Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፕሬዚዳንቱ ንግግርና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራችን

0 676

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፕሬዚዳንቱ ንግግርና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራችን

                                                     ደስታ ኃይሉ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በ5ኛው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሶስተኛው የስራ ዘመን የጋራ የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ስለ አገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማውሳታቸው ይታወሳል።

በዚህም የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እየጎለበተ መሆኑን አውስተዋል። በዋነኛነት ዴሞክራሲን ከማጎልበት አንፃር የፌዴራል ዴሞክራሲ ሥርዓቱን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችሉ አዋጆችና ፖሊሲዎችን ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ መብታቸውን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩባት፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያልታየበት፣ ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ ያልታሰበባት ሀገር፤ ዛሬ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘርግታ ይህን የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ጉዞ ማየቷ ማንኛውንም ዜጋ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም።

ታዲያ ይህን የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ በተለይም ዴሞክራሲን ለማጎልበት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሚዲያና ሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል። እንደሚታወቀው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው ምርጫ ነው፡፡

የምርጫ ጠቀሜታም ሕዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ፣ በተጨባጭ በምረጡኝ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፖርቲዎች ያከናወኑትን ወይም የሚያከናውኑትን  ተግባር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የእገሌ ፖርቲ በቀጣይ ለውጥ ያመጣልናል ብለው ያመኑበት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላንዳች ተጽዕኖ ካርዳቸውን በመስጠት ተመራጩን ፓርቲ ለስልጣን ማብቃት ነው፡፡

ይህም በህገ-መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በሕዝብ ድምፅ  እንጂ በሌላ መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ያስረዳናል፡፡ የፖለቲካ ፖርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ይህን ዕውነታ ተረድተው የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ግና እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ 26 ዓመት ብቻ የስቆጠረ ለጋ በመሆኑ፣ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድና እንከን አልባ ርብርብ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም መሰረታዊ የዴሞክራሰ ተግባራትን በማከናወንና ዴሞክራሲው እንዲጎለብት ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል፡፡

እንደሚታወቀው ባለፋት ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስርዓትን በሂደት እየገነባን መጥተን፣ ድህነትን ለማሸነፍ ባደረግነው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት አግኝተናል፡፡ ሆኖም ልዩነታችን አንድነታችን ሆኖ ካልቀጠለ፤ በመነቋቆርና በመነካከስ ከቀጠልን እንደዚህ ቀደሙ ለዘመናት ወደ መጣንበት የድህነት አረንቋላ መዘፈቃችን አይቀርም፡፡ እናም ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ የሚሆነው ለዚሁ ነው፡፡

እርግጥ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ሊረጋገጥ የሚችለው በመጎልበት ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ያለ አንዳች እንቅፋት ሳይሸራረፍ ሲቀጥል ነው፡፡ እናም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን መጠናከርና ማበብ ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡

መንግስት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት የዘወትር ፍላጐቱ መሆኑ ነው፡፡

የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል። ተቃዋሚዎቹ ግን ይህን የተዘጋ ዶሴ ከ26 ዓመት በኋላ አዋራውን አራግፈው ሊጠቀሙበት የፈለጉ ይመስላል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምህዳር ግን ይህን ዶሴ የሚያስተናግድበት ቦታ ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ምናልባትም ገዥው ፓርቲና መንግስት ‘ከስልጣናችን ቆርሰን እንስጥ’ ቢሉ እንኳን ስርዓቱ ይህን እንዲያደርጉ የሚፈቅድላቸው ስላልሆነ ነው።

እንደሚታወቀው በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ አንድ በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባር የህዝብን ውክልና መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። ህዝቡ የሚፈልገውን ለማስፈፀም እንጂ እርሱ የሚፈልገውን ነገር በህዝቡ ላይ ለመጫን አይደለም።

ምናልባትም የራሱን ፍላጎት በህዝቡ ላይ ለመጫን ካሰበ፣ ህዝቡ በፓርላማ አማካኝነት የሰጠውን የመተማመኛ ድምፅ ሊነጥቀው ይችላል። እናም ከዴሞክራሲ አኳያ የገዥ ፓርቲ ማናቸውም እንቅስቃሴ ከውክልና ጋር የተያያዘ ብቻ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ህዝብ ከሰጠው ውክልና ውጭ ሆኖ ስልጣንን ለሌላ ፓርቲ ሊያጋራ አይችልም። መብትም የለውም። ህዝቡ በ2007 ምርጫ ወቅት የሰጠውን ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ውክልና ችግር ስለገጠመው ብቻ ሸርፎ ለሌላ ፓርቲ የሚሰጥበት ምንም ዓይነት ህጋዊ አመክንዩ ሊኖር አይችልም።

ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ከላይ እንደጠቀስኩት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ፣ ስልጣንን ከመጋራት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።

ዴሞክራሲ ጊዜንና የአስተሳሰብ ልህቀትን ይጠይቃል። በእንድ ጊዜ የሚተገበር አይደለም። ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል። እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል። ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል።

ዴሞክራሲ በመወያየት፣ በመቻቻልና ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አኳያ አንደኛው ለሌላኛው ሃሳብ ተገዥ የሚሆንበት አውድ እንጂ፤ “የግድ የእኔን ተቀበሉኝ” በሚል ግትር አቋም ሃሳብን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት መድረክ ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ዴሞክራሲ ሲያስቡ ይህን እውነታ በተጠያቂነት መንፈስ ማገናዘብ አለባቸው። እናም ፕሬዚዳንቱ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ይከናወናሉ ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉም ገንቢ ሚናውን ማበርከት አለበት።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy