Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይገባል!

0 270

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይገባል!

                                                           ታዬ ከበደ

የኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በጎበኙበት ወቅት ለተፈናቃዩቹ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። በዚህም በተለይ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ተገቢውን መፍትሔ እንደሚወስድ ገልፀዋል።

ለግጭቱ ምክንያት የሆኑ ጉዳዩችን በመለየትና አስፈላጊው የእርምት እርምጃ በመውሰድ ዳግም ግጭቱ በማይከሰትበት መልኩ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባም በአፅንኦት አስረድተዋል። መንግስትም በዚህ ረገድ ማናቸውንም ድጋፎች እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።  

እርግጥ ግጭት ለየትኛውም አገር ህዝብ የሚጠቅም አይደለም። የህዝብን ህይወት ከመቅጠፍ ንብረትንና ህይወትን ከመቅጠፍ እንዲሁም መፈናቀልን ከመፍጠር በስተቀር ለየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም።

ይህ የመንግስት አቋም ሁለሌም ገቢራዊ የሚሆን ነው። የስርዓቱም መገለጫ ጭምር። የዚህ ፅሁፍ አንባቢ ፅንፈኞች የሚያናፍሱትን አሉባልታ መመከት አለበት። እንደሚታወቀው  በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን እያውቁም ወይም ቢያውቁም ለመናገር የሚደፍሩ አይደሉም። ምክንያቱም ለእነርሱ ጥላሸት የመቀባት ሥራ ይህ ሀቅ ምንም ስለማይጠቅማቸው ነው።

ሆኖም እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ በሥልጣኔ በበለፀጉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ አይቀርም። ምን ይህ ብቻ፡፡ ሰው ከራሱ፣ በአቅራቢያው ካለውና ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱም አይቀሬ ነው።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዓለማችን ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብት እጥረት ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች አይደለችም — እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሀብት እጥረት አለባት። እናም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ ያለና ወደፊትም የሚኖር ጉዳይ ነው።

ሆኖም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ።

አንዳንዶች ይህን እውነታ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ሥርዓቱን ጥላሸት ለመቀባት ካላቸው ፍላጎት ብቻ በመነሳት ‘ፌዴራሊዝሙ ችግር እያመጣ’ መሆኑን ያለ አንዳች ሐፍረት ሊነግሩን እየሞከሩ ነው።

ግና እንደ ሟርተኞቹ እሳቤ ሳይሆን የፌዴራል ሥርዓቱ የመቻቻልና በጋራ አብሮ የመኖር ተምሳሌት እንጂ የችግር መንስኤ ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ሥርዓቱ የሀገሪቱን ህዝቦች በአንድነት በማስተሳሰር ከሰሃራ በታች ጠንካራ ምጣኔ ሃብት መገንባት የቻለና ህዝቡንም በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ሆኗል። ስለሆነም ‘የክሽፈት ዓለም’ ተቃዋሚዎች ምናብ ውስጥ እንጂ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ መሆኑን ማሳወቅ ተገቢ ይሆናል።

ከላይ እንዳልኩት ግጭት ለየትኛውም ህብረተሰብ አይበጅም። ያም ሆኖ በመንግስት በኩል የውስጥ ተጋላጭነት መንስኤን በመቀነስና የህዝቡን እርካታ በማረጋገጥ ረገድ መከናወን የሚገባቸው ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉ ግልፅ ነው። እርግጥ መንግስትና ገዥው ፓርቲ በያዝነው የበጀት ዓመት ከመልካም አስተዳደርና የመንግስት ስልጣንን የግል ኑሮ መደጎሚያ ከማድረግ አኳያ የሚታዩ ጉድለቶችን እንዲሁም ህዝቡን ለምሬት የሚዳርጉ አሰራሮችንና ተግባሮችን በቁርጠኝነት እያስተካከሉ ነው። አጥፊዎችም በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው።

እርግጥ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ውስጥ ያለው ሥርዓት ለግጭት ቦታ አይሰጥም። ለዘመናት በአንድነት የኖረ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች አገራዊ ትውፊቶች የተሳሰረን ህዝብ የራሳቸው የጥበትም ይሁን የትምክህት አጀንዳ ያላቸው ታጣቂዎችና የታችኛው እርከን አመራሮች ሳቢያ በአንድ ጀንበር የሚፈጠር መለያየት ሊኖር ስለማይችል ነው።

ወሰን ተጋሪ የሆኑት የኦሮሚያም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሊ ህዝቦችን ጨምሮ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደማቸው ዋጅተው እውን እንዲሆን ያደረጉት የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትና እርሱን ተከትሎ እውን የሆነው የሀገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለግጭት የሚሆን ቦታን የላቸውም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግጭት የሚሆን ምህዳር የሌለ መሆኑ በሕገ መንግስቱ መግቢያ በተገቢው ሁኔታ ተብራርቷል።

ህዝቦች በጋራ ሰላም የመሆን፣ በጋራ የመልማትና የማደግ፣ በጋራ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እምነትና ፈቃዳቸውን በሕገ መንግስታቸው ላይ ሳይቀርገልፀው ሲያበቁ፤ በጥላቻና ላይ በተመሰረተ የጥቂት ታጣቂዎችና የበታች አመራሮች ፍላጎት እውን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አስተሳሰቡ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ቦታ የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊፈቅዱት ስለማይችሉት ጭምርም ነው። ለዚህም ነው በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ሲናገሩ ‘እዚያ ማዶና እዚህ ማዶ ያሉት ህዝቦች መጋጨት እንደማይፈልጉ ደጋግመው ነግረውናል’ በማለት የገለፁት።     

ታዲያ እዚህ ላይ ‘የክልሎች ወሰን መካለል የለበትም’ እያልኩ አለመሆኑን ውድ አንባቢያን ግንዛቤ ይይዙልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸው መገለጫ በሆነው ሕገ መንግስት መግቢያ ላይ “…የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን…” በማለት የገለፁበት አግባብ ቀደም ሲልና አሁን ይኖሩበትና እየኖሩበት ያሉበት ወሰን ያላቸው መሆኑን ያመላክታል።

ምናልባትም በቀደምት አስተሳሰቦች ሳቢያ የተፋለሱ የድንበር ማካለል ካለም፤ ይህ ሁኔታ በራሳቸው የውሳኔ ድምፅ አማካኝነት የሚቃለል ይሆናል። ሆኖም የሁለቱም ወገን አመራር ዳተኛ በመሆን ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈፀም ካልቻለ፤ የፌዴራል መንግሥቱ በሕገ መንግሥቱ በሚፈቅድለት መሰረት ጣልቃ በመግባት የህዝብ ድምፅ ውሳኔ እንዲያገኝ ያደርጋል። መንግስት አሁንም ቢሆን ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዩችን መርምሮ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አለበት።

የግጭት አራማጆች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በተለያዩ አካባቢዎች የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል። አንዳንዴም የገቢ የሆኑ የህዝቦችን ጥያቄዎች ከመጠን በላይ በማጎንና ለግጭት መንስኤ እንዲሆን በማድረግ እኩይ ሴራቸውን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል። ይህን ሁኔታ መንግስት በአፋጣኝ በማስቆም ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy