Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉድለቶችን የሚያርሙ መፍትሔዎችን የያዘ ሥርዓት

0 324

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉድለቶችን የሚያርሙ መፍትሔዎችን የያዘ ሥርዓት

                                                      ደስታ ኃይሉ

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት እንደ ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት ሊያጋጥሙት የሚችሉትን ጉድለቶች መሙላት የሚችል የመፍትሔ ሐሳቦችን ያሉት ነው። ሥርዓቱ በየትኛውም ሁኔታ ለሚፈጠሩ ወቅታዊ ክስተቶች ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ የአገራችን መተኪያ የሌለው አማራጭ ነው። ማናቸውም ወቅታዊ ተግዳሮቶች ከሥርዓቱ በላይ ሳይሆኑ በእንጭጩ መቀጨት የሚችሉ ናቸው።

 

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው።

 

ይህ የሀገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህም ይመስለኛል— ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችብን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

 

ያም ሆኖ ያለፉት ሥርዓቶች በህዝቦች መካከል የፈጠሩት የተዛባ ግንኙነቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት እጥረቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚታዮ ግጭቶች መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው አይካድም። እርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ይመስለኛል።

እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በሥልጣኔ በገፉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ ነባራዊ ክሰተት ነው። በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚመላለሰው የሰው ልጅ ቀርቶ ህይወት የሌላቸው ግዑዛን ነገሮችም በተፈጥሮ እንቅስቃሴ ሳቢያ ሊጋጩ ይችላሉ።  

እርግጥ ከሰው ልጅ ግጭቶች አኳያ በዓለማችን ላይ የተፈጥሮ ሀብት እጥረት መኖሩ እንደ መንስዔ የሚታይ ነው። ሀገራችንም ከዚህ የተፈጥሮ ዕውነታ ልትርቅ አትችልም— እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባትና። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

ይሁን እንጂ ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ይህን ዕውን ለማድረግም ሥርዓቱ አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ እየሰራ ይገኛል።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያለፉ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማረም በሚያደርገው የእኩልነትና የፍትህ ተግባራት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። የተዛቡ የህዝቦች ግንኙነቶችን በማስተካከል በሚደረጉ የፍትህና የእኩልነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለፉትን ስርዓቶች በመናፈቅ አሊያም በዚያኛው ዓይነት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሀገራችን እንድትመራ የሚፈልጉ አካላት ግን ይህን ሁኔታ ሊገዳደሩት ይሞክራሉ—ምንም እንኳን ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ለዚህ የሚሆን መፈናፈኛ ባይሰጣቸውም።

እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ አላቸው።

የአገራችን ህዝቦች መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሐዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ በህገ መንግስቱ ገልፀዋል። ላለፉት 26 ዓመታት እያከናወኑት የመጡትም ይህን እውነታ ነው።

ምንም እንኳን ያለፉት ስርዓቶች በህዝቦች መካከል የተዛቡ ግንኙነቶችን ፈጥረው ቢያልፉም፣ ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በእኩልነትና በፍትህ ዴሞክራሲያዊ መንገዶች እነዚህ ችግሮች እየተቀረፉ ነው።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወቱና ፍትህንና እኩልነትን ከማጠናከር አኳያም ረጅም ርቀት ተጉዟል። እርግጥ ሥርዓቱ ራሱን እያረመና እንደ ማንኛውም ጀማሪ የፌዴራል ስርዓት ያሉበትን ችግሮች እየነቀሰ እንዲሁም ካለፉት ክስተቶች እየተማረ በሀገሪቱ ህዝቦች በመታገዝ በአስተማማኝ መንገድ ላይ ይገኛል። ለየትኛውም ተግዳሮት ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ ነው።

እንደ እኛ ያሉ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገራት ከፌዴራሊዝም የመንግስት አወቃቀር ስርዓት ውስጥ፤ ለሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሶችና ህዝቦች ህገ መንግስታዊ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንና ውክልናን ማረጋገጥን፣ የውጭ ጥቃትን በጋራ መመከትን፣ ፈጣን ኢኮኖሚን ማምጣትን፣ የሚፈጠሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባራዊ ግጭቶችን መፍታትን እና የጋራ ኢኮኖሚያዊ አንድነት መፍጠርን…ወዘተ. ጠቀሜታዎችን ማጣጣም የሚቻል ይመስለኛል።

ይህም በፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ ዕውን የሚሆኑ ጥቅሞች እስካሉ ድረስ፤ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እያረመና ከህዝቦች ፍላጎት ጋር እየተራመደ ሊፈጠሩ ለሚችሉ ማናቸውም ነባራዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ መሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው።

ፌዴራሊዝም መሰረቱን በህገ መንግስታዊነትና በህግ የበላይነት ላይ ያደረገ በመሆኑ አንድ አገር ሥርዓቱን ሲመርጥ ብዙሃነትን የያዘ ቢሆንም፤ የተመሰረተው ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ መሆኑንም ማረጋገጥ የውዴታ ግዴታው ይሆናል፡፡

ይህም ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚከተል አገር ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ሊሸከም የሚችልበት ትከሻ የሌለው መሆኑን ያሳየናል፡፡ እናም እዚህና እዚያ የሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ምላሽ የሚያገኙ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል፡፡ ሥርዓቱ ገና ከጅምሩ ሲዋቀር ለሚፈጠሩ ለሚችሉ ጉድለቶች ሁለንተናዊ መፍትሔ የሚያስገኙ መፍትሔዎችን አመቻችቶ በመሆኑ ምንም ዓይነት ችግር ከሥርዓቱ በታች እንጂ በላይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy