Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መሠረተ ልማትና እመርታዎቹ

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መሠረተ ልማትና እመርታዎቹ

ዳዊት ምትኩ

የኢፌደሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በፓርላማ የመክፈቻ ንግግራቸው ከጠቀሷቸው በርካታ ጉዳዩች ውስጥ መሰረተ ልማትን አንዱ ነው። ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው አገራችን በመሰረተ ልማት ዘርፍ ረጅም ርቀት መጓዟን አመልክተዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ በኤሌክትሪፊኬሽን፣ በመንገድ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በኤሌክትሪፊኬሽንና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ከፍተኛ እመርታዎችን አስመዝግባለች። በተለይ በትራንስፖርቱ የመሰረተ ልማት ዘርፍ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የባቡር ዝርጋታን በማከናወን የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በዓለም ደረጃ ትላልቅ ከሚባሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ተርታ የሚሠለፈው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኘሮጀክት በራሳችን የፋይናንስ አቅም እና በአገር ውስጥ ተቋራጮች ተሳትፎ ጭምር ግንባታውን ተጀምሮ ከ60 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ ኘሮጀክቱ ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና በሂደት ከምንፈጥረው የኘሮጀክት አስተዳደር አቅም በተጨማሪ በመላ ሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የልማት መነሳሳት ፈጥሯል፡፡

1870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው የግቤ ሦስት ኘሮጀክት በዕቅድ ዘመኑ የሚጠናቀቅ ሲሆን የፊንጫ አመርቲ ነሺ፣ አሸጐዳ እና የአዳማ ኘሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰፋፊ የኤሌክትሪክ ኃይል የማከፋፈያ፣ ማሠራጫ፣ የማስተላለፊያ እንደዚሁም የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ሌላኛው የመሠረተ ልማት ኘሮግራም የትራንስፖርት ልማት ነው። በመንገድና በባቡር ትራንስፖርት አመርቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አራት የዕቅድ ዓመታት ወደ ተጨማሪ 12ሺ ኪ.ሜ ርዝመት ያላቸው የፌዴራልና የክልል መንገዶች የተገነቡ ሲሆን 40ሺ ኪ.ሜ የሚጠጋ የወረዳ መንገዶችም ተሠርተዋል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ጠቅላላ የመንገድ ርዝመት ከ100 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ደርሷል። ይኸም ወደ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ የገጠር ቀበሌዎች ክረምት ከበጋ በሚያስኬድ መንገድ እንዲገናኙ እና ክረምት ከበጋ የሚያስኬድ መንገድ ላይ ለመድረስ ያስቻለአፈፃፀም ነው፡፡

 

የኢኮኖሚ እድገታችን በተፋጠነ ልክ ይኸው ፍጥነት ከዚህ በበለጠ እንዲቀጥል ታዲያ ቀልጣፋና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የየብስ ትራንስፖት መሰረተ ልማት አገልግሎት እንደሚያስፈልገን እሙን ነው።

ሀገራችን ልትጠቀምባቸው ከምትችለው ዋና ዋና ወደቦች ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ያስፈልገናል፤ በአገር ውስጥም ዋነኛ የትራስፖርት ኮሪደሮችን የሚያገናኝ የባቡር መስመር እንደሚያስፈልገን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።

እንደሚታወቀው ቀደም ባሉት ጊዜያት ለባቡር ትራንስፖርት በቂ ትኩረት ስላልተሰጠውና የሚፈልገውም ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ፋይዳ ያለው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ላይ ደርሰናል። ይሁንና መንግስት ይህንን ሁኔታ ለመቀየር አቅም በፈቀደ መጠን በርካታ ስራዎችን እየከወነ ይገኛል።

እርግጥ አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የመንገድ ትራንስፖርትንና የባቡር ትራንስፖርትን በማቀናጀት ፈጣንና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የትራንስፖርት ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባን አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ይህን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚረዳው የኢፌዴሪ መንግስትም ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት የበለጠ ማረጋገጥ የሚያስችለውን የየብስ ትራንስፖርት ስርዓት ገንብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ይህ ዘርፍ ለሀገራችን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድ እየተኘበት የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር አንዱ ማሳያ ነው።

የዘርፉ ጠቀሜታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ አንጻር የሚጫወተው ሚና የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰዎችን በፍጥነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ማስቻሉም እንዲሁ፡፡ ባቡር በርካታ ስዎችን በአንዴ ከቦታ ቦታ ስለሚያንቀሳቀስ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ አኳያም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

የተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሚገኙባትንና ስብሰባዎች የሚሄዱባትን የመዲናችንን ውበትና ዘመናዊነት በመጨመር ረገድም አስተዋፅኦው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም እንዲሁ፡፡

የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በኤሌትሪክ የሚሰራ በመሆኑ ሀገራችን ለነዳጅ ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለመቆጠብ እንዲሁም የአየር ብክለትን በመከላከል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ በኩልም ጠቀሜታ አለው። በዚህም ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታከናውናቸው መሰል ግንባታዎች የሀገራችን ሰራተኞች የሚቀስሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ሙሉ በሙሉ የመስራት ችሎታቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ የባቡር መስመር ዝርጋታ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ የላቀ ሚና ይጫወታል ሲባል፤ ሽግግሩ ሀገራችን ለወጠነቻቸው የልማት ፕሮግራሞች ማሳኪያ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልጋት ለይቶ መጠቀም ወሳኝነቱ አያጠያይቅም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ በሂደት መቅዳት፣ መላመድና ማሻሻል በስተመጨረሻም ቴክኖሎጂውን በማመንጨት የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡

እርግጥ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ለመረዳት እንደሚቻለው የጎንዮሽና የቀጥታ የቴክኖሎጂ ማሸጋገርያ መንገዶች አሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን በመሰሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባው አካሄድ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡት ሀገራት ልምድ በመቅሰም የሚከናወነው የልማት ስራ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

እናም ፈጣን ለውጥ ለማምጣት መሰረታዊ የሚባለው የጎንዮሽ የቴክኖሎጂ ሽግግር በብዙ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የባቡር ዝርጋታ ፕሮጀክት ነው ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እየዋለ የሀገሪቱ ባለሙያዎች ትምህርት ይቀስማሉ፡፡

ለወደፊትም መሰል ፕሮጀክቶች በሀገራችን ሲገነቡ በእኛው መሃንዲሶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ሀገራችን ላለፉት 10 ዓመታት በተከታታይ ያስመዘገበችው የአስራ አንድ በመቶ አማካይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሀገሪቱ በ2025 ልትደርስበት ያሰበችውን የመካከለኛ ገቢ ጎራ ካላቸው ሀገራት የመቀላቀል ዕድልን መደላድል እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይም የሀገራችንን ከተሞች፣ ክልሎችንና አጎራባች ሀገሮችን የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶች ለዚህ ትልም ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡

በኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ እና በባቡር መስመር ዝርጋታ እየተደረጉ ያሉ ሰፊ መሰረት ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ያለ ምንም እንቅፋት እየተከናወኑ ናቸው፡፡ በተለይም በትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንደ ባቡር ዓይነት በፍጥነት ግዙፍ የሆነን ሎጀስቲክካዊ አቅርቦት ወደ ተፈለገበት ቦታ የሚያደርስ ዘርፎችን እየገነባች መሆኗ አገልግሎቱ አገልግሎቱ የወጭ ንግድን በመደገፍ ረገድ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የተገኙት እመርታዎች እንዲሁ በተመጋጋቢነት የአገራችንን እድገት የሚያሳልጡ ናቸው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy