Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝብ እስካለ ድረስ ኢህአዴግም ይኖራል!

0 368

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝብ እስካለ ድረስ ኢህአዴግም ይኖራል!

                                                          ታዬ ከበደ

ኢህአዴግ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፈጠሩት ፓርቲ ነው። ከትናንት ተግባራቶቹ ዛሬ እየተማረ የመጣ ነው። በህዝብ ይሁንታንና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ለስልጣን የበቃና እንደ ገዥ ፓርቲ ስራዎቹን ከህዝብ ጋር እየተመካከረ የሚፈፅም ድርጅት ነው።

ጠንካራ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በጠንካራ አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች የሚመራና የሚደገፍ ድርጅት ነው። በህዝብ እየታረመ ለህዝብ የሚሰራ ድርጅትም ነው። እናም ይህ ህዝብ እስካለ ድረስ ኢህአዴግም መኖሩ አይቀርም።

ገዥው ፓርቲ ባለፉት 26 ዓመታት መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ችሏል። በዚህም በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለችው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያድግ ማድረግ የቻለ ነው።

በተለያዩ ቅቶች የህዝቡን አመኔታ የሚሸረሽሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይ እንደ አምናው ከህዝቡ ጋር በመሆን ተገቢውን የእርምት ርምጃ ወስዷል። ይህም የድርጅቱን ህዝባዊነት የሚያሳይ ነው። ድርጅቱ በመተካካት የሚያምን ነው።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሦስተኛው የአመራር መተካካት አሰራር መሠረት ጥቂት የማይባሉት በዕድሜ መግፋት ምክንያት የመሸጋሸጋቸው እውነታ አለ። ከዚህ ቀደምም ተኘጋሽገዋል። ይህ ሲባል ግን የእኛዎቹ ተሸጋሻጊዎች የሚገኙበት የዕድሜ ደረጃ ከሌሎች አጋሮች ጋር ሲነፃፀር የውጪዎቹ ከፍተኛውን እርከን ገና የሚወጡበት እድሜያቸው መሆኑ ነው።

የአመራር አባላቱ በገዛ ፈቃዳቸው ለተለያዩ ደረጃዎች ላለመወዳደር ሲወስኑና ይህም ይሁንታ ሲያገኝ የሚፈፀም የሦስተኛው የአመራር መተካካት አሰራር ነው። በውጪው ዓለም እምብዛም ያልተለመደው ይህ ዓይነቱ አሰራር ቀደም ሲል የተጠቀሱትን በግምገማና በአባላት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚፈፀም የአመራር መተካካትን አሊያም ሽግሽግን የሚተካ ባይሆንም ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር በመሆን ይህን ማሳካት ችሏል።

ኢህአዴግ ጥበትንና ትምክህትን የሚሸከም ጫንቃ የለውም። አገራችን ውስጥ ያሉት የጠባብነት፣ የትምክህተኝነትና እነርሱን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ መገልገያነት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መኖሩ የግድ ነው።

እነዚህ ችግሮች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡና እዚህ ሀገር ውስጥ ላለፉት 25 ዓመታት የተገኙት የልማት ትሩፋቶች የፈጠሯቸው አውዶች በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊወገዱ የሚችሉ አይመስሉኝም። ሆኖም ችግሮቹ ገዥ እንዳይሆኑና የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እጅግ አነስተኛ ማድረግ ይቻላል። በእኔ እምነት ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን ይህን ማድረግ ይችላል። ለዚህም ይመስለኛል በተለያዩ ወቅቶች በጥልቀት በመታደስ ተግዳሮቶቹን መፍታት እንደሚችል እየገለፀ የሚገኘው።

እረግጥ ኢህአዴግ “እታደሳለሁ” ካለ ይታደሳል። ይህንንም በተለይም የዛሬ 16 ዓመት ገደማ አሳይቶናል። በዚያ የተሃድሶ ወቅት በተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሀገራችንን የልማት ተምሳሌት አድርጓል።

የኢህአዴግን መስመር ዛሬ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደ “ሞዴል” እየወሰዱት ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ህዝባዊ ኃይል ነው።

የጥልቅ ተሃድሶ መንገድ ረጅም በመሆኑ እንደ ትናንቱ ዛሬም ከህዝብ ጋር ሆኖ ራሱን በጥልቀት ይፈትሻል። በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ሁከቶች በማርገብ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ድርጅቱ ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሊፈተን የሚችል ቢሆንም፤ ዋናው ነገር ችግሮቹን በተገቢው ሁኔታ ከህዝብ ጋር ሆኖ ለማለፍ ያደረገው ጥረት ነው።

ምርጫ 97 እንደ አንድ ተሞክሮ ሊነሳ የሚችል ነው። የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ምርጫ 97ትን ነፃና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት መንቀሳቀሱን እናስታውሳለን። ሆኖም የተቃውሞው ጎራ ይህን የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት በተሳሳተ መንገድ ተጠቀመበት።

ተቃዋሚዎች የህዝቡን ቅሬታዎችና ብሶቶች የማራገብ፣ ልክ እንደ አሁኑ ወቅት ‘ኢህአዴግ አብቅቶለታል’ የሚል ቀቢፀ-ተስፋዊ ስብከት እንዲሁም ፍፁም ዘረኛ በሆነ አስተሳሰብ ‘ወደ መጡበት እንመልሳቸዋለን…ምንትስ’…ወዘተ የሚሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችን እስከማራመድ ደረሱ።

ባልተገባ ሁኔታም ምቹውን የምርጫ ምህዳር ዘመቱበት። የትምክህትና የጥበት ሃይሎች በአንድነት ተቀናጅተውም የዘመቻው አካል ሆኑ። በዓለም ላይ የሚገኙ አክራሪ ኒዮ-ሊበራሎችና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ከያሉበት ዋሻ በፉጨት ተጠራርተው የዚሁ ዘግናኝ ቅስቀሳ አካል ሆኑ። የቀለም አብዮት ዘመቻም በውጭና በውስጥ ሃይሎች የጋራ ጊዜያዊ ግንባር አማካኝነት ተከፈተ።

ሻዕቢያም በበኩሉ በግንባር ላይ ያጣውን ድል በከተማ ውስጥ የጎዳና ላይ ነውጥ አገኛለሁ በሚል ቀቢፀ-ተስፋ ተንቀሳቀሰ። በስተመጨረሻም እነዚሁ ኃይሎች በፈጠሩት ሁኔታ ተቃዋሚዎች በጎዳና ላይ ነውጥ መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድና ህገ-መንግስቱን ቦጫጭቀው ለመጣል በቀለም አብዩተኞች እየታገዙ ተንቀሳቀሱ። መንግስትና ኢህአዴግ ግን ይህን በሀገር ላይ የተጋረጠ ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድና በህጉ መሰረት ለመፍታት ተንቀሳቀሱ።

በዚህም በጎዳና ላይ ነውጥ በህዝቡ ህይወትና ንብረት ላይ ለመዝመት የተጀመረው ጥረት ለማስቀረት ተችሏል። መንግስት የህዝቡን ሰላማዊ ህይወት መጠበቅ ያለበት አካል በመሆኑ በወቅቱ መወሰድ ያለበትን ርምጃ ሳይወድ በግድ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ጥረት ተደርጓል።  

በአንድ ወገን ሰላምን የማስከበር ስራ እየተከናወነ በሌላ በኩል ደግሞ ታዋሚዎች ባሸነፉበት አዲስ አበባ ያገኙትን ወንበር እንዲወስዱና በመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እንዲለመኑ ተደረገ። ይህ የሆነበት ምክንያትም እነርሱን የመረጠውን ህዝብ በማክበርና ኢህአዴግ ለህዝብ ካለው አክብሮት የመነጨ ነበር። እነርሱ ግን በእምቢታቸው ፀኑ።

በሚያስገርም ሁኔታ የመረጣቸው ህዝብ ፓርላማ ግቡ ብሏቸው የሰጣቸውን ድምፅም መልሰው ለውይይት አቀረቡት። በስተመጨረሻም አንዳንዶቹ ፓርላማ አንገባም በማለት የመረጣቸውን ህዝብ ድምፅ አሽቀንጥረው ጣሉት።…መንግስትም የህዝቡን ድምፅ አክብረው ፓርላማ ከገቡት ታዋሚዎች ጋር አብሮ መስራቱን ቀጠለ።

እንግዲህ በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ነገር ኢህአዴግ በሂደት ከችግሮች ትምህርት እየወሰደ የሚያጋጥሙትንም ተግዳሮቶች ከህዝብ ጋር በመሆን እየፈታ መምጣቱን ነው። ድርጅቱ በህዝብ የተፈጠረና ለህዝብ የሚሰራ በመሆኑ ሁሌም ህዝብ እስካለ ድረስ ስራውን ለህዝብ ያበረክታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy