Artcles

ልዩነቶችን በማቻቻል እንጂ በማስፋት አንድነት አይጠነክርም!

By Admin

October 30, 2017

ልዩነቶችን በማቻቻል እንጂ በማስፋት አንድነት አይጠነክርም!

አባ መላኩ

ኢትዮጵያ ወደ ሰማንያ  የሚጠጉ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባት በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች የሚስተዋሉባት፤ ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምስራቅ አፍሪካ  ቀጠና የምትገኝ አገር ናት። ኢትዮጵያችን በዚህ  አስቸጋሪ  በሚባለው የምስራቅ አፍሪካ  አካባቢ  የሰላም ደሴት ለመሆን የቻለችው  የህዝቦቿን   ልዩነቶችና ፍላጎቶች  አጣጥማ መኖር የሚያስችላት የፌዴራል ስርዓት መተግበር በመቻሏ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ የህዝቦች  የዘመናት  ጥያቄዎች የሆኑት እኩልነት፣ ሰላምና ልማት  የተረጋገጡት በዚህ የፌዴራል ስርዓት ወቅት ነው። እንደእኔ እንደኔ ፌዴራሊዝም   ለአዲሲቷ  ኢትዮጵያ   የህልውናዋ  መሰረት ነው።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰላማችንና  የልማታችን  መሰረት  የሆነውን  የፌዴራል  ስርዓት አያያዙን ያወቅንበት  አይመስልኝም “በእጅ የያዙት  ወርቅ…” እንደሚባለው  ሆነና  የአንዳንዶች  አካሄድ  ለሁላችንም የማይበጅ፣ የሁላችንንም ቤት የሚበትን  አይነት ሆኖ አገኝቼዋለሁ።  እንደኢትዮጵያ ላሉ  በርካታ ልዩነቶች የሚስተዋሉበት አገር  የፌዴራል ስርዓት  መከተል  ብቸኛው አማራጭ  ነው።  አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከፌዴራል ስርዓቱ ውጪ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም። “አንድ አይና በአፈር አይጫወትም”  እንደሚባለው እኛም አካሄዳችንን በአግገባብ ብንመዝነው መልካም ይመስለኛል። ይህ የፌዴራል ስርዓት ችግር እንዲገጥመው የሚደረገው ሩጫ ለማንም የሚበጅ አይመስለኝም።      

 

በደርግ መንግስት ውድቀት ማግስት በርካታ ታጣቂዎች አሰፍስፈው በነበሩበት ወቅት  ኢትዮጵያ የነበሯት አማራጮች ሁለት ነበሩ። የመጀመሪያው  ብዝሃነትን  ማስተናገድ የሚችል  ያልተማከለ  አስተዳደርን   በመተግበር  ስልጣን ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ማከፋፋል   አሊያም እንደቀድሞ መዕከላዊነትን  በማጠናከር  በነውጥና ሁከት በመቀጠል  ወደማይቀረው መበታተን መግፋት ነበሩ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መክረውና ዘክረው በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት መመሥረት የሚያስችላቸውን  የፌዴራል ስርዓት  በመከተላቸው  በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም አስፍነዋል፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማጠናከር  አገሪቱንም ከመበታተን ታድገዋታል።  

 

ብዝሃነትን በአግባብና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ ነው።  የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን  ተቀብሎ  ዴሞክራሲያዊ  በሆነ  ሁኔታ ማስተናገድ  የሚችል ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የሥርዓቱ ዋልታና ማገር በመሆን በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነትን የሚያጠናክር የአንድነት ማሰሪያ ገመድ ነው። ብዝሃነት በህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ የሚኖር  ትልቅ አሴት ነው።  የፌዴራል ሥርዓታችን ብዝሃነትን ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ የአገሪቱ ሠላም በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሰረት መልካም እድል ፈጥሯል። ብዘሃነትን ማስተናገድ ማለት ልዩነቶችን በማክበር  አንድነትን በማጠናከር  አብሮ መኖር ማለት ነው።

 

በአገራችን በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች  ይንጸባረቃሉ። እነዚህን አጣጥመን መጓግዝ የግድ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን ደፍጥጠን  በሃይል አንድነት እናመጣለን የሚባልበት ወቅት አይደለም። ይህን ሁላችንም ልንገነዘበው ይገባል። ባለፉት ስርዓቶች በአገራችን ይስተዋል የነበረው ቀውስ ምክንያቱ ይታወቃል። በመሆኑም ብዝሃነታችንን ሊያስተናግድ የሚችል ስርዓት መከተል አንድነታችንን ማጠናከር ነው። አብሮነታችንን አጠናክረን ለመቀጠል ያለን ብቸኛ አማራጭ በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን አንድነት ማጎልበት ነው።

 

የጽንፈኛው  ሃይል የፖለቲካ አካሄድ ልዩነቶችን በማስፋት ህዝብን ማጫረስና አገርን መበተን ነው። ህዝቦችን በማታኮስ፣ ህዝቦችን  በማጋደልና በማራራቅ  የፖለቲካ ትርፍ  ለማግኘት የሚደረግ መሯርጥ ምን ያህል የወረደ አስተሳሰብ እንደሆነ  መገመት አይመስለኝም። በተንደላቀቀው የምዕራብ አገር ተቀምጦ ስሜት ቆስቋሽ የሆኑ መረጃዎችን በመልቀቅ ወጣቱን  ለጭፍጨፋና ለዝርፊያ  ፋኖ ተሰማራ ማለት ምን ያህል ዘግናኝ ተግባር እንደሆነ መመልከት ይቻለል።  በመደጋገፍ፣  በመተባበርና  በመተሳሰብ  እንጂ  ልዩነትን  በማስፋትና እርስ ስበርስ  በመገፋፋትና በመጠላለፍ ለህዝቦች ጥቅምና ለአገር እድገት የሚያመጣው አንዳችም  መልካም ነገር  የለም። የመጣንበት 27 ዓመታትም  የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው። በቀል ማንንም አሸናፊም  ሆነ  ተጠቃሚ አድርጎ አያውቅም።

መንግስት ልዩነታችንን ሊያሰፉ ህዝብን  ሊያራርቁ  የሚሯሯጡ  ሃይላትን  ከህዝቡ ጋር በመተባበር ህግ ፊት ሊገትራቸው ይገባል። ይህ ነገር ከመፈክር አልፎ በተግባር  ልናየው እንፈልጋለን። ክብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሲገልጹት እንደነበረው ማንኛውም አካል ግጭት በመቀስቀስ  ወይም  ግጭት እንዲባበስ  ያደረገ ከህግ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ አስረግጠው የተናገገሩትን  በተግባር ማየት እንፈልጋለን። ምክንያቱም የፌዴራል ስርዓታችን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ እስትንፋስ ነው።  የህልውናችን  መሰረት የሆነውን የፌዴራል ስርዓታት ሊያፈርሱ አገራችንን ሊበትኑ የሚሯሯጡ የጥፋት ሃይሎች የሆኑትን  ጸረ-ሰላሞች፣ ጸረ-ህዝቦች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጠባቦችና ትምክህተኞች የምንታገሳቸው? ካልደፈረሰ አይጠራም እንደሚባለው በየዋሻው መሽገው የሚያጠቁንን ሃይሎችን ለህግ ልናቀርባቸው ይገባል።

 

እነዚህን የጥፋት  ሃይሎች ለህግ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለድርድር እንደማይቀርብ አንድ ማሳያ አድርገን  ልናቀርባችው ይገባል። አዎ ማንኛውም  አካል  ለዚህ ግጭት ምክንያት  የሆነ ሁሉ ከህግ ፊት ቀርቦ  ማየት እንፈልጋለን። ይህ ሲሆን ሌላውም ትምህርት ያገኛል፤ የጥፋት እጁንም ይሰበስባል።   ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው አንዳንዶች የህዝብን ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ ህገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ  ይቆዩና  ተመልሰው  ህዝባዊ ሆነው ለመታየት ይሞክራሉ።

 

ከጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ባሻገር በዚሁ በአገራችን ያሉ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሸሸጉ ጥቅመኞች ለህዝብና  አገር  ተቆርቋሪ  በመምሰል  አንዱን ብሄር  ተጠቃህ፣ ወገኖችህ አለቁ  ድርስላቸው ወዘተ በማለት  በግጭቶች  ላይ ቢንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። አንዳንድ ሚዲያዎችም የወቅቱን ነበራዊ ሁኔታዎች በቅጡ አልተረዱትም አሊያም ግጭቶቹን በማራገብ የሚያገኙት ጥቅም ያለ በሚመስል ሁኔታ የግጭት ቆስቋሽ ሆነዋል። መንግስት እነዚህን የጥፋት ሃይሎች  በአግገባብ  በመለየት ሁሉም እንደየጥፋቱ  ተጠያቂ  የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል። ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  በአጥፊ ሚዲያዎቻቸውና  በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያሰራጫቸው  መርዘኛ መረጃዎች ለህዝቦች አብሮነት የማይበጅ የአገሪቱን አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጥ እጅግ የወረደ ተገባር ነው።  

 

የፌዴራሊዝም ስርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻልና መከባበርን ነው። ይሁንና ይህን እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነው። ህዝቦችን በማጋጨት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ  ለማንም አይበጅ። ወክለዋለሁ ለሚባለው ብሄርም  ቢሆን  በመደጋገፍና በመተሳሰብ  አብሮ በመኖር እንጂ  በመነቋቆር  የሚገኝ  አንዳችም ትርፍ የለም።  በዚህ የጥፋት ድርጊት የተሰማራም ሆነ የጥፋት ሃይል  ያሰማራ  ማንኛውም  አካል  መጠያቅ ይኖርበታል። ችግሮችን  በመነጋገገርና  በመወያየት መፍታት ይቻላል። አገራችን ድንበር ተሻግራ ለጎረቤት አገራት ቀውሶች መፍትሄ በመስጠት ላይ ባለችበት ሁኔታ የገዛ አገራችን ህዝቦች ለግጭት መዳረጋቸው አሳፋሪ ነው።    አገራችን ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት ዓለምን ያስደመመ  ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓቷንም ለማጎልበት ደፋ ቀና ማለት የቻለችው  ሰላም በመሆናቸን  ነው።

 

በአገራችን የፌደራሊዝም  መርሆዋችና እሴቶችን በአግባቡ በመፈፀም ላይ ውስንነቶች ቢታዩም እንዲህ ያለ ህዝብን  ለመጉዳት ታስቦ የሚደረግ እንቅስቃሴዎችን ግን  የፌዴራል ስርዓቱ ክፍተቶች ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የፌዴራል ስርዓታችን የቡድኖችን መብት ብቻ ሳይሆን  የግለሰቦችንም ማንኛውንም መብት ማረጋገጥ የሚያስችል  ስርዓት ነው።   በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በህዝቦች መካከል  የተከሰቱ ግጭቶች ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም በፌደራል ስርዓታችን ጉድለት ሳቢያ የተከሰቱ  ችግሮች እንዳልሆኑ ግን  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም  የፌዴራል ስርዓታችን ባለፉት 26 ዓመታት አገራችንን በስኬት ጎዳን እንድትረማመድ  አድርጓታል።