነ ለሀገር የሚበጅ ስራ በሚሰራበት ሰአት መሽቶ እስኪነጋ  ነግቶም እስኪመሽ ድረስ የጥላቻ ዘገሩን እየነቀነቀ ፌስ ቡክ ላይ ተጥዶ  ምላሱን ለስድብ አሞጥሙጦ እየጻፈ ስድብ ሲያዘንብ አንዱ ሌላውን ጥላሸት ሲቀባ ውሎ ያድራል፡፡ መቸም ጤነኛ የሆነ ሰው ያስበዋል ወይንም ያደርገዋል። ታዲያ የሄ የጤና ነው ያስብላል?

በፖለቲካው ጎራም ፌስቡክ የስድብ፣ የአሉባልታ የወረደ ተራ ወሬ መናሀሪያ የጥላቻ መስበኪያ ሕዝብን መንቀፊያ መስደቢያ ከሆነ ውሎ አድሮአል፡፡ ጥያቄው በዚህ መልኩ በስድብ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በሀገር ደረጃ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ይቻላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይህ መንገድ የባሰ መተናነቅን የባሰ ጥላቻን የመጠፋፋት አቅጣጫን ይበልጥ እያሰፋ መቻቻልና መከባበር መደማመጥ የሚለውን እየናደና እያወደመ ሀገሪትዋን ወደማይፈለግ የጥፋት አቅጣጫና እልቂት ከመምራት ውጭ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋትን አይፈጥርም፤ ይህን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል።

ይህ እንዲሆን ችግር እንዲፈጠር ማሕበራዊ ሚዲያውን ተጠቅመው ሕዝብን ከሕዝብ የማናቆር የማባላት የማለያየት አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳ ግጭት እንዲፈጠር ሰላም እንዲደፈርስ በአጠቃላይ ሀገሪትዋ የቀውስ ማእበል ውስጥ እንድትወድቅ ቀን ከሌሊት የሚሰሩ እንቅልፍ አጥተው የሚንቀሳቀሱ ልማትና እድገታችንን የማይፈልጉ ጠላቶች እንዳሉን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡

በግብጽና በኤርትራ የደሕንነት ኃይሎችና ቁጥጥር ስር ሁነው በኢትዮጵያዊነት ስም እየተጠቀሙ በፌስ ቡክ አካውንታቸው ከፍተኛ የማባላት ስራ የሚሰሩ የመንግስት ደጋፊ መስለው ሕዝብን ከሕዝብ በማናከስ ስራ የተጠመዱ በጠባብነት በትምክሕት የአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ የሚዋኙ እንዳሉም ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ግዜው አርቆ ማስተዋልን፣ ስለሀገርና ስለሕዝብ ሲባል ችግሮችን ሁሉ በመደማመጥና በመከባባር ልዩነትን በልዩነት ይዞ በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆምን የሚጠይቅ ነው፡፡

በፌስቡክ መንደር ውስጥ መሽገው የሚንከላወሱ ከእኛ በላይ አዋቂ የለም ለማለት የሚዳዳቸው፤ አስተሳሰበ ደካማዎች የሚጽፉትንና የሚለጥፉትን ተጠንቅቀው ለማስተዋል ቢችሉ በሀገርና በሕዘብ ላይ ችግር ከመፍጠር ቢቆጠቡ ሀሳቦችን በጨዋ መልኩ ቢገልጹ ተጠቃሚው ሕዝብም መንግስትም ነው፡፡ ከስድብና ከጥላቻ ፖለቲካ የሚገኝ ትምሕርትም ሆነ ትርፍ የለም፡፡

አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል ሆነና ትናንሽ አስተሳሰብ ያላቸው ፍጡራን ስለትልቋና በታሪክ ውስጥ ስለከበረችው ዛሬም ወደትልቅነት እንደገና በመረማመድ ላይ ስላለችው በአለማችን የሰው ዘር መፍለቂያና መገኛ የታላላቅ በአለም ደረጃ የተመዘገቡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች፤ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት፤ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችም እናት የሆነችውን ሀገር ሕዝቡን እርስ በእርሱ አባልተው ሊያፋጁት በዚህ ትርምስ መሀልም ለኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ መሳሪያ ሁነው ሀገር ለማጥፋት ሲክለፈለፉ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቶአል፡፡

ያላወቁት ትልቅ ነጥብ በየትኛውም የታሪክ ወቅት ጥንትም ዛሬም ሀገሩን ከየትኛውም አይነት ሴራና ደባ ጠብቆ አንድነትዋ ሳይፈርስና ሳይናጋ ያኖራት ሕዝቡ መሆኑን ነው፡፡ የፌስቡክ አርበኞች በወሬና በስድብ የሚጋጭ የሚባላ በአሉባልታ ለዘመናት የኖረና ዛሬም ድረስ የዘለቀ አንድነቱን የሚያፈርስ ሀገሩን ለውጭ ጠላቶች መፈንጪያነት አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝብ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ሳይለያይ አብሮነቱን አንድነቱን ጠብቆና አጽንቶ የሚዘልቅ ብዝሀነቱ ውበቱና ድምቀቱ እንጂ የመለያያ ነጥቡ እንደማይሆን ወደ ኋላ ሄደው ታረክን ቢፈትሹ ይመረጣል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy