Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዳዩ የሁለቱ ክልሎች ብቻ አይደለም!

0 789

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዳዩ የሁለቱ ክልሎች ብቻ አይደለም!

                                                     ዘአማን በላይ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የድንበር አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ የሁለቱ ክልሎች ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ለተፈጠረው ግጭት ዋነኛ መፍትሔ በመሻት ለስራ ተነሳስቶ የሀገሩን ልማት ለማሳለጥ ደፋ ቀና የሚለውን የሁለዩን ክልሎች ህዝብ መደገፍ መቻል ይኖርብናል። በመሆኑም ለግጭቱ መፍትሔ በመሻትም ይሁን በሁለቱም ክልሎች በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን መርዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነትና ባህላዊ ትውፊት በመገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ መስራት የሁሉም ዜጋ ድርሻ ይሆናል።

እንደሚታወቀው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ የህዝቦች የሰበብ አስባብ ግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም።

የጋራ ወግ፣ ባህልና ትውፊት ያላቸው፣ በዘመናት አብሮነት ገመድ የተሳሰሩ፣ በተለይም አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ገንብተው የማየት ራዕይ ያላቸው የሁለቱም ክልል ህዝቦች በጥቂቶች ፍላጎት እንዲህ በቀላሉ ሊለያይ የሚችል አይደለም። በፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውስጥ አገራዊ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታን ለማስረፅ ከ23 ዓመታት በላይ አብረው በመፈቃቀድ ኖረውና በአገራችን ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ የራሳቸውን አሻራ በማኖር ላይ ያሉት ወንድምና እህት ህዝቦች በጥቂት ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ፍላጎትና ሴራ ሊፈቱ አይገባም።

ሀገራችን ሰላም ሆና በህዝቦቿ ተሳትፎ እንዳታድግና ወደ ህዳሴዋ እንዳትግሰግስ የማይሹ ፅንፈኛ ኃይሎችና የውጭ አጋሮቻቸው ሰለባ ላለመሆንም የየክልሎቹ አመራሮች ከህዝባቸው ጋር በመሆን ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ለዚህ ደግሞ በሁለቱም ወገን ያለው አመራር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅድሚያ የህዝቡን ድምፅ መስማት፣ ለጥቆም ቁርጠኛና አሳታፊ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበትን አካሄድ መከተል ይኖርባቸዋል።

ሀገራችን የምትከተለው ፌደራላዊ ስርዓት አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ ነው። በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች የተዋቀረም ስርዓት ነው። እናም አገራችን ውስጥ ለግጭት የሚሆን ስፍራ እንደሌለ ግጭት አራጋቢዎቹ ሊያውቁት ይገባል። ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች  

 

ያም ሆኖ ግጭትን የሚያራግቡ ሃይሎች ለልማት በመትጋት ላይ በሚገኘው ወጣት እጅ እሳት ለመጨበጥ በበሞከር የሚያረጉት ሴራ አንድ ቦታ ላይ መቆም ይኖርበታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የበላይነት መያዝ ያለበት የልማታዊ አስተሳሰብ እንጂ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል አኮኖሚ የበላይነት ባለመሆኑ ነው።

 

በኮንትሮባንዲስቶችና በኪራይ ሰብሳቢዎች አሉባልታ እንደ ቦይ ውሃ የሚነዳ ህዝብም ሆነ መንግስት አለመኖሩን ማወቅ የሚገባ ይመስለኛል። ርግጥ የፀረ-ሰላም ኃይሎቹ አሉባልታ የሰላም ወዳዱና ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድነት የማደግ ፍላጎት ያለው የኦሮሞም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ አጀንዳ አይደለም።

የሁለቱ ህዝቦች ፍላጎት ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በመተሳሰብና በመደጋገፍ በጋራ የመልማት፣ ከአጎራባች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲሁም ባደረገው መራር ትግል ዕውን እንዲሆን ባስቻለው ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩት መብቶቹ ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩላቸው ነው።

በግጭት አራጋቢዎች አሉባልታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤ ሴራው ሆን ተብሎ ሁለቱ ህዝቦች አገራዊና ክልላዊ ተጠቃሚነት ለማደናቀፍ እንዲሁም በትግል ያገኛቸውንና እያጎለበታቸው የሚገኙትን ሁለንተናዊ ህገ-መንግስታዊ መብቶቹን ለመሸርሸር ብሎም ህዝቡ ተረጋግቶ በልማት ስራው ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ የታለመ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ባለፉት ዓመታት በተጎናጸፏቸው የልማትና የዕድገት ዕድሎች በብቃት በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል። በህዝቦች ይሁንታ የተመሰረተው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መገንባት ከጀመረበት ወዲህ በሁለተም እየታየ ያለው ለውጥ ከፍተኛ ነው።

ከለውጦቹ መካከል በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በተመዘገቡ ለውጦች አጠቃላይ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አሃዝ እንዲያድግ አስችሏል። በዚህ ሂደት ውሰጥ የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊነትና ባለቤትነት ነበር። ያለ ህዝቡ ይሁንታና ፈቃድ የተከናወነ ነገር የለም፤ ሊኖርም አይችልም።

ዳሩ ግን የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ግጭት አራጋቢዎች ሁሌም በክልሉ ላይ በማተኮርና በሽብርተኝነት ከተፈረጁ እንደ ኦነግ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በጸረ ሰላም ሚዲያዎች የሀሰት ወሬ በመንዛት ሁከት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። የሰው ህይወትም አጥፍተዋል።

እነዚህ ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ሽብርተኛው ኦነግ ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው ናቸው። በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት የሁለቱ ክልል ህዝቦች የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት ሲያደርጉ አድርገዋል። ግና ጊዜያዊ ችግር ከመፍጠር በዘለለ ሌላ የሚሳካላቸው ነገር አይኖርም።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሁለቱ ክልል ህዝቦች በተፈጥሮ በተቸራቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ለዘመናት ተነፍጎ ከኖረበት ሁኔታ ራሳቸውን በማላቀቅ ዛሬ ላይ ቋንቋቸው የሳይንስ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የእድገት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል። ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆንም ባካሄዱት መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በማምጣት የየክልላቸውን ህዝቦች በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

ይህ በክልሎቹ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት የሚያሳበዳቸው እነዚህ ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የልማቱን ግስጋሴ ባዩ ቁጥር እንዲሁም መንግስት በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃን ሲመለከቱ ጥቅሞቻችን ከመቃብር በታች ይውሉብናል በሚል ስጋት የሞት ሽረት ትግል ማድረጋቸው የማይቀር መሆኑን በገሃድ አሳይተዋል። በቅርቡ በኢሉባቡር ቡኖ በደሌ አካባቢ የታየው የንፁሃን ህዝቦች እልቂት የዚህ አባባሌ መገለጫ ነው።  

ጥቅማችን ይነካል በሚል ስጋት ግጭትን በማቃጠል ስራ ላይ የተጠመዱት እነዚህ ኮንትሮባንዲስቶችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በሁለቱም ክልሎ ውስጥ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ቢያደርጉም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በግጭቱ የተጎዱት የሀገሩ ዜጎች በመሆናቸው የችግሩ መፍትሔ መሆን አለባቸው።

ችግሩ የሁለቱ ክልሎች ብቻ አይደለም። በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኘው ህዝብ እንደ ሌሎቹ የሀገራችን ህዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓትን ለመገንባት በህገ መንግስቱ ቃል የገባ ነው። የእነዚህ ህዝቦች ችግር ውስጥ መግባት ይህን ሀገራዊ ራዕይ ሊያስተጓጉለው ይችላል። እናም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ ከሁለቱም ክልሎች በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን በመርዳት ኢትዮጵያዊ ባህሉን ከማሳየት ባለፈ ግጭቱ ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ የመፍትሔው አካል መሆን ያለበት ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy