መልካም አስተዳደር የሚረጋገጠው በሁሉም ርብርብ ነው!
አባ መላኩ
አገራችን በፈጣን የለውጥ ዑደት ውስጥ ናት። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አገራችን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ ነች። መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ በአገራችን እየተመዘገበ ላለው ዘርፈ ብዙ ለውጦች ቀጣይነት የሚኖረው አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ነው። መልካም አስተዳደርን ማስፈን የአንድ ጀንበር ስራ ካለመሆኑም ባሻገር የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚጠይቅ ተግባር ነው።
መልካም አስተዳደር በማስፈን ረገድ ሲቪል ሰርቫንቱ ያለው አስተዋጾ እጅግ ወሳኝ ነው። በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በቅጥርም ሆነ በፖለቲካ ሹመኝነት ተመድቦ የመንግስትን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያስፈፅም የህዝብ አገልጋይ ወይም ሰርቫንት የሚል ብያኔ ይሰጠዋል። የሲቪል ሰርሻንቱ አስተዋፅኦ ለአንድ አገር ሁለንታናዊ ዕድገት የጀርባ አጥነት ነው። ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ከካፒታል ሃብት ባልተናነሰ መልኩ የሰው ሃብት (man power) ጉልህ ሚና ይጫወታል። መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚቻለው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በተጠያቂነትና ሃላፊነት መንፈስ ህዝብን ማገልገል ክብር ነው የሚል መንፈስ ሲላበስ ነው። ሲቪል ሰርቫንቱ በህዝብ ገንዘብ የተማረና ልምድ የቀሰመ በመሆኑ አገርንና ህዝብን በቅንነት የማገልገል ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ያለበት አካል ነው።
መንግስት ለህዝብ የሚያቀርበውን አገልግሎት ተደራሽ የሚሆነው በሲቪል ሰርቫንቱ አማካኝነት ነው። በመሆኑም በተሃድሶው ወቅት መንግስትና ህዝብ በጋራ ለለያቸው ችግሮች መፍትሄ በመሰጠት ላይ ነው። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩት በርካታ መሻሻሎች መሰረታቸው የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ የተደረገው ጥረት ነው። በሲቪል ሰርቫንቱ መንግስት የቀረጻቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አምኖ የመቀበል እንዲሁም በቅንነትና ታማኝነት አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነት አለበት። የሲቪል ሰርቫንቱ ህልውና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልካም አስተዳደር ከመረጋገጥ ጋር የተያያዘ ነው።
መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግሉ ሲቪል ሰርቫንት በርካታ እንደሆኑ ሁሉ አንዳንዶች ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተጣለባቸውን ሃላፊነት ተጠቅመው የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ እንዳሉ በቅርቡ ከየመንግስት መስሪያ ቤቱ በኪራይ ሰብሳቢነት ተጠርጥረው ተጠያቂ እየሆኑ ሲቪል ሰርቫንቶችን ተመልክተናል። እንደእኔ አንደኔ መልካም አስተዳደር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ግለሰቦች ለሰሩት ጥፋት ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ከማንገሱ ጎን ለጎን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በዘመናዊና አዳዲስ አሰራሮች መደገፍ መቻል ለመልካም አስተዳደር መስፈን ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው።
መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ውጤት ሊያመጡ የሚችሉት እያንዳንዱ ሲቪል ሰርቫንት የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት መወጣት ሲችል ነው። በመሆኑም በየደረጃው ያለው ሲቪል ሰርቫንት ህዝብን ማገልገል ድርብ ክብር መሆኑን ከመረዳት ባሻገር መልካም አስተዳደር መስፈን ለሲቪል ሰርቫንቱ ቀጣይ ህይወት መሰረት መሆኑን በመረዳት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡን በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ማርካት ይኖርበታል።
አብዛኛው ሲቪል ሰርቫንት የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ያለው፤ ህዝብ ሲጠቀም፣ እጠቀማለሁ፤ አገር ስታድግ አብሬ አድጋለሁ፤ የሚል አገራዊ ራዕይ ያለው ነው። ለዚህም ይመስለኛል ባለፉት 15 ዓመታት አገራችን ተከታታይነት ያለው ዓለምን ያስደመመ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው። ለአገራችን ዕድገት የሲቪል ሰርቪሱ አስተዋጽዖ እጅግ ወሳኝ ነው። ይሁንና አንዳንድ ሲቪል ሰርቫንቶች መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት ለግል ጥቅም ማካበቻ ሲያደርጉት ተመልክተናል።
የአብዛኛው ሲቪል ሰርቫንት መልካም ተግባር በጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዳበከል ጥፋተኞችን ለህግ አሳልፎ የመስጠት ባህላችን ሊዳብር ይገባል። እንደነዚህ ያሉ ሃላፊነት የማይሰማቸውን ስግብግቦች ከሲቪል ሰርቫንቱ የተደበቁ አይደለምና ለህግ አሳልፎ መስጠት ተገቢ ነው። መንግስት የሰው ሃብቱን በዕውቀትና ክህሎት እንዲሻሻል የተለያዩ የረጅም ጊዜ የትምህርት ዕድሎችን ለመስጠት ከሚያደርገግው ጥረት ጎን ለጎን የተለያዩ አጫጭር የስራ ላይ ስልጠናዎችንም በመስጠት ላይ ነው። ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። መንግስትም የሲቪል ሰርቫንቱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አቅም በፈቀደ ነገር ሁሉ እያደረገ ያለውን ጥረትም ማጠናከር ይኖርበታል። መንግስት የነደፋቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ የሚሆኑት በሲቪል ሰርቫንቱ በመሆኑ የዚህን አካል ችግሮች መቅረፍ ለአገር ዕድገት ያለው አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ ነው።
የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ አላቸው የምንላቸው የዓለማችን አገራትን ሁኔታ ስንመለከት ለዕድገታቸውና ለመለወጣቸው አብይ ምክንያት የሰው ሀብት በተለይም የተማረ የሰው ሃይላቸውን በአስተዳደር ጥበብና በተደረጀ መልኩ በመጠቀማቸው እንደሆነ ማየት ይቻላል። በርካታ የአውሮፓና የሩቅ ምስራቅ አገራት (ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ) እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሃብት ሳይኖራቸው ያላቸውን የሰው ሀብት በአግባብ መጠቀም በመቻላቸው እጅግ ውጤታማ መሆን ችለዋል። እነዚህ አገራት የሰው ሃብት ተጠያቂነት ያለው ሰርዓት ዘርግተው በየደረጃው ተግባራዊ በማድረጋቸውና ህዝብን በቀጥተኛ ተሳታፊ አንዲሆን በመስራታቸውና የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ስርዓት ዘርግተው በቁርጠኝነት ተግባራዊ በማድረጋቸው አገራቸውን ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል።
ዛሬ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት አላቸው የተባሉት በርካታ የአፍሪካ አገራት ያላስመዘገቡትን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አገራችን እያስመዘገበች ያለችው መንግስት በቀረጻቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሳቢያ ነው። እነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ደግሞ ተግገባራዊ የተደረጉት በዚህ ሲቪል ሰርቫንት መሆኑን ይታወቃል። በመሆኑም ሲቪል ሰርቫንቱ በተጠናከረ ቁጥር የመልካም አስተዳደር ችግሮችም እንደሚቃለሉ መታወቅ ይኖርበታል። አዳዲስ አደረጃጀቶችን በመጠቀምና ንቅናቄ በመፍጠር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል። ለዚህም ባለፈው አንድ አመት የተካሄዱ እንቅስቃሴዎች መልካም ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው።
ይሁንና አሁንም ሲቪል ሰርቫንቱን አደራጅቶና አቀናጅቶ ከመምራት አኳያ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ለአብነት አንዳንድ ሲቪል ሰርቫንቶች የለውጥ መሳሪያዎችን በተለይ አንድ ለአምስት አደረጃጀቶችን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ። አንድ ለአምስት አደረጃጀቶች የተሻለ ተሞክሮ የሚቀመርበት፣ ለጋራ ችግሮች በጋረ መፍትሄ የሚፈለግበት እንጂ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር አይኖርም። በሲቪል ሰርቫንቱ ውስጥ የአገልጋይነት መንፈስ እንዲጎለብት ማድረግ እንዲሁም ሲቪል ሰርቫንቱ ከህብረተሰቡ ጋር አብሬ እጠቀማለሁ የሚል አስተሳሰብ እንዲያጎለብት ማድረግ ተገቢ ነው።