ሕዝብ ከሕዝብ አይጋጭም
ይልቃል ፍርዱ
ካገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ እንደምንረዳው፣ ሕዝብ በሰላም፣ በፍቅርና በመቻቻል ነው የኖረው፡፡ ወደፊትም በዚሁ መልክ መኖሩ ይቀጥላል። በማንኛውም ግዜ የሚነሱ ግጭቶች ግለሰቦችን ወይንም የፖለቲካ ቡድኖችን መነሻ ያደረጉ እንጂ ሕዝብ ከሕዝብ በየትኛውም የታሪክ ዘመን ተጋጭቶ አያውቅም፤ ሊጋጭም አይችልም፡፡ ግጭት የሚያስነሱት ሁከት የሚቀሰቅሱት የጥበት፣ የትምክሕት፣ የዘረኝነትና የጎጠኝነት ካንሰር በሽታ የተጠናወታቸ ክፍሎች ናቸው፡፡ ጥላቻን በመዝራት የሚሰብኩት፣ ሕዝብን ለተለያየ ጥፋት የሚቆሰቁሱት ግለሰቦችና የተለያዩ አክራሪና ጽንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች ናቸው፡፡
ይህ እውነት በአፍሪካም፣ በላቲን አሜሪካና አውሮፓም ታይቶአል፡፡ እንዲህ አይነቱ ደካማ አስተሳሰብ ለሀገርና ለሕዝብ የማይበጅና የማይጠቅም እጅግ ኋላ ቀር ፖለቲካ ከመሆኑም ባለፈ የሀገርን ውድመት የሕዝብን ጥፋት ከመጋበዙ ውጪ ሀገር ሲያለማ ሕዝብን ሲታደግ አልታየም፡፡ የቀድሞው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር የጎሳ ፖለቲካን የ12ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ይሉታል፡፡
አለም አድጎ ወደላቀው የእድገት ደረጃ በተስፈነጠረበት በዚህ ወቅት የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ሊከበር ነው የሚገባው፡፡ የሰው ልጅ ዘር፣ መንደርና ጎጥ ቆጠራ ላይ ከወረደ የመጨረሻው ኋላቀርና ደካማ አስተሳሰብ ጨለማ ውስጥ ያለ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ዘረኝነትም ሆነ ጎጠኝነት አስከፊ የካንሰር በሽታ ነው፡፡ ለሀገርና ለህዝብም ጠንቅ ነው፡፡ አብሮነትን አንድነትን መከባበርና መቻቻልን የሚንድ ታላቅ ጥፋትንም የሚያስከትል ነው፡፡
የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ መከበር አለበት፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የተከበሩ ሰብአዊ መብቶች አሉ፡፡ የትም ሄደ የትም በነጻነት የመስራት፣ የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራት፣ ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የፈለገውን የፖለቲካና የኃይማኖት እምነት የመከተል፣ በነጻነት የመደራጀት . . . የማይጣስና የተከበረ መብት አለው፡፡
አለም ወደ አንድ መንደርንት እየጠበበች ባለችበት ከአፍሪካና ከኤሽያ ወደ አውሮፓ ተሰደው የሄዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አውሮፓን በሞሉበት፤ ሰርተውም ሆነ ዜግነት አግኝተው በሚኖሩበት በዚህ ዘመን ከአለም አጠቃላይ ተጨባጭ እውነት ጋር የማይራመዱ እጅግ ኋላቀር የሆኑ ፖለቲከኞች በሚቆሰቁሱት የጎሳና የዘር ፖለቲካ ተነሳስቶ መፋጀት፣ መጋደል አንዱ ሌላውን ከክልሌ ለቀህ ውጣልኝ ማለት ይህ አይነቱ ሁኔታ በሀገራችን መከሰቱ እጅግ አሳዛኝ፤ ጸያፍ ድርጊት ነው፡፡ በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያውያን በእጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች ወገን እርስ በእርሱ በዚህ መልኩ ሲተራመስ ማየት ሕሊናን የሚያቆስል አስከፊ ሁኔታ ነው፡፡ ሠ
ሀገራችን ሰፊ፣ ለምና እጅግ ሀብታም ናት፡፡ ገና በሚፈለገው መጠን ሰርተን አልተጠቀምንባትም፡፡ ትልቁ ችግራችን አስከፊው ድህነት ነው፡፡ እንኳን እርስ በእርስ ለመባላትና ለመፋጀት ቀርቶ ገና ብዙ ያልተወጣናቸው አፍጠው የሚጠብቁን ከድሕነት ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች አሉብን፡፡ ለእርስ በእርስ መባላት የምንሰጠው ምንም አይነት ግዜ የለንም፡፡
ይሄንን አጀንዳ አድርገው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ አላማቸው አድርገው የሚያራምዱ ጸረ ሕዝብና ጸረሀገር ክፍሎችን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩና ለሕዝቡ ሰላም ሲል ጸንቶ ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ከድሕነት ለመውጣት ታላቅ ተጨባጭ ተግባራዊ ስራዎችን በመስራት በመሰረተ ልማት በኢኮኖሚ እድገት ታላላቅ ስራዎች የሰራች፤ በመስራት ላይ ያለችና ታላቅ የእድገት ተስፋ የሰነቀችውን ሀገር ከጀመረችው ታላቅ ጉዞ ለማሰናከል እድገትዋን ለመግታት ተመልሳ የጦርነት አውድማ እንድትሆን ለሚመኙ ክፍሎች በር መክፈት አይቻልም፤ ማንም እውነተኛ ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ዜጋም ይህ ይሆን ዘንድ አይፈቅድም፡፡
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች በመንግሰትና በሕዝብ እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በርካታ ምክክሮችም በስፋት እየተካሄዱ ሲሆን ጥልቀት ያላቸው ሕዝባዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ችግሩን ነቅሶ በማውጣት መንስኤዎቹን አጣርቶ ለይቶ በማወቅ ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ መስራት ለነገ የማይባል የዛሬ ስራ መሆን ከመገባቱ አንፃር ይህ ተገቢ ስራ ነው፡፡
ብቸኛው አማራጭ ጉዳዩን ባለቤቱ ከሆነው ሕዝብ ጋር በቅርበት ተነጋግሮ ተወያይቶ መርምሮ ሰላማዊ እልባት መስጠት መቻል ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ግጭቱ ተከስቶ በነበረባቸው አካባቢዎች መረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ተጀምሯል፤ በግጭቶቹ አካባቢዎች ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፤ የበለጠ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠርም እየተሰራ ይገኛል፡፡
ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በመንግስትና በሕዝቡ ትብብር ሰፊ ርብርብ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ መንግስት ለተፈናቃዮች ከሚያደርገው እገዛና እርዳታ ውጪ ለተፈናቃች የሚደረገው ሕዝባዊ እርዳታ የማሰባሰብ ፕሮግራም በሰፊው ቀጥሎአል፡፡ እርዳታው ለሁሉም ተፈናቃይ ዜጎች የሚደርስበትን መንገድ ማቀናጀት አስፈላጊ ነው የሚሆነው፡፡
ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተፈጠረውን የስነ ልቦና ችግር ለመፍታት ግዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ችግሩን በሂደት የማስተካከል ስራ በሰፊው መሰራት አለበት፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እየጠነከረ እየጎለበተ መሄድ ይገባዋል፡፡ በሁለቱም ወገን የተጎዱት የተፈናቀሉት ዜጎቻችን በመሆናቸው እገዛውና እርዳታው ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ ሊሆን ይገባል፡፡
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት እንደቀውስ በመመልከት ቀውሱን ለበጎ ስራ ልንጠቀምበት ወደሚችል መልካም አጋጣሚ የመቀየር ለሕዝቦች ይበልጥ መቀራረብ፣ መረዳዳት፣ መተጋገዝ፣ ችግሮችንም በጋራ ለመፍታት የሚያስችል አቅም ከዛሬው ተምረውና ልምድ አግኝተውበት ወደፊት እንዳይደገም ለማድረግ የሚያስችል፤ በመቀራረብና በመነጋጋር ላይ ተመስርቶ ችግሮችን ሁሌም በሰለጠነ አግባብ እንዲፈቱ የሚያስችል አቅም መገንባት ይጠበቅብናል፡፡
ቀደም ሲል እንደጠቀስነው በሕዝቦች መካከል መቼም ሆነ መቼ እንደዚህ የከፋ ችግር ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ የችግሩ ምንጮች ሁሌግዜም ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡ ይህ በስሜታዊነት፣ በጀብደኝነት፣ በእብሪት መነሻነት የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት የሚያደፈርስ ግጭት እንዲከሰት የሚያደርግ የሕይወት መስዋእትነት የሚያስከፍል፣ ከመኖሪያ ቀኤና ደጅ የሚያፈናቅል እኩይ ድርጊት የግድ ሊገታ ይገባዋል፡፡ ተጠቃሚ ማንም አይኖርም፡፡ የሀገር ጥፋትና ውድመት ብቻ ነው የሚያስከትለው፡፡ አይጠቅመንም፡፡
የምን ግዜም የሕዝቦች የጋራ ፍላጎት ሰላምና ሰላም ብቻ ነው፡፡ ከግጭት ተጠቃሚ አትራፊ ማንም ወገን ሊኖር አይችልም፡፡ ይህንን ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የግጭት ፍላጎትና አላማ የለውም፡፡ ሊኖረውም አይችልም፡፡ የተፈጠረው ችግር ይፈጠራል ተብሎ የማይታሰብና የማይገመት የነበረ ቢሆንም ችግሩን አምኖ በመቀበል በጊዜያዊነትም በዘላቂነትም ለመፍታት ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ሁሉም ሕዝብ የሚፈልገው ቀዳሚ ጉዳይ የሀገሩን ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ ዋናው አጀንዳው ሰላምና ሰላም ብቻ ነው፡፡ ከሰላም በላይ ለአንድ ሀገር ታላቅና ውድ የሆነ ነገር የለም፡፡ የትኛውም ብሔር ወይም ድርጅትና ፓርቲ ከሰላም ተቃራኒ የሆነ አጀንዳ ይዞ ቢነሳ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሕዝብ የሀገሩን ሰላም ከምንም ነገር በላይ ነቅቶ ይጠብቃል፡፡
በሁለት ክልሎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የሁለቱ ክልሎች ብቻ አድርጎ መውሰድ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሰፊ መስተጋብርና ትስስር ባለበት ሀገር የአንዱ ወይም የተወሰኑ ክልሎች ችግር ውስጥ መግባት ሀገራዊ ችግር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በአገር ደረጃ የተፈጠረ ችግር ስለሆነ ሊፈታ የሚገባውም ይሄንኑ መሰረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡ መላው ሕዝባችን ተረባርቦ ሊገታው፤ ሊቆጣጠረው ይገባል፡፡
የሀገርን ሕልውና ለአንድነቱ ጸንቶ በመቆም የሚጠብቀው ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ከሕዝቡ ውጪ ስለሀገሩ ሰላምና አንድነት የሚመለከተው ማንም የለም፤የ ሀገሩን አንድነት የሚጠብቅም እንደዛው፡፡ ለዚህ ግጭት መነሳትና አድማሱን ማስፋት እጃቸው ያለበት አካላት ተጠያቂ ከመሆን ሊድኑ የማይገባ መሆኑ የህዝብ ፍላጎት ነው፡፡
ችግሩን ከመፍታትና ከማርገብ ባሻገር ግጭቱን ለማባባስ በተለያየ መንገድ መስራት በመገናኛ ብዙሀንም ሆነ በማሕበራዊው ሚዲያ ከመቀስቀስ ተግባር መታቀብ ይገባቸዋል፤ ከጥፋት በስተቀር የሚገኝ ትርፍ ሀገራዊ ወይም ሕዝባዊ ጥቅም የለውምና፡፡
በአሁኑ ሰአት፣ ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የፌዴራሉ መንግስት ተወካዮች ችግሩን ለመፍታት ሰፊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሰላማዊ እልባት ለማስገኘት የሚሰራ ስራ፤ ሁሉም ወገን ሊደግፈው ይገባል፡፡ የክልሎቹ ሰላምና መረጋጋት የመላው ሀገራችን ሰላም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሚዲያው ቁልፍና ገንቢ የማረጋጋት ስራ በመስራት ሰላም እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የበኩሉን ግዙፍ ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡