Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግጭትን ማራገብ ተጠያቂነትን ያስከትላል!

0 555

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግጭትን ማራገብ ተጠያቂነትን ያስከትላል!

                                                          ታዬ ከበደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት አስመልክተው በችግሩ ውስጥ ተሳትፈው ግጭቱን ለማራገብ የሚሞክሩ የውጭም ይሁን የውስጥ ሃይሎችን ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳን ከእርሳቸው ማስጠንቀቂያ በኋላ ችግሩ የቀዘቀዘ ቢሆንም፤ አሁንም በተለያዩ ዘውጎች ግጭትን በማራገብ ስራ ላይ የተጠመዱ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች የህዝቦች ፍላጎት ያልሆነውን ግጭት ማራገባቸው ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትከተለው ስርዓት ግጭትን የሚያርቅ እንጂ ለግጭት የሚጋብዝ ስላልሆነ ነው፡፡

እርግጥ ግጭቶች በየትኛውም ሁኔታ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግጭት መፈጠር የለበትም ሊባል አይችልም፡፡ በየትኛውም ማህበረሰብ መስተጋብራዊ ግንኙነት ውስጥ  ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናረጋጋቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ መጥፎ የሚያደርጋቸው አስተሳሰባችን ነው፡፡

 

ለውጥን መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ከተቃኘ፣ ግጭት የለውጥ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ፌዴራሊዝም የግጭት መነሻ ነው የሚባለው አመለካከት መሰረት የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት መቻቻልን ያመጣና በሂደትም በመጎልበት ላይ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ በመሆኑ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች ስለተዋቀረ ነው፡፡ በመሆኑም እዚህ አገር ውስጥ ለግጭት የሚሆን ስፍራ እንደሌለ ግጭት አራጋቢዎቹ ሊያውቁት ይገባል፡፡

 

ያም ሆኖ ግጭትን የሚያራግቡ ሃይሎች ለልማት በመትጋት ላይ በሚገኘው ወጣት እጅ እሳት ለመጨበጥ በበሞከር ከስሮ የወደቀ ፖለቲካቸውን ለማንሰራራት የሚከጅሉትን ፀረ-ሰላም ሃይሎችን ማንነት በሚገባ የሚያውቀው ዕውነታ ነውና።

ስለሆነም ህዝቡ በሂደት እንደ አሜኬላ እሾህ ከመሃሉ እየነቀለ በማውጣት ህግ ፊት እንደሚያቀርባቸው በእርግጠኝነት መግለጽ ይቻላል። ምክንያቱም በሀገር አቀፍ ደረጃም ይሁን በክልሉ እየተመዘገበ ካለው ባለ ሁለት አሃዝ ፈጣንና ተከታታይ ልማታዊ ዕድገት ተጠቃሚነቱ እንዲስተጓጎልበት ስለማይፈልግ ነው።

 

በመሆኑም በአሸባሪዎችና በፀረ-ሰላም ሃይሎች አሉባልታ እንደ ቦይ ውሃ የሚነዳ ህዝብም ሆነ መንግስት አለመኖሩን ማወቅ የሚገባ ይመስለኛል። እርግጥ የፀረ-ሰላም ኃይሎቹ አሉባልታ የሰላም ወዳዱና ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአንድነት የማደግ ፍላጎት ያለው የኦሮሞም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ አጀንዳ አይደለም።

 

የሁለቱ ህዝቦች ፍላጎት ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በመተሳሰብና በመደጋገፍ በጋራ የመልማት፣ ከአጎራባች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲሁም ባደረገው መራር ትግል ዕውን እንዲሆን ባስቻለው ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩት መብቶቹ ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩላቸው ነው።

 

በግጭት አራጋቢዎች አሉባልታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤ ሴራው ሆን ተብሎ ሁለቱ ህዝቦች አገራዊና ክልላዊ ተጠቃሚነት ለማደናቀፍ እንዲሁም በትግል ያገኛቸውንና እያጎለበታቸው የሚገኙትን ሁለንተናዊ ህገ-መንግስታዊ መብቶቹን ለመሸርሸር ብሎም ህዝቡ ተረጋግቶ በልማት ስራው ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ የታለመ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ባለፉት ዓመታት በተጎናጸፏቸው የልማትና የዕድገት ዕድሎች በብቃት በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በህዝቦች ይሁንታ የተመሰረተው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መገንባት ከጀመረበት ወዲህ በሁለተም እየታየ ያለው ለውጥ ከፍተኛ ነው፡፡

ከለውጦቹ መካከል በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በተመዘገቡ ለውጦች አጠቃላይ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አኃዝ እንዲያድግ አስችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ውሰጥ የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊነትና ባለቤትነት ነበር። ያለ ህዝቡ ይሁንታና ፈቃድ የተከናወነ ነገር የለም፤ ወደፊትም አይኖርም።

ሆኖም የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ግጭት አራጋቢዎች ሁሌም በክልሉ ላይ በማተኮርና በሽብርተኝነት ከተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በጸረ ሰላም ሚዲያዎች የሀሰት ወሬ በመንዛት ሁከት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። የሚሳካለቸው ግን አይደለም።

እነዚህ ግጭት አራጋቢዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው ናቸው። በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት የሁለቱ ክልል ህዝቦች የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት ሲያደርጉ አድርገዋል። ሊሳካላቸው ባይችልም።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሁለቱ ክልል ህዝቦች በተፈጥሮ በተቸራቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ለዘመናት ተነፍጎ ከኖረበት ሁኔታ ራሳቸውን በማላቀቅ ዛሬ ላይ ቋንቋቸው የሳይንስ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የእድገት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆንም ባካሄዱት መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በማምጣት የየክልላቸውን ህዝቦች በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

ይህ በክልሎቹ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት የሚያሳበዳቸው እነዚህ ግጭት አራጋቢዎች የልማቱን ግስጋሴ ባዩ የጥፋትና የብተና አቋሞቻቸው ከመቃብር በታች ይውሉብናል በሚል ስጋት የሞት ሽረት ትግል ማድረጋቸው የማይቀር ቢሆንም፤ የሁለቱም ክልል ህዝቦች የእነዚህን እኩይ ሃይሎች ትክክለኛ ፍላጎት በመገንዘብ ሴራቸውን ዛሬም እንደ ትናንቱ ሊያመክኑት ይገባል።

ግጭት አራጋቢዎች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በሁለቱም ክልሎ ውስጥ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል። አንዳንዴም የገቢ የሆኑ የህዝቦችን ጥያቄዎች ከመጠን በላይ በማጎንና ለግጭት መንስኤ እንዲሆን በማድረግ እኩይ ሴራቸውን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል። ያም ሆኖ ግጭትን ማራገብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ እነዚህ ሃይሎች ሊገነዘቡ ይገባል።

የአገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት የህግ የበላይነት የነገሰበት በመሆኑ የትኛውም አካል ግጭትን በማራገብ ተግባር ላይ ተሳትፎ እስከተገኘ ድረስ ከተጠያቂነት አያመልጥም። በመሆኑም በውጭም ይሁን በውስጥ የሚገኙ ግጭት አቀጣጣዩች ተግባራቸው መልሶ ራሳቸውን እንደሚያስጠይቃቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy