ዴሞክራሲ የተለያዩ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት የደራ ገበያ ነው
ስሜነህ
ብዝሃነት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ ይቅርና የኢትዮጵያ ህዝብ በርካታ መብቶቹ በተረጋገጡበትና መተንፈሻ እንኳ በታጣበት በዚያ ዘመን ችግሮቹን ሁሉ ተቋቁሞ ያለፈው የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአመለካከትና የመሳሰሉት ልዩነቶችን አክብሮ የመኖር የዘመናት ልምዱን ተጠቅሞ መሆኑ ይታወቃል።
የሃገራችን እና የህዝቦቿ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑት ውስጥ ጨዋነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ የመከባበር እና የመመካከር ባህላችን፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት የቆየ ልምድና ለሃገር ሽማግሌዎች የምንሰጠው ቦታ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ የማይዳሰሱ እና አኩሪ የሆኑቱ እሴቶቻችን ከምንም በላይ ሃገራችንን በጋራ ለመጠበቅና የሃገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ያገለገሉን ዋነኛ መሠረቶች ናቸው። ሌላውና የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ አክብሮት ከሚያገኝባቸው ተምሳሌታዊ እሴቶቹ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው አገር ወዳድነቱ ነው። ይህ ለቅኝ አገዛዝ ያልተንበረከከ የአገር ፍቅር ፅናት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ባሉት ለየት ያሉ እና ከላይ በተመለከቱት ተምሳሌታዊ እሴቶቹ ነው።
መንግስትም ሆነ መንግስትን የሚመራው ፓርቲን ጨምሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያስፈልጋል ሲሉ፣ በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች የመደራጀት መብታቸውን ተጠቅመው ፓርቲ በማቋቋም በምርጫ ብቻ የመንግሥት ሥልጣን መጨበጥ መቻልን ተቀብለው እና አምነው መሆኑ አያከራክርም። የሥልጣን ምንጭ የሆነው ሕዝብ የሚፈልጋቸውን ወኪሎች በነፃነት መርጦ ለሥልጣን የማብቃትን ብቸኛና ዴሞክራሲያዊ አማራጭ አምነውና ተቀብለው እንጂ በአመጻ ቆርበው እንዳልሆነም መገመት አይከብድም።
የሃገራችን ህዝቦች መንግስትንም ሆነ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና አክቲቪስቶችን ይልቁንም ማህበራዊ ሚዲያውን እና ዴያስፖራ ተቃዋሚዎችን መዳኘትም ሆነ መስማት ያለባቸው በነዚሁ ህጋዊ ማእቀፎችና ከላይ በተመለከቱት አኩሪ እሴቶቹ ውስጥ ሆኖ ሊሆን የሚገባ መሆኑ ላይ ልዩነት የሚኖረው አካል ይኖራል ብሎ ለመገመት ይከብዳል።
ይህ ማለት ግን ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት ሲያጠፉ እና ይልቁንም አክብረው እንዲያስከብሩ የሚጠበቅባቸውን የህግ ማእቀፎች ሲጥሱ ህዝቡ ዝም ብሎ ሊመለከት ይገባዋል ማለት አይደለም። ከላይ የተመለከቱትን አኩሪ እሴቶቹን ይዞ በተቀመጠለት የህግ አግባብ የመጠየቅ፤ በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉ መብቶቹንም በሙሉ አሟጦ የመጠቀምና ወጥሮ የመያዝ መብት ያለው መሆኑን የሚያጠይቅ ነው።
በመንግስትም ሆነ በመሪ ድርጅቱ በኩል በተለይ አሁን በየአጋጣሚው ለሚነሱ ቅሬታዎች እና ሮሮዎች ዋነኛው ምክንያት “የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲውል ከማድረግ ይልቅ፣ ከግል ብልፅግና አንፃር፣ የግል ኑሮን መሠረት አድርጎ የመመልከት በአንዳንዶቹም ዘንድ የግል ጥቅምን ከማስቀደም ጋር የተያያዘ ነው፤” በሚል ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎች ምንጭም ይኼው ያልተገባ ድርጊት የፈጠረው ችግር መሆኑ ተመልክቷል።
ከዚህ በመነሳት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግሥት ሥልጣንን ያላግባብ ለግል ኑሮ መሠረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌ መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ዕርምጃዎችም መውሰድ እንደሚገባ በወሰነው አግባብ ስራውን እየሰራ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለዚህም ከክልል መንግስታት ጀምሮ በፌደራሉ መንግስት የተጀመሩት እና በርካቶችን ለወህኒ ቤት ያበቁት እርምጃዎች ሁነኛ ማሳያ ከሆኑት ውስጥ ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ይህም ሆኖ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች የኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳቸውን እና የጽንፈኛ አክራሪነት ግባቸውን የሚዘጉ መንገዶችን ሁሉ ለማስከፈት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ በየአጋጣሚው እየተስተዋለ ነው። በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል በተነሳው ግጭትና የግጭት አፈታት ሂደት ላይ የታየው ይህ ነው። በፌስቡክ አብዮት ተጠርቶ በነበረው የስራ ማቆም አድማ ላይም የነዚሁ ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮች እጅ ያለበት መሆኑ አያጠያይቅም።
በኦሮሚያም ሆነ ሌሎቹ ክልሎች በመልካም አስተዳደር እጦት የተለበለበ ህብረተሰብ የሚያሰማቸው የተቃውሞ ድምጾች ሊደመጡ ይገባል። ያም ሆኖ ግን እነዚህን ጥያቄዎች ከላይ በተመለከቱት እሴቶች ማእቀፍ ውስጥ ማሰማት ካልተቻለ የኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች እጅ የበረታ መሆኑን ያጠይቃል። ይህ አይነቱ አካሄድ ህገወጥነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ምናልባትም ለእለት ትርፍ ጽንፈኞቹን፤ አክራሪዎቹን እና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎቹን ካልጠቀመ በቀር በማናቸውም መልክ ሃገርና ህዝብን የማይጠቅም ይልቁንም የሚያወድም መሆኑ ሊታወቅና በአጽንኦት ሊያዝ የሚገባው ይሆናል።
በዴሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ ያለው ብቸኛ አማራጭ የመንግሥት ሥልጣን ከፓርቲዎች ወደ ፓርቲዎች የሚሸጋገረው በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው። አገር ሰላም ሁሉም ጤና የሚሆነውም በዚሁና በዚሁ መንገድ ብቻ ነው። ከላይ የተመለከቱት የጋራ እሴቶች ከህገ መንግስታዊ መንገዶች ባሻገር ልዩነታችንን በብልሃት እየፈታንና አንድነታችንን እያጠናከርን እንድንዘልቅ የሚያደርጉ መሆናቸው ከላይ በተመለከተው አግባብ ተረጋግጧል። ስለሆነም በውስጣችን የነበሩት እና ያሉት ጨዋነትና አርቆ አሳቢነት ልዩነትን ላከበረ አንድነት ምሰሶዎች ሆነው እንዲቆዩ እንጂ በየአጋጣሚው የማንም መቀለጃ እንዲሆኑ መፍቀድ አይገባም። እርስ በርሱ እየተከባበረና እየተመካከረ ልዩነቱን በአንድነት መንፈስ እያሸነፈ የኖረ ህዝብ በልዩነት ውስጥ አንድነትን፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነትን በተግባር ያፀናውን ሕዝብ ለሚመስል ምግባር ሊተጋ ይገባዋል እንጂ የጥቂቶች መቀለጃ መሆን በእርግጥም ሊያበቃ ይገባዋል።
በአሁኑ ጊዜ ከጨዋነት ጋር የማይመጋገቡና የሰዎችን መብት የሚዳፈሩ አሳሳቢ ድርጊቶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው። ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ፈተና ውስጥ ከወደቀባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው በመንግሥት አማካይነት የሚፈጸመው መሆኑ ላይ መንግስት አምኖ የመታረም እርምጃ ውስጥ ገብቷል። ያም ሆኖ ግን የተለየ ሃሳብን ያለማክበር ብሎም በጠላትነት የመፈራረጅ አባዜ በነፃነት ማሰብ የሚፈልጉ ዜጎችን እያሳቀቀ፤ አንተም ተው አንቺም ተይ ሊሉ የሚገባቸውን ሽማግሌዎችና ልሂቃንም ከየአደባባዩ እያራቀ ይገኛል።
በሃሳብ መለያየት ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ስለሆነም ለምን ተቃራኒ ሃሳብ እንሰማለን የሚሉ አምባገነኖች ግባቸው ኪራይ መሰብሰብ መሆኑን ተረድተን ልንታገላቸው ይገባል። መሃል ቆሞ አያገባኝም ማለት የሚቻልበት ሰዓት አሁን አልፏል። የነዚህ ሃይሎች ትከሻ ቀስ በቀስ እየፈረጠመ፤ የከፋ አደጋውም ከወዲሁ እየሸተተ ነውና አደባባይ ማውጣትና ማጋለጥ አሁን ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።
ሃሳብን ከመገደብ እና እነርሱ ያሉትን፣ በየድረገጹ የሚጎርፈውን ናዳ ከመመልከት የዘለለ አብዮት አሁን ያስፈልጋል። የማህበራዊ ሚዲያዎቻችን “ጀግኖች” ሰዎች በተናገሩ ቁጥር በሌላ ሃሳብ ከመሞገት ይልቅ ማንነትንና ሰብዕናን በሚያዋርድ ስድብ ማሳቀቃቸውን ሊያቆሙ ከተገባ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው። ዴሞክራሲ የተለያዩ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት ገበያ ነው ሲባል፣ ከየትኛውም አካባቢ የሚነሱ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ዕድል ይኑራቸው ማለት ነው። የሰዎች ሐሳብ በድጋፍና በተቃውሞ ውስጥ እየተቀረቀረ እንደ ስሜቱ ልክ ማሞገስና ማዋረድ ኢምክንያታዊ ከመሆኑም በላይ ከላይ ከተመለከቱት ምግባሮቻችን ያፈነገጠና ህገወጥነት ነው።
ይህ የሕዝባችንን የጋራ እሴቶች የማይወክልና ከተራ የፖለቲካ ፍጆታ የማያልፍ አጓጉል ፍረጃ ለአገር የማይበጅ ከመሆኑም በላይ፣ ቅን ዜጎችን የአደባባይ ሰዎች እንዳይሆኑ በማድረግ የአዳጋውን ቀን እያቀረበው ነው። ስለሆነም ዴሞክራሲን ከሃሳብ ገበያነቱ ባሻገር የሚመለከቱ ሃይሎችን በግልፅ ልናወግዝ፣ ልንታገልና ልንፋረዳቸው ከተገባ ጊዜው አሁን ነውና አደባባዩ ላይ ሁሉም ወጥቶ ፊት ለፊት ሊተናነቃቸው ይገባል።
ሠላም ለሠው ለጅ በአማራጭ የማይቅብ አየር ነው