Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝባዊው መከላከያ ሰራዊታችን

0 276

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝባዊው መከላከያ ሰራዊታችን

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በአዲስ መልክ ህብረ-ብሔራዊ ሆኖ በአዋጅ ከተቋቋመት ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ሀገራችንን ከውስጥና ከውጭ ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች የመከላከል ተልዕኮዎችን ከመፈፀም ባሻገር፤ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ በሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ሰንቆ በፅናትና በጀግንነት ሲወጣ የመጣ ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን በየትኛውም ቦታ ለግዳጅ ሲሰማራ በቅድሚያ የህዝብን ደህንነትና ህዝብን በሚጠቅም ተግባራት ዙሪያ ብቻ የሚንቀሳቀስ ለህዝብ የወገነ ኃይል ነው። በህዝብና በመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ለግዳጅ በሚሰማራበት ወቅት “ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር”፣ ምንግዜም የተሟላ ስብዕና”፣ “ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ” እና “በማንኛውም ግዳጅ/ሁኔታ የላቀ አፈፃፀም” የሚሉ  እሴቶቹን በህዝባዊነት መንፈስ ተላብሶ ተልዕኮውን የሚፈፅም ለህዝብ የወገነ ኃይል ነው።

ይህ ህዝባዊ ሰራዊት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለተለያዩ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ተልዕኮዎች ሲሰማራ ሁሉንም ተልዕኮዎቹን የሚወጣው ህዝብን ማዕከል አድርጎ ነው። መከላከያ ሰራዊታችን በእነዚህ እሴቶቹ እየተመራ ህዝብንና ሀገርን የሚጠቅም ስራ የሚያከናውን እንጂ አንዳንድ ፅንፈኞች እንደሚያስወሩት በአካባቢው ማህበረሰቦች የጋራ መስተጋብሮች ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮችን እየተከተለ ጣልቃ የሚገባ አይደለም።

የሰራዊቱ አመጣጥም ይሁን የተገነባበት አግባብ ይህን የፅንፈኞችን የቅንፈት አጀንዳ የሚያሳይ አይደለም። የአገራችን መከላከያ ሰራዊት እንኳንስ በሀገር ውስጥ ቀርቶ በውጭ ሀገርም ቢሆን የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በፍፁም ህዝባዊ መንፈስ ተግባሩን በመወጣት ላይ የሚገኝ ከህዝብ አብራክ የተገኘ ኃይል ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን በህገ መንግሥታዊ እምነቱ፣ በዓላማ ጽናቱና በማይነጥፍ ጀግንነቱ በተደጋጋሚ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ የሀገሩን ዳር ድንበር በደምና አጥንቱ አስከብሯል፡፡ ፀረ ሰላምና ፀረ -ልማት  ኃይሎችን በመደምሰስ ለልማቱ አስተማማኝ ሠላም አስፍኗል፡፡ በዓለም- አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች ጭምር ያለ አንዳች ልዩነት በመመረጥ ብቸኛ የዘመናችን ሰራዊት ሆኗል። በዚህ አነስተኛ ፅሑፍ ተዘርዝረው የማያልቁ ስኬቶቹ ምስጢር ደግሞ ህዝባዊነቱ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

የዚህ ሁሉ ስኬቶች ምክንያትም ፍርሃትን ሳይሆን አክብሮትን፣ በጥላቻ ፈንታ ጥልቅ ህዝባዊ ፍቅርን ማትረፍ በመቻሉ ነው። ሰራዊታችን በአንድ እጁ ጠብ መንጃ፣ በሌላኛው አካፋና ዶማ ይዞ በልማቱም ግንባር ቀደም ሆኖ ይሰለፋል። ከአርሶ አደሩ ማሳም ተለይቶ አያውቅም። ያርሳል፣ ይዘራል፣ ያርማል፣ ያጭዳል፣ ይወቃል፣ ምርት እንዳይበላሽም ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል።

በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ የወገኖቹን ችግር በመረዳት የመፍትሔ አካል የመሆን ተግባራትን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል። “ህዝብ  ነው ኃያል ክንዳችን፣ ሰላምና ልማት ነው ቋንቋችን” በማለት ማልዶ የዘመረው ይህ የህዝብ ልጅ፤ ቃሉን አጥፎ አያውቅም። በመዝሙሩ ጎላ አድርጎ እንደገለፀው ህዝቡን ኃያል ክንዱ እንዲሁም ሰላምንና ልማትን ቋንቋው በማድረግ ሁሌም ለህዝቡ እየሰራ ዛሬ ላይ የደረሰ የህዝብ ወገንተኛ ኃይል ነው።

ሰራዊቱ ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ተጋፍጦ፣ ለአንዴ ብቻ የሚኖራትን ህይወቱን ለእልፎች የመኖር ተስፋ ያለመለመ ነው። ምን ይህ ብቻ! ይህ ለህገ መንግስቱና ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ዘብ የቆመስው ሰራዊት፤ ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያንና አረጋዊያትን የሚጦር፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመሳሰሉ ቀሳፊ በሽታዎችና በሌሎች ምክንያቶች ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናትን የሚያሳድግና የሚያስተምር፣ ከራሱ በላይ ለህዝቡና ለሀገሩ ጥቅም ሲታትር ውሎ የሚያድር ነው።

የዚህን ህዝባዊ ሰራዊት የሰላምና የልማት ተሳትፎ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ አንደኛው ሀገራችን አድጋ የረሃብ፣ የድህነትና የመሃይምነት ተምሳሌነቷ ተፍቆ ማየት የማይፈልጉ፣ መበታተንና ተስፋ አልባነታችንን የሚናፍቁ የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችን እኩይ ሴራ ማክሸፍ ነው። ይህን ከኤርትራ ወረራ እስከ አሸባሪው አል ሸባብ የግብረ ሽበራ ተግባርን በመመከት እንዲሁም ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉ የሀገራችን አካባቢዎች የኤርትራ መንግስት እያስታጠቀ በሚልካቸውን አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎችን ላይ ህዝባዊ ክንዱን በማሳረፍ ህዝባዊ ተግባሩን ተወጥቷል፤ ነገም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።

እናም ይህ ሠራዊት ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እንዳለሙት የብጥብጥና የትርምስ ሀገር ሳትሆን የአህጉሪቱ መዲና፣ የድሃ ህዝቦች መብትና ጥቅም ተሟጋች እንድትሆን ያስቻላት ነው ብል ከእውነታው መራቅ ሊሆንብኝ አይችልም። ከትናንት እስከ ዛሬ ያከናወናቸው ተግባራት ይህን እውነታ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።

የሰራዊታችን ሁለተኛ የልማት ገፅታው ደግሞ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ካለው የአገሪቱ አቅም አኳያ ከሚያገኛት አነስተኛ ገቢ በፍፁም ህዝባዊና ሀገራዊ ፍቅር የሚገለፅ ቀጥተኛ የልማት ተሳትፎ እያደረገ ነው። ርግጥ ሰራዊታችን በዚህ በኩል የነበረውንና ያለውን ድርሻ በቀላሉ ለመግለፅ አይቻልም—ተግባራቱ ግዙፍ ናቸውና። ያም ሆኖ ግን ጥቂቶቹን ማንሳት ያስፈልጋል።

ርግጥ መከላከያችን የትልቋ ኢትዮጵያ እውነተኛ ተምሳሌት ብቻ አይደለም— መሃንዲስ፣ መምህር፣ አርሶና አርብቶ አደርም ጭምር እንጂ። መንገድ ገንብቶም ህዝቦችን ማገናኘት የቻለ ነው። ግድብ ሰርቶ አርብቶ አደሩ ወደ አርሶና ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀየርም አድርጓል። ትምህርት ቤት ሰርቶም የመማር ዕድሉ ያልነበራቸውን የህዝብ ልጆች ከዕውቀት ጋር አገናኝቷል።

ምን ይህ ብቻ! የጤና ተቋማት ላይ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን አፍስሶ ለእልፎች የመኖር ዋስትና የሰጠ የህዝብ ልጅ ነው። የእናቶችንና ህፃናትን ሞትን በመቀነስ ረገድም በተግባር ተሳትፏል። በምህንድስና እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቃት ያላቸው ሙያተኞቹን በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር አብዮትን በመለኮስ ፋና ወጊ ሆኗል። ካለው እያካፈለ፣ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር እየዋለ ድርብ ድርብርብ ኃላፊነቱንም ተወጥቷል። ኧረ ስንቱ ተዘርዝሮ ይገለፃል።…

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገራችን የቀየሰችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ዕውን በማድረግ ረገድ ጠላትን ተዋግቶ ከማሸነፍ ያልተናነሰ ድል አስመዝግቧል። የተራቆተውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን ወደ ነበረበት ለመመለስና የአካባቢን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ በተደረገው ርብርብ የበኩሉን ኃላፊነት በመወጣት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የቻለ ኃይል ነው። የሰራዊቱ አባላት ለሀገራዊ ግዳጅ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለዋል። ችግኞቹ ከሰራዊታችን ድርሻ ላይ ተቀንሶ በሚጠጡት ውኃ፣ በሚደረግላቸው ከሀገር ፍቅር የመነጨ እንክብካቤ ፀድቀዋል።

ርግጥ “ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር” ብሎ የተነሳ ህዝባዊ ኃይል፣ መነሳት ብቻ ሳይሆን ያወቀ፣ ያመነና እምነቱን ስንቁ አድርጎ ወደ ተግባር የለወጠ ኃይል ውጤታማነቱ ለህዝብ የፈፀማቸው ጉዳዩች ላያስገርሙ ይችላሉ። ምክንያቱም እነዚህ ተግባሮቹ እጅግ ከገዘፈው ስብዕናው ተቆርሶ የሚታይ ስለሆነ ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን እነዚህንና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን ህዝባዊ ክንዋኔዎች እውን የሚያደርገው በህገ መንግስቱ ላይ ባለው ፅኑ እምነት መነሻነት ነው። ይህ ህገ መንግስታዊ እምነቱ ዛሬም ይሁን ነገ የሚቀየር አይደለም። ከዚህ ፍፁም እምነቱ በመነሳትም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መገለጫ የሆነው መከላከያ ሰራዊታችን ሁሌም በህገ መንግስታዊ እምነቱ እየታገዘ የህዝቡን አደራ ሰንቆና ከህዝቡ ጋር ሆኖ ለሀገሩ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።

የሰራዊታችን ህዝባዊ ወገንተኝነት መቼም የሚቀየር አይደለም። ከራሱ በፊት ለህዝቡና ለሀገሩ ሲል ህይወቱን ለመስጠት የተሰለፈ ኃይል በምንም መልኩቢሀን የተነሳበትን ዓላማ ሊስት አይችልም። ሰራዊቱ እንደ ወታደር ህዝብና ሀገር የምትጠብቅበትን ማናቸውንም ተግባር መወጣት እንደሚችል በተለያዩ ወቅቶች ማስመስከሩ የዚህ አባባሌ መገለጫ ነው።

ሌላው ቀርቶ በቅርቡ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ለኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የቀጣናውን ሰላም ለማረጋጋት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት የሀገሪቱን ከፍተኛ ኒሻን መሸለማቸው ህዝባዊነትን ሰንቆ የጎረቤቶቹን ሰላም ለማስጠበቅ የተሰማራው ሰራዊት ማንነት ማሳያ ነው።

ርግጥ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ለጄኔራል ሳሞራ ያበረከቱት ሽልማት በእርሳቸው አመራር እየተመራ የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማረጋገጥ በተለያዩ የክፍለ አህጉሪቱ ቀጣናዎች የተሰማራው ሰራዊታችን ትክክለኛ የግዳጅ አፈፃፀሙን የሚያሳይ ነው። ሽልማቱ የሁሉም መከላከያ ሰራዊታችን አባላት በመሆኑ ለሀገርም ሆነ ለወገን ኩራት ነው። ይህ የሰራዊታችን ህዝባዊ ወገንተኝነት ከሀገር እስከ ጎረቤቶቻችን፣ ከቀጣናው እስከ አፍሪካ ብሎም እስከ ዓለም ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy