Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መፍትሔ የሌለው ችግር የለም!

0 503

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መፍትሔ የሌለው ችግር የለም!

                                                                 ደስታ ኃይሉ

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ነበራዊ ጉድለቶችን የሚያረምና ለዘለቄታው ማስተካከል የሚችል ነው። ሥርዓቱ ሌላው ቀርቶ ለጥቃቅን ችግሮች የሚሆን ክፍተት የማይሰጥ፣ ምናልባትም ችግሮች ከተስተዋሉ በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል አቅም አለው። ይህም አገራችን የምትከተለው ሥርዓት ራሱን በራሱ ከማረም ባለፈ ለህዝቦች አንድነትና መተማመን ዋስትና መሆኑን ያሳያል።

አገራችን በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መፍትሔ የሌለው ችግር የለም። ሁሉም ጊዜያዊ ችግሮች በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈቱ ናቸው። የየራሳቸውም አሰራር አላቸው። ይህ አሰራርም ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታና የህዝቦችን አብሮነት ይበልጥ የሚያጠናክር እንጂ የሚያላላ አይደለም።

ፌዴራሊዝም በተለያዩ የፖለቲካ ክፍሎች ስር የሚኖር፣ ነገር ግን የጋራ ቋንቋና ባህል ያለውን ህዝብ ወይም በጋራ የፖለቲካ ክፍሎች ውስጥ በአባልነት የመሳተፍን ጥቅም የሚፈልግ ነገር ግን በቋንቋና በባህል የሚለያይ ህዝብን አንድ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በፌዴራሊዝም የሚፈጠረው የአንድነት ውጤት በፌዴሬሽኑ የተካተቱ የአባል መንግስት መስተዳድሮችን የተለየ መሆን የሚያዋህድ ወይም የሚያጠፋ ሆኖ መወሰድ አይኖርበትም።

ፌዴራሊዝም አንድነት የሚያራምደው ፌዴሬሽኑን ያቋቋሙትን አካላት የተለየ ማንነት የራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን፣ እንዲሁም ለጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ መስተዳድራቸው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚወከሉበትንና የሚሳተፉበትን ተቋማዊ ማዕቀፍ በህገ-መንግስት ዋስትና የሚሰጥ የስርዓት አወቃቀር ነው። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ፌዴራሊዝም የሚያልመው በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ አንድነትንና ህብራዊነትን በመጠበቅና በመኮትኮት ዓላማ ያለው በመሆኑ ነው። በዚህም በፌዴራላዊ ስርዓቱ የጋራ እሴቶችን እና ሁሉ አቀፍ ማንነትን መገንባት ይቻላል።

ፌዴራሊዝም ከውጭ የሚመጣ ወታደራዊ ጥቃትን ወይም የጦርነት ስጋትን በመከላከል ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋጥ የሚረዳ ስርዓት ነው። በተሳካላቸው ፌዴሬሽኖች ጀርባ ፌዴሬሽኖቻቸው በተመሰረቱበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ይህ ጥቃትንና ስጋትን በጋራ የመከላከል እሴት ይስተዋላል። ለምሳሌ በአሜሪካ የውጭ ጥቃትን ወይም የጦርነት ስጋትን በጋራ የመመከትና ሰላምና ፀጥታን ማስፈን ዓይነተኛ የፌዴራሊዝም እሴት ሆኖ አገልግሏል። በአሜሪካ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ የነበሩት መንግስታት ፌዴሬሽንን ያቋቋሙት አንዱ አብይ ምክንያታቸው ከውጭ ሊቃጣባቸው የሚችሉ ጦርነቶችን እና የጦርነት ስጋቶችን ለማምከንና ለመከላከል ጠንካራ የመከላከያ አቅም ለመፍጠር በማሰብ ነው።

በሌላ ምሳሌ ደግሞ ህንድንና ቤልጂየምን የመሳሰሉ ከዚህ ቀደም አሃዳዊ የመንግስት የፖለቲካ ስርዓት የነበራቸው ቢሆኑም፣ በውጭ ከሚመጣ ወይም ሊመጣ ይችላል ተብሎ ከሚገመት ስጋት ሳይሆን፣ በውስጣቸው ያሉት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ልዩነቶች ባላቸው ሕዝቦች የእኩልነት፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት የመሆንና የመጋራት ጥያቄዎችና ትግሎች አማካኝነት ወደ ፌዴራላዊ የመንግስት የፖለቲካ ስርዓት ሊሸጋገሩ መቻላቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።

እርግጥ እነዚህ ሀገራት ፌዴራሊዝምን ለመምረጥ የተገደዱበት ምክንያት ስንመለከተው ከውስጣቸው በተፈጠሩት ኃይሎች አማካኝነት አንድነታቸው እንዳይሸረሸርና እንዳይጠፋ ለመከላከል በማሰብ ሆኖ እናገኘዋለን። ያም ሆነ ይህ ግን በሁለቱም ምሳሌዎቻችን ፌዴራሊዝም ለተጠቀሱት እሴቶች ማራመጃ ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግል የፖለቲካ ስርዓት መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

ፌዴራላዊ ስርዓት ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣንና ነፃነትን በህገ-መንግስት መሰረት በመስጠትና በማቋቋም በፌዴሽኖች ውስጥ ያሉት የመንግስት መስተዳድሮች በየአካባቢያቸው ካሉት ህዝቦች ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣሙ የፖሊሲ አማራጮችን እንዲቀርፁና የአካባቢ ባለስልጣናት ለየአካባቢያቸው ህዝብ ቅርብ እንዲሆኑ በማድረግ የህዝብን ፍላጎቶች እያዳመጡ ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል። እንዲሁም የፌዴራሊዝም አደረጃጀት ለፈጠራ ስራዎች በተወሰኑ አካባቢዎች ለፖሊሲ ሙከራዎች ዕድሎችን በመፍጠር በማህበረሰቡ ውስጥ የላቀ ጠቀሜታን ይፈጥራል። በተለያዩ የስልጣን ማዕከላት መካከል በሚኖረው በጎ ፉክክሮች ፈጣንና ጠቃሚ ውጤቶች እንዲገኙም በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ፌዴራሊዝም በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊኖሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ልዩነቶችን በማቻቻል አብሮ ለማራመድ እና ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በሚፈጠሩበት ውቅት ችግሮቹን ለማርገብ አግባብነት ያለው የፖለቲካ ስርዓት ነው። በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩና ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን ለመቀነስ ፌዴሬሽኖች ብዙ የመንግስት ስልጣን ማዕከላትንና የፖለቲካ ምህዳር (political space) ስላላቸው ለሰላማዊ ድርድር ምቹ ተቋማዊ ማዕቀፍ ይፈጥራሉ። ይህም የፌዴራላዊ ስርዓት ዋነኛው ጠቀሜታ ነው ተብሎ በመስኩ ምሁራን ይገለፃል።

ከዚህ በተጨማሪም ፌዴሬሽኖች ብሔሮች ብሔረሰቦና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና የጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ የማስተዳደር ለጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ የማስተዳደር መብት ዋስትና በመስጠት የብሔር ብሔረሰብ እና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ተቋማዊ መሰረት አላቸው።

ፌዴራሊዝም ከአብዛኛው ብሔር እኩል የመወሰን ነፃነት ስሜት እንዲሁም በአካባቢያዊ ጉዳዮች ስልጣን በመስጠት በአንድነት በባለ ብዙ ብሔር ሀገር ውስጥ ዕውን እንዲሆን ያስችላል”  በማለት ገልፀውታል። ይህ አባባል እንደ ሀገራችን ባሉ እጅግ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላሉ ሀገራት በአንድነት የተሳሰረን ህዝብ በአንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብነት ለማስቀጠልና የሚፈጠሩ የማህበራዊ መስተጋብር ግጭቶችን በመቻቻል ምህዳር ለመፍታት ፌዴራላዊ ስርዓት ጠቀሜታው እጅግ የላቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው።    

የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አገር የሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለሁሉም ህዝቦች ህገ መንግስታዊ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንና ውክልናን ማረጋገጥን፣ የውጭ ጥቃትን በጋራ መመከትን፣ ፈጣን ኢኮኖሚን ማምጣትን፣ የሚፈጠሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባራዊ ግጭቶችን መፍታትን እና የጋራ ኢኮኖሚያዊ አንድነት መፍጠርን…ወዘተ. ጠቀሜታዎች አስገኝቷል።

ይህ ተጨባጭ በፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ ዕውን የሚሆኑ ጥቅሞች እስካሉ ድረስ፤ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እያረመና ከህዝቦች ፍላጎት ጋር እየተራመደ ሊፈጠሩ ለሚችሉ ማናቸውም ነባራዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ መሆን እንደሚችል የሚያረጋግጥ ነው። የአገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት ለሁሉም ችግሮች መፍትሔዎች ያሉት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ራሱን በራሱ እያረመ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታና ይህንንም ክህሎት ያዳበረ ጭምር ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy