Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራሊዝም እና ኢትዮጵያ

0 1,065

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራሊዝም እና ኢትዮጵያ

ወንድይራድ ኃብተየስ

ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ብቸኛው አማራጭ ነው። የፌዴራል ሥርዓትን መከተል ለኢትዮጵያ እስትንፋስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጽንፈኛ  የትምክህትና ጥበት ቡድኖች በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ላይ የሚሰጡትን አስተያየት ላዳመጠ ሳይደመም አይቀርም።

እነዚህ ቡድኖች ወይ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ አያውቁም፤ አሊያም ይህቺ አገር ቀጣይ እጣ ፋንታዋ ምንም ይሁን ምን ደንታ የላቸውም። ምክንያቱም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የፌዴራል ሥርዓቱን ለማፍረስ መዳዳት፣ የአገሪቱን ጉሮሮ ማነቅ፣  እስትንፋሷን መዝጋት፣ ሉዓላዊት አገርን መበታተን ብሎም ህዝብን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ ማስገባት እንደሆነ መታወቅ አለበት።

የኢትዮጵያን ታሪክ የኋሊት መለስ ብሎ ላስተዋለ ለረዥም ዓመታት በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መዝለቅን ነው። በመላ አገሪቱ ተከስቶ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት እልባት ያስገኘው የፌዴራል ሥርዓቱ ነው።

በኢትዮጵያ ዛሬ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ይዘዋል፤  ቋንቋቸውንና  ባህላቸውን መጠቀም ችለዋል፤ በማንነታቸው  ኮርተዋል፤ አካባቢያቸውን በማልማት ከምጣኔ ሀብታዊ ዘርፉ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህን የህዝቦችን መብት ያስጠበቀ ሥርዓትን መነካካት መዘዙ የከፋ ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት ፌዴራላዊ  ሥርዓትን መከተል ችላለች። ዜጎች ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች  ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጠዋል።

ለመሆኑ ፌዴራሊዝም ወይም ፌዴራላዊ ሥርዓት ምንድነው? ፌደራላዊ ሥርዓት ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ መንግሥታት (ፌዴራልና ክልል መንግሥታት) የሚፈጥሩት የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን ያጣመረ፣ በቃል ኪዳን የሚመሠረትና የሚመራ አጋርነት ነው፡፡ ይህ አጋርነት በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን ክፍፍልና ዝምድና ይወስናል፡፡ አንዱ የሌላውን ቅንነትና አብሮ የመኖር እሳቤን በማመን ላይ የተመሠረተ፤ አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት በማክበርና በእኩልነት በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን 28 የሚደርሱ አገራት በፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት የሚተዳደሩ ናቸው። 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በእነዚህ አገራት ሥር የሚኖሩ መሆኑም በፌዴራሊዝም ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ዴሞክራሲን ለማስፈን ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች የመንግሥት አወቃቀር መልኮች የበለጠ የተሻለ በመሆኑ 21ኛው ክፍለ ዘመን አገራት ወደ ፌዴራሊዝም አስተዳደር የሚሸጋገሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

አገራት ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥትን ምርጫቸው የሚያደርጉበት የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው። አራት ዋና ዋና ምክንያቶችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ ብዝሃነትን ማስተናገድ፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰፊ ገበያና ትልቅ ኢኮኖሚ የመገንባት ፍላጎት ነው። ሦስተኛው ምክንያት ጠንካራ የመከላከያ ኃይልና የደህንነት ሥርዓት ባለቤት መሆን ነው፡፡ አራተኛው ምክንያት አስተዳደራዊ አመቺነትን መፍጠር ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓትን እንድትከተል ያስገደዳት በአገሪቱ ያለው ብዝሃነት ነው።  

የኢፌዴሪን ህገ መንግሥት መሠረታዊ ዓላማዎች በህገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ በዚህ መልኩ ሰፍሯል። በአገራችን ባለፉት ሥርዓቶች ይስተዋሉ የነበሩት የተዛባ ግንኙነቶችን ለማስተካከል፣ ቀድሞ ያላቸውን የጋራ አብነቶችና እሴቶች ትስስር ለማጠናከር፣ ዘላቂ ሠላምን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቃል የገቡ መሆናቸውን፣ ይህን ለማሳካት የግለሰብም ሆነ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች መብቶችና የፆታ እኩልነት ማረጋገጥ፣ ባህሎችና ኃይማኖቶች ያለ አድሎና ልዩነት እንዲራመዱ ማድረግ ፅኑ እምነታቸው እንደሆነ መወሰናቸውን የሚል ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ሁሉን ያሟላ ዘመናዊ የሚባል ህገ መንግሥት ነው። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በየዘርፉ ማለትም በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያደርግ አንቀጾችን አካቷል። በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ደጋግሜ መጠቃቀሴን ለማስታወስ እወዳለሁ። በዛሬው መጣጥፌም ይህንኑ ሀሳብ ለማጉላት እሞክራለሁ።

 

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን የምትከተል አገር ነች። አገሪቱ በዚህ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች ወዲህ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ፌዴራል ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓቶች የሚለይባቸው አምስት መሠረታዊ የተባሉ ባህሪያት አሉት፡፡ የመጀመሪያው የመንግሥት አወቃቀርና ተጠያቂነት ማስፈን ነው። ሁሉም ፌዴራል አገሮች ቢያንስ ሁለት መንግሥታት (ፌዴራልና ክልሎች) አሏቸው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፣ ተጠያቂነታቸውም ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ እነዚህ መንግሥታት ህልውናቸው የሚረጋገጠው በህገ መንግሥት ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር እንደየአገራቱ ሁኔታ ጂኦግራፊያዊ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለመረጣቸው ህዝብ ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥት የሚመረጠው በአጠቃላይ በአገሪቱ ህዝብ ነው። የክልል መንግሥታት ደግሞ በየክልሉ ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በዋናነት የተዋቀረው በህዝቦች ማንነት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት አደረጃጀት የተመረጠበት ምክንያት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፈው ታሪክ የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን በሕገ መንግሥት ዋስትና እንዲያገኙና በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችል አወቃቀር ስለሆነ ነው፡፡

እነዚህ ህዝቦች የተዛባው ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋራ ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው፡፡ የአገራችን የአከላለል መሥፈርት ማንነትን፣ ቋንቋን፣ አሠፋፈርንና ፈቃደኝነትን ታሳቢ ያደረገው በአገሪቱ ህዝቦች የትግል ታሪክ የእኩልነት ጥያቄ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ነው። የማንነት መገለጫ የሆኑትን ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን፣ ባህልንና ታሪክን ለማጥናት ለመንከባከብና ለማሳደግ ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

ሁለተኛው የፌዴራላዊ ሥርዓት ባህሪ የሆነው የሥልጣን ክፍፍል ማለትም የራስ አስተዳደር እና የጋራ አስተዳደር መመሥረት መቻል ነው። የሥልጣን ክፍፍል የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ እያንዳንዱ መንግሥት በተሰጠው አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የመፈፀም፣ ሕግ የመተርጎምና ገቢን የመሰብሰብ ሥልጣን አለው፡፡ የሥልጣን ክፍፍሉ እንደየአገራቱ ሁኔታ ቢለያይም አገራዊ ጉዳዮችንና አንድነትን ለማስጠበቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሥልጣኖች ለፌዴራሉ መንግሥት የሚሰጡ ናቸው። ከክልሎችና ብሄር ብሄረ-ሰቦች ልዩ ሁኔታና ባህል ጋር የተያያዙ ሥልጣኖች ደግሞ ለክልሎች ይሰጣሉ፡፡ በኢትዮጵያም ፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ሕግን የማውጣት፣ ሕግን የመፈፀምና ሕግን የመተርጎም ሥልጣን አላቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በአንቀፅ 51 የክልሎች ደግሞ በአንቀጽ 52 ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ተለይተው ያልተዘረዘሩ ቀሪ ሥልጣኖችም ለክልሎች ተሰጥተዋል፡፡

ሦስተኛው የፌዴራል መንግሥታት ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌዴራል አገሮች የተፃፈ ሕገ መንግሥት ያላቸው መሆኑ ነው። ሕገ መንግሥት የስምምነታቸው ወይም ቃል ኪዳናቸው ማሰሪያ ሰነድ ነው፡፡ በአንድ በኩል አንዱ እርከን ሥልጣኑን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት የሌላውን እርከን ሥልጣን እንዳይነካ የሚገታው ወይም ሥልጣኔ ተነካ የሚል ካለ ተጠቃሽ ሆኖ የሚያገለግል የተፃፈ ህገ መንግሥት መኖር የግድ ይሆናል፡፡ እንደየአገራቱ ህገ መንግሥቱን የማሻሻል ሥርዓት ቢለያይም ሁሉም ፌዴራል አገሮች የህገ መንግሥታቸውን የተወሰኑ አንቀፆች ያለፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ስምምነት ሊያሻሽሉ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግሥትም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና የኅብረተሰብ ተወካዮች የድርድር ውጤት ነው፡፡

አራተኛው የፌዴራል ሥርዓቶች ባህሪ የሆነው ሁሉም ፌዴሬሽኖች ሁለት ምክር ቤቶች አሏቸው፡፡ አንዱ “የተወካዮች ምክር ቤት” ወይም “የታችኛው ምክር ቤት” የሚባል ነው። ሌላው ደግሞ “የላይኛው ምክር ቤት” ወይም “ሁለተኛ ምክር ቤት” በሚል ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው ምክር ቤት በተለያዩ ፌዴራል አገራት የተለያየ መጠሪያ አለው። በኢትዮጵያም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ አወቃቀርና ሥልጣኑም እንደየአገራቱ ሁኔታ ይለያያል። የኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ አንድ ውክልና ለተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ተጨማሪ አንድ ወኪል እንዲኖር ያደርጋል፡፡

የምክር ቤቱ ተወካዮች አመራረጥን በተመለከተ በአንዳንድ ፌዴሬሽኖች በቀጥታ በህዝብ ሲመረጡ በሌሎች ደግሞ ከግማሽ በላይ ወይም ከግማሽ በታች ተወካዮች በክልሎች ሥራ አስፈፃሚዎች ይመረጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ አባላቱ በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ ወይም ምክር ቤቶቹ በክልሎች ህዝቦች በቀጥታ እንዲመረጡ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት መንገድ ይወስናል፣ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ ቀመር በማውጣት ያከፋፍላል፣ ህገ መንግሥትን ይተረጉማል፣ በክልሎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሄ ይሰጣል፡፡

አምስተኛው የፌዴራል ሥርዓት ባህሪያት የሆነው የህገ መንግሥት ጉዳዮች ገላጋይ ተቋም  መኖር ነው። የፌዴሬሽኖች ህገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍል ጥቅል፣ መደራረብና መጋራት የሚታይበት ነው፡፡ በመሆኑም በአፈፃፀም ሂደት አንዱ የሌላውን ሥልጣን ሊነካ ስለሚችል በዚህ ጊዜ የሚነሳን አለመግባበት በውይይት መፍታት ካልተቻለ የዳኝነት ፍርድ የሚሰጥ ገላጋይ ተቋም አላቸው፡፡ በዚህ ዙሪያም እንደየአገሩ ልዩነቶች አሉ፡፡ በኢትየጵያ ህገ መንግሥታዊ አለመግባባቶችን ግልግል የሚሰጠው ተቋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት መከተል ከጀመረች ጊዜ አንስቶ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸውንና ነጻነታቸውን በማረጋገጣቸው በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ሰፍኗል። በዚህም ፈጣን ልማት አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን ጥቅም ያስገኘላቸውን ሥርዓት መነካካት ወይም ለማፍረስ መሞከር የማይታሰብ ነው። በመሆኑም በሁለቱም በኩል ማለትም በትምክህትም ሆነ በጥበት  የምናስተውላቸውን ጽንፈኛ ኃይሎች መዋጋት የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው። ትምክህትና ጥበት የፌዴራል ሥርዓታችን ጠንቆች መሆናቸውን ተገንዝበን የሃሳብ ትግል ልናደርግባቸው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy