Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለህዳሴያችን የሚተጋ የትምህርት ሠራዊት

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለህዳሴያችን የሚተጋ የትምህርት ሠራዊት

                                                          ደስታ ኃይሉ

በአገራችን በትምህርት ዘርፍ ላይ የሚገኘውን ወጣት እጅግ በርካታ ነው። ይህ የትምህርት ሠራዊት ወጣት ለህዳሴያችን ምቹ ምህዳርን መፍጠር የሚችል ነው። እናም ወጣቱ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ጠንክሮ በመማር የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። የወጣቱ በትምህርቱ መጠንከር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር የሚያሳልጥ መሆኑ ይታወቃል።

የዛሬው ትውልድ ወጣት እድለኛ ነው። ትምህርት በሩ ድረስ ተዘርግቶለታል። ባለፉት ስርዓቶች የጥቂቶች መጠቀሚያ የሆነው ትምህርት ዛሬ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በር እያንኳኳ ነው። ወጣቱ በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ራሱንና ሀገሩን ሊጠቅም ይችላል።

ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ቤቶች ስርጭት ኢ- ፍትሃዊነትን ለማስወገድ በአገሪቱ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሥርጭት ፍትሃዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡  ከዚህ አንፃር ቀደም የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡

በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢ-ፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ስርጭት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ እንዳይችሉ እንዲሁም የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡

በአገራችን ባለፉት 26 ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፣ የማስፋፊያ ግንባታም ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲስፋፉ በመደረጉ የተቋማቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ባለፉት 26 ዓመታት በተግባር ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ተግባር እየፈፀሙ ነው፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተስፋፍተዋል። ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያፈራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያደርጋሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፉት 26 ዓመታት በአገሪቱ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች እንዲስፋፉና ወደ 34 ከፍ እንዲሉ ብሎም ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው በመደረጉ የቅበላ አቅማቸው አድጓል፡፡

እንደሚታወቀው በኢፌዴሪ መንግስት በኩል ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ዛሬ በትምህርት ዘርፍ የተያዘው ግብ የትምህርት ጥራትን የማሳደግ እና የአገልግሎት ሽፋኑም የማጠናከር ዕቅድ ነበር። እናም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መንግስትና ህዝቡ ባረደጉት ከፍተኛ ጥረት የአንደኛ ደረጃ (ከ1-8 ) ንጥር ተሳትፎ ምጣኔ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 82 በመቶ በ2007 ወደ 92 በመቶ ከፍ ለማድረግ ተችሏል። የወንድና ሴት ሕፃናት ተሳትፎ ምጥጥን 0.94 ገደማ ደርሷል፡፡ ይኸም አፈፃፀም የምዕተ – ዓመቱ የትምህርት ግብ ለማሳካት ያስቻለ ነው።

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። በትምህርት ጥራቱ ዙሪያ ዛሬም እንደ ፈተናው መሰረቅ ዓይነት ያሉ ተግዳሮቶችን ማስወገድ ይገባልና።

የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (ከ9-10) ጥቅል ተሳትፎ ምጣኔ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 39.7 በመቶ ወደ 62 በመቶ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙም ለውጥ ሳያሳይ ባለበት መቆሙን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ስለሆነም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት እየጐረፈ ያለውን ተማሪ ለማስተናገድና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ለማሳደግ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታን ማስፋፋት የግድ ይላል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርት (ከ11-12) ጥቅል ተሳትፎ በ2002 ከነበረበት 7 በመቶ በ2007 ወደ 20 በመቶ ገደማ በማሳደግ ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን ያገኘኋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የቅበላ አቅም ከፍ ያለ ሲሆን፤ የባለሙያዎች የብቃት ምዘና በስፋት ተከናውኗል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የጥራትና አግባብነት ችግር አሁንም ጐልቶ የሚታይ በመሆኑ በቀጣይ በዚህ ዙሪያ መሠረታዊ መሻሻል ለማምጣት ከፍተኛ ርብርብ መጠየቁ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡

ዛሬ ላይ በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ በተከናወነው የማስፋፋት ሥራ በቅድመ ምረቃ የቅበላ አቅምን ወደ 400 ሺህ እንዲጠጋ አድርጎታል። በድህረ ምረቃም በኩል የቅበላ አቅም ወደ 28 ሺህ ገደማ ከፍ ብሏል። የሴት ተማሪዎች ድርሻ በቅድመ ምረቃ 32 በመቶ፣ በድህረ ምረቃ 19 በመቶ ደርሷል።

እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በዕናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ምን ያህል ርቀት እንደተየጓዘች የሚያሳዩ ናቸው።

እርግጥ ከዚህ የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች እንደሚኖሩና በችግሮቹ ሳቢያ የሚፈጠሩ የትምህርት ሥርዓቱ አጠቃላይ መገለጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው።

በመሆኑም ሀገራችን “ዕውቀት ሁሉ ከውጭ የሚገባ ነው” ከሚባልበት ዘመን ወጥታ፣ ዛሬ ላይ በራሷ አቅም የትምህርትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። በዚህም በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉ መስኮች የቅበላ አቅሟን አሳድጋለች። የዚህ ለውጥ ተጠቃሚ ወጣቱ ነው። ወጣቱ በትምህርቱ ላይ በመጠንከር የሀገሩን ውለታ መክፈል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ በያዘችው የልማት ዕቅድ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት የተማረውን ወደ ተግባር በመለወጥ የሽግግሩ የለውጥ ሰራዊት መሆን ይጠበቅበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy