Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ – ስለ ማረሚያ ቤት ቆይታው

1 515

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

Written by  አለማየሁ አንበሴ

“እንደ ፍርደኛ ሳይሆን እንደ ጦር ምርኮኛ ነበር የምታየው”
• “በሃገሪቷ ላይ ምን እየተካሄደ እንዳለ አላውቅም ነበር”
• “እናቴ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ያላት ነች”

ባለፈው አርብ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ከእስር እንደሚለቀቅ ሲጠበቅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ፤በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት በዕለቱ ሳይፈታ በመቅረቱ ቤተሰቦቹ ማዘናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ጋዜጠኛው ከሁለት ቀን በኋላ ግን የ3 ዓመት እስሩን ያለ አመክሮ አጠናቅቆ፣መፈታቱ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ የማረሚያ ቤት ቆይታው ምን ይመስል ነበር? ወደፊትስ ምን አቅዷል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን አነጋግሮታል፡፡

የ3 ዓመት የማረሚያ ቤት ቆይታህ ምን ይመስላል?
እንግዲህ ወደ 2 ዓመት ከ10 ወር ገደማ የቆየሁት በዝዋይ እስር ቤት ነው፡፡ ቃሊቲና ቂሊንጦ ትንሽ ጊዜ ነበር የቆየሁት፡፡ ዝዋይ እስር ቤት የተወሰድኩት ደግሞ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ነው። ህገ መንግስቱ፤ ማንም ሰው መታሰር ያለበት ከመኖሪያ ቦታው በ25 ኪ.ሜትር ክልል ውስጥ ነው ቢልም እኔ ግን 165 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ የበረሃ እስር ቤት ነው ተወስጄ የታሠርኩት፡፡ ዝዋይ የሚሄዱ እስረኞች፣ ከ5 አመት በላይ የተፈረደባቸው እንደሆኑ በራሣቸው መመሪያ ላይም ተቀምጧል። ይህ እንግዲህ በመጀመሪያ በ25 ኪ.ሜትር ርቀት ውስጥ የሚለው የህገ መንግስቱ ድንጋጌና የራሱ የማረሚያ ቤቱ መመሪያ ተጥሶ ነው፣ እዚያ በረሃ ላይ ከ2 ዓመት በላይ እንድታሰር የተደረገው፡፡ በእነዚህ አመታት ደግሞ ልዩ ጥበቃ የሚባል ቦታ ነው

የታሰርኩት፡፡ ይህ ቦታ ከሰማይ በስተቀር ምንም የማይታይበት ቦታ ነው፡፡ በዚያ ላይ በፍ/ቤት በኩል እንደመጣ እስረኛ ሣይሆን በተፋፋመ የጦር አውድማ ላይ እንደተያዘ የጦር ምርኮኛ ነበር የምታየው፡፡ ይሄ አመለካከት ደግሞ ከፍተኛ በደልና ተፅዕኖ እንዲደርስብኝ አድርጓል፡፡ ሰው የገደሉ ወይም አስገድዶ የመድፈር ወንጀል የፈጸሙ እስረኞች እንኳን የሚያገኙትን መብት አላገኝም ነበር፡፡ እነዚህን መሰል እስረኞች በነፃነት ካፍቴሪያ ሄደው ቡና ጠጥተው፣ ተዝናንተው ይመለሳሉ፤ ሲያሻቸውም በላይብረሪ መጠቀም፣ የሃይማኖት ቦታዎች መሄድ፣ ኳስ ሜዳ ወርደው መጫወት ይችላሉ፡፡ ለእኔ ግን እነዚህ ሁሉ የተከለከሉ ነበሩ፡፡
እነዚህን መብቶች  ስትጠይቅ የሚሰጥህ ምላሽ ምን ነበር?
አብዛኞቹ ጠባቂዎች ከላይ የተነገራቸውን ነው የሚፈፅሙት፡፡ ስለዚህ ለኔ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና ሁኔታውን ለማስረዳት የሚጨነቅ ሃላፊ የለም፡፡ ለምሳሌ ምግብ የምመገበው በርከት ካሉ የእስር ቤት ወዳጆቼ ጋር ነው፡፡ እነ ጀነራል አሣምነው ፅጌና ሌሎችም አብረውኝ ይመገቡ ነበር። ስለዚህ ቤተሠብ በርከት አድርጎ ነበር ምግብ የሚያመጣው፡፡ እነሱ ግን ምግቡን በራሣቸው ፍቃድ ይቀንሱብኝ ነበር፡፡ ባስ ሲልም ከበር ከእነ ጠያቂዎቼ ይመልሱታል፡፡ ለምሣሌ 5 እንጀራ የሚመጣልኝ ከሆነ፣ እንዲገባ የሚፈቅዱት አራቱን ብቻ ይሆናል። አንድ ሊትር ወተት ሲመጣ “ለተመስገንማ ግማሽ ሊትር ይበቃዋል” ተብሎ እንዲቀነስ ይደረጋል ወይም ያመጣው ሰው ተቀንሶ እንዲጠጣው ይደረጋል፡፡ ይሄ ሁሉ በማን እንደሚፈፀም ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ መንግስት ይሄን ትዕዛዝ ያስተላልፍ ወይም ግለሰቦች በፈቃዳቸው ይፈፅሙት ለማወቅ ይቸግራል፡፡

በእስር ቤት ቆይታህ ያምህ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ህመምህ በእስር ወቅት የተፈጠረ ነው ወይስ በፊትም የነበረ?
ከመታሠሬ በፊት የወገብ ችግር ነበረብኝ፡፡ ብዙ ጊዜ ቴራፒ እየወሰድኩበት ነበር የምንቀሳቀሰው። ከታሰርኩ በኋላ ግን እዚያ ጭለማ ቤት የምንቀሳቀስበት ቦታ አልነበረም፡፡ ህክምናም በአጠቃላይ ተከልክዬ ነበር፡፡ ስለዚህ ከፍተኛና አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰው እዚያ ከገባሁ በኋላ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የወገቤ ህመም እጅግ እየከፋ በመጣ ጊዜ የቀይ መስቀል ማህበር ሰዎች እንድታከም ግፊት አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ሃላፊዎቹ ፍቃደኛ ሣይሆኑ ቀሩ፡፡ በመሃል ግን በከፍተኛ ግፊት፣ ወገቤን ታምሜ መራመድ የማልችለው ሰውዬ፣ እንደ አንድ ዓለማቀፍ አሸባሪ፣ በካቴና ታስሬና በበርካታ ፖሊስ ተከብቤ፣ ባቱ (ዝዋይ) ሆስፒታል እንድታይ የተደረኩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በወቅቱ ሃኪሞቹ፣ “ህመምህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ከኛ አቅም በላይ ስለሆነ ሪፈር ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንፅፍልሃለን” ብለው ቢፅፉልኝም፣ ወደ ሆስፒታሉ መጥቼ እንድታከም እድሉ አልተሰጠኝም፡፡ የህክምናዬ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ብዬ ስጠይቅ፣ “እንዳታመጡት ተብለናል፤ እኛ ምን እናድርግ” የሚል ምላሽ ነበር የሚሰጡኝ። “ዝዋይ ሆስፒታል ስለወሰድንህ ራሱ እንደ ጥፋት ታይቶብናል” ብለውኝ ነበር ሃላፊዎቹ፡፡

ከወገብ ህመሜ በተጨማሪ ባላወቅሁት ምክንያት ድንገት የጀመረኝ የጆሮ ህመሜ ተባብሶ፣ ህክምና ለማግኘት ባለመቻሌ፣ አሁን የቀኝ ጆሮዬ ሙሉ ለሙሉ አይሰማም፡፡ በአጠቃላይ የእስር ቤት ቆይታዬ በስቃይ የተሞላ ነበር፡፡ ቀን የበረሃው ንዳድ፣ ሌሊት እንደ አሸዋ በሰውነት የሚሯሯጥ የትኋን መአት እንቅልፍ ይነሳሃል፡፡ ለኔ እስር ቤት የሚለው ቃል እንኳ የማይገልፀው ከፍተኛ የማሠቃያ ቦታ ነው፡፡
አሁን ጤንነትህ በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

እንግዲህ ከተፈታሁ በኋላ እቤት እንግዶች ስለበዙብኝ መውጣት አልቻልኩም እንጂ ሙሉ ምርመራ አድርጌ ያለሁበትን ሁኔታ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በእርግጥ ጆሮዬ ሙሉ ለሙሉ እንደማይሰማ አረጋግጫለሁ፡፡ አሁን ማወቅ ያልቻልኩት የወገቤ ህመም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ነው፤ ይሄን ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
ያለህበትን ሁኔታ ለማወቅ በማረሚያ ቤት ተገኝቶ ያነጋገረህ አካል ነበር?
ማንም መጥቶ ያነጋገረኝ አካል የለም፡፡ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ እኔ ላይ ምንም ጥላቻ እንደሌላቸው ነገር ግን በትዕዛዝ የሚሰሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መሆናቸውን ይነግሩኝ ነበር፡፡ የሚፈጽሙትን  በሙሉ ታዘን ነው ይሉኝ ነበር፡፡ መጡ ከተባለ ምናልባት የፓርላማ አባላት መጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ራሳቸውን ሲያስተዋውቁን፣ “በህዝብ ምርጫ ከተቋቋመው ፓርላማ” የመጡ መሆናቸውን ሲገልፁ፣ እዚያው ጋ ነገር ተበላሽቶ አልተግባባንም፤ መነጋገርም አልቻልንም፡፡
ወላጅ እናትህ ማረሚያ ቤት እየመጡ  ይጠይቁህ ነበር?

እናቴ በ70ዎቹ ውስጥ ያለች አዛውንት ነች፡፡ በመንፈስ ግን እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጥንካሬ ያላት እናት ነች፡፡ አልፎ አልፎ ትመጣ ነበር፡፡ እሷን እንኳ እንዳትጠይቀኝ ከበር ይመልሷት ነበር፡፡ ከክፍለ ሀገር የመጡ ዘመዶቼ ጭምር ይመለሱ ነበር – ሳይጠይቁኝ፡፡ እናቴ በዚህ መጎሳቆሏ ያሳዝነኝ ነበር። በኋላ ግን እንዳትመጪ ብዬአት መምጣት ተወች፡፡
የሀገሪቱን ሁኔታ በሚዲያ የመከታተል እድሉ ነበረህ? መረጃስ ታገኝ ነበር?

እኔ የነበርኩበት ቦታ የመንግስት ሚዲያ ይሰማል፤ በተረፈ ግን ምንም ዓይነት መፅሐፍ አይገባም ነበር፡፡ የፖለቲካም ሆነ ሌላ ልቦለድ መፅሐፍ ሳይቀር እንዲገባ አይፈቀድም፡፡ የመንግስት ዜና ብቻ ነበር እንድከታተል የሚደረገው፡፡ በዚያ ላይ የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳይ አንስቶ መወያየት አይቻልም ነበር፡፡ ጠያቂዎቼን ገና “አዲስ አበባ እንዴት ነች?” የሚል ጥያቄ ሳነሳ ነበር ወዲያው የሚያስቆሙኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ምንም መረጃ አልነበረኝም፡፡ ሀገሪቱ ላይ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡ እንደውም ከእስር ተለቅቄ ወደ ቤት እየመጣሁ ሞጆ ስደርስ፣ የኦነግን ባንዲራ የያዙ ወጣቶች መንገዱን ሞልተው፣ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ አይቼ፣ በጣም ነው የተገረምኩት፡፡ ምክንያቱም ከ3 ዓመት በፊት ይሄ ባንዲራ ያስከፍል የነበረውን ዋጋ አስታውሳለሁ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት እንደተደረሰ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ግራ ተጋብቼና ተደንቄ ነው ሁኔታውን ስመለከት የነበረው፡፡
አመክሮ የተከለከልክበትን ምክንያት ታውቀዋለህ?

የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ስለ አመክሮ የሰጡኝ ህገ ደንብ አለ፡፡ እዚያ ሰነድ ላይ “አንድ እስረኛ አመክሮ የሚከለከለው እስር ቤቱ ውስጥ ወንጀል ከፈፀመ ብቻ ነው” ይላል፡፡ እኔ ደግሞ አንድም ወንጀል አልፈፀምኩም፡፡ ስለዚህ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አመክሮ የተከለከልኩበት ምክንያት የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡
ይቅርታ ጠይቀህ እንድትወጣ ተጠይቀህ ነበር የሚባለው እውነት ነው?
ይሄ እንዴት መሰለህ? አንድ ዓመት እንደታሰርኩ፣ ከጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም አስራ አምስት ቀን በፊት ኃላፊዎቹ፤ “ጥቅምት 3 ትፈታለህ ተዘጋጅ” አሉኝ፡፡ እኔ በወቅቱ ሁኔታው አልገባኝም ነበር፡፡ ከሁለት ወር ቀደም ብሎ ከጨለማ ቤት አስወጥተውኝ፣ ከሌሎች እስረኞች ጋር ቀላቀሉኝ፡፡ ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ከ2 ሺህ ያህል እስረኞች ጋር ቀላቅለው፣ “ተፈትተሃል እቃህን ይዘህ ውጣ” አሉኝ፡፡ እኔም እፈታለሁ በሚል አስቀድሜ እቃዬን ሁሉ እዚያው ለቀሩ እስረኞች አከፋፍዬ ጨርሼ ነበር፡፡ ልክ ውጣ ባሉኝ መሰረት ፍተሻ አልፌ በሩን ከወጣሁ በኋላ አስቁመውኝ፣ “በስህተት ነው” በማለት ወደ እስር ቤት መለሱኝ፡፡ እንዳልኩት እቃዬን በሙሉ አከፋፍዬ ባዶ እጄን ቀርቼ ነበር፡፡ እና ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር በወቅቱ፡፡
የእስር ጊዜህን ያሳለፍከው ከምን ዓይነት እስረኞች  ጋር ነበር?

ሁለቱን አመት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል ተብለው ከታሰሩት ከእነ ጀነራል አሳምነው ፅጌና ጀነራል ተፈራ ማሞ ጋር እንዲሁም ከኦነግ፣ ኦብነግና ከግንቦት 7 ተከሳሾች ጋር ነበር ያሳለፍኩት፡፡
የወደፊት ዕቅድህ ምንድን ነው?
የመጀመሪያው ዕቅዴ፣ የጤንነቴ ሁኔታ ምን ላይ እንዳለ ማወቅ ነው፡፡ የጤንነቴ ሁኔታ ያለበት ደረጃ ደግሞ ቀጣዩን ዕቅዴን ይወስነዋል፡፡ ምክንያቱም ሃኪሞች፣ “የጆሮ ህመምህ ፓራላይዝድ ሊያደርግህ ይችላል” ብለውኛል፡፡ አሁን በዋናነት ማወቅ የምፈልገው ይህ ህመሜ ያለበትን ደረጃ ነው፡፡
በመጨረሻስ …?

እንግዲህ እናቴና ወንድሞቼ ከእኔ እኩል ነው የታሰሩት፡፡ ያን ሁሉ መከራ አብረውኝ አሳልፈዋል። ቤተሰቦቼ በጠላትነት እየታዩ ብዙ መከራ ከኔ ጋር አሳልፈዋል፡፡ እንደውም ታናሽ ወንድሜ ታሪኩ፣ በማረሚያ ቤቱ ጥበቃዎች ተደብድቦ ነበር፡፡ ይሄን ሁሉ እያደረጓቸውም ሶስቱን ዓመት አብረውኝ ታስረዋል፤ እነሱን አመሰግናለሁ፡፡ እንዲሁም የእኔ እስር አሳስቧቸው፣ ከኔ ጋር ሲጨነቁ ለነበሩ የፌስቡክና የማህበራዊ ሚዲያ አባላት ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም 3 ዓመት ሙሉ ከጎኔ ቆሟልና በእጅጉ አመሰግናለሁ፡፡

  1. Mulugeta Andargie says

    ተመስገን!! ውነት ያንተ ቃለ ምልልስ ከሆነ ከላይ ያለው ቃል: እጅግ ዋሽተሃል:: ለነገሩ እስራትህ’ን ጨርሰህ ተገላግለሃል:: አንድ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ እስር ቤት ከገባ: ማለትም ከተፈረደበት: የወህኒው ቤት: በመሰለው መንገድ አጠባበቅ ያደርጋል:: ኣንተን በተለየ መልክ ኣያይህም:: ወንጀለኛ መብት የለውም!!
    ጥፋትህን እንድታርም ስለሆነ የመረረ ቅጣት ይሰጥሃል:: ቁምነገሩ ከስህተት መማሩ ነው!! መከራክር የነበረብህ ዳኛው እንዳይፈድብህ ነበር!!!ዳግም እንዳታያት ተጠንቀቅ!!! የዲሞክራሲ መብትህን ማንም ለይቶ የሚነጥቅህ ሰው የለም!!ስልጣንም የለውም!!!ወጣት ነህ ላገርህ ብዙ ስራ ትሰራ ይሆናል!! ካኮረፍክ ደግሞ መንገዱ ባራቱም ማእዘን ነው!! መልካም ዕድል!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy