ለፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል
ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርአት
ዮናስ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት አንቀፅ 97 ስለ ግብርና የገቢዎች ጉዳይ በግልጽ ተመልክቷል። በተለያዩ ጊዜያት ይፋ በተደረገው እና ይህንኑ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት አድርጎ በየወቅቱ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የግብር ገቢ የመሰብሰብ ስልጣን ተሰጥቶታል። በእርግጥ የግብር ገቢ መሰብሰብ ሥራ ለክልል መንግሥታትም ተለይቶ የተሰጠው የራሱ ስልጣን አለው። ሃገራችን ከተለያዩ ምንጮች ከግብር በየአመቱ የምትሰበሰበው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ቢታወቅም አሁንም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሃገራት እንኳ ሳይቀር ሁራ ስለመሆኗ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚገኘው ገቢ በሀገሪቱ አመታዊ የበጀት ምንጭ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እያያዘ በመምጣት አሁን ላይ 80 በመቶ ደርሷል። ለምሳሌ በተጠናቀቀው 2008 በጀት ዓመት መንግሥት በአጠቃላይ 106 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህም ከእቅዱ ከ91 በመቶ በላይ ነው፤ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው።
ግብር የፌዴራል፣ የክልልና የአካባቢ አስተዳደር አካላት በግለሰቦችና ህጋዊ ተቋማት ላይ ከሚያገኙት ገቢ ይከፍሉ ዘንድ የሚጣል የውዴታ ግዴታ ነው። የፊሰካል ፖሊሲ /Fiscal policy/ ዋነኛ አካል የሆነው ግብር አይነቱ ብዙ መሰረቱ የሰፋ ነው። ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆነው እስከ ወጥና አይነተ ብዙ የሚሉ ምድቦች አሉት። መንግሥት ከዜጎች በግብር የሰበሰበውን ለመከላከያ፣ ለት/ቤቶች፣ ለጤና ተቋማትና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ ወጪዎች መሸፈኛ ያውላል። የሂሳብ መዝገብ መያዝ ለመልካም የንግድ አሠራር ሥርዓት በጣም ጠቃሚና ከማንኛውም ግብር ከፋይ የሚጠበቅ፤ የንግድ አሠራር ሥርዓቱም የሚጠይቀው በመሆኑ በንግድ ሥራ ውስጥ ያለ አብይ ተግባር ሲሆን ለግብር አሰባሰብና አስተዳደር አመቺ እንዲሆን ከደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ማለትም የቁርጥ ግብር ከሚከፍሉት በስተቀር ማንኛውም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ወይም የሚከራዩ ህንፃዎች ባለቤት የሆነ ሰው የሂሳብ መዝገቦችንና ሰነዶችን የመያዝ ግዴታ እንዳለበት በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 48 ላይ በግልጽ ተደንግጓል።
ይህም ማለት ግብር ከፋዮች ተጨባጭ ወደሆነ የግብርና ታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ስርዓት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ አዋጁና ይሄንኑ ለማስፈጸም የወጣው ደንብ የሂሳብ መግለጫዎችና ደጋፊ ሰነዶችን የደረጃ “ሀ ” እና የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከደረጃ “ሐ” ከተመደቡት የቁርጥ ግብር ከፋዮች የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴና ዓመታዊ ሽያጭ እንደሚኖራቸው ታሳቢ በማድረግ ተቀባይነት ያገኘውን የሂሳብ አያያዝ መርህን መሰረት በማድረግ ዓመታዊ ሽያጫቸው ከብር አንድ መቶ ሺህ ያለበለጠ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በስተቀር ዓመታዊ ሽያጫቸው ከብር አምስት መቶ ሺህ በላይ የሆኑት የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች እና ዓመታዊ ሽያጫቸው እስከ ብር አምስት መቶ ሺህ የሚደርስ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዛግብቶችና ሰነዶችን እንዲይዙ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችም ቢሆኑ ምንም እንኳን መዝገብ የመያዝ ግዴታ ባይጣልባቸውም ለግብርና ታክስ አወሳሰን፤ የገቢያቸውን ልክ ለማወቅና ትርፍና ኪሳራቸውን ለመገንዘብ ያስችላቸው ዘንድ የሂሳብ መዝገብ ቢይዙ ተቀባይነት ያለው አሰራር ይሆናል፡፡
የግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ አያያዝ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ መርሆዎችን መሰረት ያደረገና በግብር ባለሥልጣኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አያያዝ ሆኖ ፤ የደረጃ “ሀ “ግብር ከፋዮች በየዓመቱ መጨረሻ ላይ የዓመቱን የዕዳና ሀብት መግለጫ እንድሁም የትርፍና ኪሣራ መግለጫ፤ ያልተጣራውን ትርፍ የተሰላበትን የሂሳብ አሰራር ዘዴ የሚያሳይ ሰነድ፤ የሥራ ማስኬጃና የአስተዳደር ወጪን የሚያሳይ ሰነድ፤ ስለእርጅና ቅናሽ የሚያሳይ ሰነድ እና ሌሎች ደጋፊ የሆኑ ሰነዶችን በመያዝ ለ10 ዓመታት ጠብቀው የማቆየት ግዴታ ሲኖርባቸው ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ቀንሰው የሚያስቀሩ ድርጅቶች /withhold Ajents/ ደግሞ የሂሳብ መዝገብና ደጋፊ ሠነድ በመያዝ ለ5 ዓመታት ጠብቀው የማቆየት ግዴታ የተጣለባቸው እንደሆነ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የትርፍና ኪሣራ መግለጫ በዓመቱ መጨረሻ ለግብር አስገቢው መ/ቤት በማቅረብ ገቢያቸውን በማስታወቅ ባስታወቁት ልክ ግብሩን መክፈል ያለባቸው እንደሆነም በተመሳሳይ የተገለጸ ሲሆን፤ የደረጃ “ሐ” ግብር የሚወሰነው የቁርጥ ግብር አወሳሰን ዘዴን በስራ ላይ በማዋል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ውስጥ በተመለከተው በንግድ ስራው ዓይነት፤ በንግድ ስራው ስፋት፤ የንግዱ ሥራው በሚገኝበት ቦታ ማለትም ለስራው ያለው አመችነትን ግምት በሰጠ የቁርጥ ግብር አወሳሰን ሰንጠረዥ መሠረት በማድረግ የሚወሰን የግብር መጠን መሆኑም ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ ከዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርአት ጋር ተያይዞ የየዘመኑ ሂሳብ በሚሰራበትና ሰነድ በሚዘጋጅበት ወቅት ሰነዱ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡትን አንዳንድ ነጥቦች ስንመለከት፡- ያለተጣራ ትርፍ የተሰላበት የሂሳብ አሰራር ዘዴ የሚያሳይ መሆን፤ ለዕቃ ሽያጭ ምርት ተግባር የሚውሉ ዕቀዎች ዝርዝር የያዘ፤የማምረቻና ሌሎች ዕቃዎች የዕርጅና ቅናሽ ሀብቶቹን ለመስራት ወይም እነዚሁኑ ሀብቶች ለማሻሻል፤ ለማደስ መልሶ ለመገንባት የተደረገ ወጪ፤የተወገዱ እቃዎች የሽያጭ ዋጋ፤ በተፈጥሮ አደጋ ለወደሙ ንብረቶች የተገኘ ካሣ፤ ለንግድ ስራው ንብረት የተደረገ የጥገና እና የማሻሻያ ትክክለኛ ወጪ፤የሚያሳይ መዝገብና ሰነድ፤ ማንኛውንም ግብይት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የተከናወነበት ሰነድ ወይም የንግድ ዕቃን ወደ ውጭ ለመላክ ወይም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያገለግል አንድ ህጋዊ ስነ-ሥርዓት የተፈጸመበት ሰነድ….ወዘተ የያዘ ሊሆን የሚገባው እንደሆነም በአዋጁ ተመልክቷል፡፡
ማናቸውም ግብር ከፋይ በህግ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ግብሩን አስታውቆ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ማናቸውም ግብር ከፋይ ሲባል የሦስቱም ደረጃ ግብር ከፋይ ሲሆን የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ የማሳወቅ ግዴታን በተመለከተ ሁለት አይነት አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ይታያል። አንደኛው ሀሳብ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ የማስታውቅ ግዴታ አለበት ሲል ሌላኛው ክፍል ግን ይህ ደረጃ የቁርጥ ግብር ከፋይ በመሆኑ ገቢው ለውጥ እስከሌለው ድረስ ማስታውቅ ግዴታ ሳይኖርበት በቁርጥ ግብሩ ልክ ግብሩን መክፈል ሆኖ የማስታወቅ ግዴታ የተጣለበት ግን የገቢ ግብሩ ደንብ ቁጥር 78/1994 አንቀጽ 22 መሠረት ሦስት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ማለትም በበጀት ዓመቱ ያገኘውን ጠቅላላ ገቢ፤ ከመደበኛ ስራው በስተቀር ከሌላ ምንጭ ያገኘውን ገቢ እና ይሠራው የነበረውን መደበኛ የንግድ ሥራውን የለወጠ ከሆነ አዲሱን የንግድ ስራ ዓይነት ለግብር አስገቢው ባለሥልጣን የማስታወቅ ግዴታ ተጥሎበታል እንጂ በገቢ ግብር አዋጁ መሰረት ለሚጣልበት ቁርጥ ግብር ግን የማስታወቅ ግዴታ ሊኖርበት አይገባም የሚል ልዩነት ነው፡፡
እዚህ ላይ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ደንቡ ‹‹በበጀት ዓመቱ ያገኘውን ጠቅላላ ገቢ›› ሲል የቁርጥ ግብሩን ገቢ ብቻ ማለቱ አለመሆኑን እና ሌላ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ሲችል ማስታወቅ እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ ግብር ከፋዩ ግብሩን በቁርጥ ግብር እንዲከፍል ውሳኔ ላይ ደርሶ የቁርጥ ግብር ከፋይ ሊስት ውስጥ ካስገባው ከግብር ከፋዩ የሚጠብቀው በተጣለበት ቁርጥ ግብር ልክ የቁርጥ ግብሩን መክፈል ሲሆን፤ ማስታወቅ የሚገባው ከቁርጥ ግብሩ በላይ ገቢ ስለማግኘቱ ወይም ገቢው ከሚከፍለው የቁርጥ ግብር በታች ሆኖበት ኪሳራ ያጋጠመው ሲሆን እንጂ በገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ ተጠንቶ የተጣለበትን ቁርጥ ግብር መልሶ ማስታወቅ ማለት አይደለም፡፡
ግብር ከፋዩ በቁርጥ ግብር ከተወሰነበት በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱን በራሱ ካወቀ ከቁርጥ ግብሩ በላይ ያገኘውን ገቢ እና ቁርጥ ግብሩን በመለየት ማስታወቅ ያለበት መሆኑን ለማመልከት ሆኖ በቁርጥ ግብሩ ልክ ከሆነ ግን የማስታወቅ ግዴታ የሌለበት መሆኑን የሚያጠይቅ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርአት መርሆዎ ግብር ከፋዩ የዘመኑ ገቢው ከቁርጥ ግብሩ በታች ከሆነበትም ሊያስታውቅ ይችላል። ይህም ማለት የዘመኑ ገቢው ማነሱንና ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ ከተወሰነበት የቁርጥ ግብር ሊቀነስለት ስለሚያስችለው ነው። ይህም የሚያገለግለው ለሁለት አላማ ሲሆን አንደኛው ግብር ከፋዩ የቁርጥ ግብር ተወስኖልኛል በሚል ግብሩን አሳንሶ እንዳይከፍልና የተሻለ ገቢ መኖሩን እያወቀ ገቢውን ደብቀሃል ተብሎ ቅጣት እንዳይጣልበት ለመከላከል እና ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱም የተሻለ ገቢ ግብር ከፋዩ ማግኘቱን ካወቀ የግብር ከፋዩን ደረጃ ሊያሻሽል እንዲያስችለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ግብር ከፋዩ ገቢው ከወትሮው ያነሰ መሆኑን ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቱ በተጨባጭ ከተረዳ ተወስኖበት የነበረውን ቁርጥ ግብር በማሻሻል ከታወቀው ገቢ ጋር የተመጣጠነ ቁርጥ ግብር ለመወሰን እንዲያስችለው እንደሆነ መርሁ ያስቀምጣል፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ አግባብ እየተመራ እንደማይገኝ በብዙ ጥናቶች የተረጋገጠበት የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ህዝቡን ኢፍትሃዊ ለሆነ የሃብት ክፍፍል በመዳረግ ረገድ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ጥናቶቹ ያረጋግጣሉ።
በተሟላ መልኩም ባይሆን ከቁሳቁስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሰው ሃይል አንጻር ለዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ስርአት የተመቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ቢሆንም በግብር አስተደደር ስርዓቱ ውስጥ ኪራይ ሰበሰቢነትን ከመድፈቅ፣ መሰብሰብ ያለበትን ገቢ ከመሰብሰብ እና ፍትሃዊነትን ከማስፈን አኳያ በየደረጃው ባለው አመራርም ሆነ በባለሙያዎች ዘንድ ያልተቀረፉ በርካታ ጉድለቶች የሚታዩ መሆኑን የመያመለክቱት መረጃዎች እነዚህ ችግሮች በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በመፍጠር ህዝቡ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረጉት እንደሆነም ያስቀምጣሉ።
በጥናት የተደገፉት እነዚህ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በፌዴራሉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከጉምሩክ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ በወደብ፣ ደረቅ ወደብና በአውሮፕላን ማረፍያ አካባቢ የሙስና፣ የስራ መጓተትና ኢ-ፍትሃዊ ትመና በስፋት እንደሚታይ እንዲሁም ከገቢ ግብር ትመና ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ነጋዴ ላይ ከፍተኛ የግብር ግምት የሚጣልበት፤ በተቃራኒው ደግሞ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ነጋዴ ላይ አነስተኛ የግብር ግምት የሚጣልበት ሁኔታ በስፋት መኖሩ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥፋት ያጠፉትን ተመሳሳይ ቅጣት አለመቅጣት ኪራይ ሰብሳቢነት በግልጽ እንደሚፈጸም ያሳያሉ። በጥናቶቹ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጉምሩክ ስርዓቱ ባለጉዳይን ማስተናገድ ላይ የሚታይ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ሠነድ በፍጥነት አለመበተን፣ ታሪፍ እያሳሳቱ ያልሆነ ቀረጥና ታክስ መጠየቅ፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መደራደርና ከጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር ተመሣጥሮ መስራት የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎች ናቸው፡፡
አንዳንድ አመራሮች በገቢ አሰባሰብ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን ተጠቅመው ጣልቃ በመግባት አለአግባብ ጥቅም ለማግኘት የመሻት፣ አድልዎና ኢፍትሃዊ ተግባራት በፍትሃዊ የንግድ ውድድር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳረፉ መሆናቸውን በጥናቶቹ የተገኙት መረጃዎች አሳይተዋል፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ አመዘጋገብ ላይ አንዱን መመዝገብ ሌላኛውን ችላ ማለት ይታያል፡፡ በተጨማሪም ዝቅተኛው ግብር ከፋይ ከሞላ ጐደል ወደ ስርአት የገባ ቢሆንም በከፍተኛው ግብር ከፋይ የግብር ስወራ እንዳለ በተለይ የፖሊሲ ጥናት ማእከል ጥናት በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች ተዟዙሮ ባደረገው ጥናት አረጋግጧል።
መሃንዲሶች ቢል ኦፍ ኳንቲቲ አጋንነው በመፃፍ የቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚዎች የንግድ ሰርአቱን ወደሚያዛባ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ይደግፋሉ፡፡ ከቀረጥ ነፃ መብትን ለህገወጥ መንገድ የሚያውሉትን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ላይም በገንዘብና በትስስር ከህግ ስለሚያመልጡ በቁርጠኝነት ለመታገል የሚደረገው ጥረት ደካማ ሆኗል። በተመሳሳይ አየር ባየር ነጋዴዎች ለህግ ቢቀርቡም በአፋጣኝ አይቀጡም፡፡ በአማራ ክልላዊ መንግስትም በግብር አስተዳደር በተለይ በቁርጥ ግብር ውሳኔ፣ በግብር ከፋይ ደረጃ ሽግግር፣ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት ምዝገባ እና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ መጠቀም ያለባቸውን አንዲጠቀሙ ከማድረግ አኳያ በአመራሩና በባለሙያው አድሎ የሚፈጸም መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል።እነዚህ ጥናቶች ከላይ ከተመለከተው የዘመናዊ የግብር አስተዳደር መርሆዎ አኳያና በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖም ከላይ ለተመለከቱት ችግሮች መንስኤዎቹን ለይተው አስቀምጠዋል።
ዋነኛው መንስኤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በመዋቅሩም ሆነ በህብረተሰቡ ውስጥ የተንሰራፋ መሆኑ፤ የተጠያቂነት ማነስና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የሚደረገው ትግል ያዝ ለቀቅ የበዛበትና በሙሉ ልብ የማይካሄድ መሆኑ ነው። በርከት ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች በጥቅም ትስስር የተነካኩ ወይም አድርባይነት የተጠናወታቸው በመሆናቸው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን በቁርጠኝነት ለመቀላቀል የማይደፍሩ አንዳንዴም በፀረ ዲሞክራሲ መንገድ የመታገያ መድረኩ እንዲጠብ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው።
ሌላው መንስኤ በዘርፉ ያለው በርካታ አመራር ምደባውና ስምሪቱ ለዘርፉ የሚመጥን ፖለቲካዊና ሙያዊ ብቃት እንዳለው በሚያረጋግጥ መንገድ አለመሆኑ፤ ብቃቱን ለማዳበርም በቂ ጥረት የማያደርግ በመሆኑ ያለበት የብቃት እጥረት በስራው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳረፉ ነው። ከዘርፉ ውጪ የሚገኘው አብዛኛው አመራርም በግብር ማሰባሰብ ስራው ላይ ትክክለኛ አመለካከትና ዕውቀት ባለመያዙ የግብር መሰብሰብ ስራን ከፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጡ ጋር አስተሳስሮ ከማየት ይልቅ ተራ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ አድርጎ በመመልከት፤ በግብር ማሰባሰብ ሂደት የሚደረገውን ትግል በትክክለኛ ይዘቱ አለመገንዘብና በዚህም ምክንያት ተቀናጅቶ ለመስራት የተነሳሽነት መጓደል ነው። ሌላው መንስኤ የገቢና ሌሎች የለውጥ ተግባራት የግብር ስርዓቱን ከመሰረቱ በመለወጥና የህብረተሰቡን ግንዛቤ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ በድምር ውጤታቸው ለፖለቲካል ኢኮኖሚው ለውጥ ያላቸውን ጠቀሜታ በአግባቡ ተገንዝቦ በተሟላ ቁርጠኝነትና የህዝባዊ ወገንተኝነት መንፈስ ለመፈፀም ባለመፈለግ ወይም በግብር ይውጣ መልክ በመንቀሳቀስ የሚገለፅ ነው። ሁሉም ጥናቶች የግብር አስተዳደር ስርአቱን በማዘመን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ የሚቻልባቸው የቅርብና የረዥም ጊዜ የሆኑ ወሳኝ የመፍትሄ ሃሳቦችን ጠቁመዋልና በዛው አግባብ መስራት ያስፈልጋል።
በገቢዎች ዘርፍ የሚታየውን የኪራይ ሰበሳቢነትና ኢፍትሃዊነት ችግር ለመፍታት የአሰራር ጉድለቶችን በጥልቀት በመፈተሸ በተለይም በዘርፉ ከፍተኛ የግብር ስወራ የሚካሄድባቸውን መስኮች በማጥናት የሚፈፀመውን የታክስ ማጭበርበር ሊገቱ የሚችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረግና ሌሎች ዘርፉን የማጥራት ርምጃዎች መውሰድ ይገባል፡፡
በዘርፉ የሚታየውን የመፈፀምና የማስፈፀም ጉድለቶች ለማስተካከል ከአጭር ጊዜ አኳያ አሁን ያለውን አመራርና ባለሙያ ሁኔታ በመገምገም አፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ ይጠይቃል። ከረጅም ጊዜ አኳያ ደግሞ ችግሮቹን በጥናትና ምርምር እየለየ የምክር እና የስልጠና አገልግሎት የሚሰጥ የታክስ ኢንስቲትዩት ማቋቋም ይገባል፡፡
በዘርፉ ያለውን የመረጃ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የመረጃ ስርዓቱን ማዘመን ይጠይቃል፡ ስለሆነም የታክስ ስርዓቱንና አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ተክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግና የመረጃ ልውውጡ ፈጣንና አስተማማኝ እንዲሆን ለማስቻል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ የግድ ይላል።
በጥቅሉ የታክስ አስተዳደር ህጉን በሁሉም አካባቢዎች ወጥነት ባለው መንገድ ተግባራዊ በማድረግ እና ስርአቱን በማዘመን ልማትን ማፋጠን እና ከተገኘው ልማት እኩል ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት እድል ሰፊ ነውና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በተቀናጀ መንገድ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡