ethiopian news

Artcles

“ራዕይ ሰንቀናል፤ ለላቀ ድል ተነስተናል”

By Admin

October 10, 2017

“ራዕይ ሰንቀናል፤ ለላቀ ድል ተነስተናል”

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

የፊታችን ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በመላው ሀገራችን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለአስረኛ ጊዜ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ዕለቱ “ራዕይ ሰንቀናል፤ ለላቀ ድል ተነስተናል” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፤ ሰንደቅ ዓላማው ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለው ትርጉም ምን እንደሆነ የሚዘከርበት ነው። የሀገራችን ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ከፍተኛ ተግባሮችን ፈፅመዋል።

ርግጥም የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ…ከፍ በማለት ላይ የሚገኘው፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት አንገታቸውን ሲያስደፋ የነበረውን ድህነትን ለመቅረፍና በአዲስ የህዳሴ ጉዞ ለመጓዝ እያደረጉት ባለው ብርቱ ጥረት ነው። በዚህም የሀገራችን ህዝቦች በተለይ ላለፉት አስር ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በየመስኩ ተሰልፈዋል። ይህ የሆነውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዴሞክራሲያዊ አንድነቱ መገለጫ በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ስር ተሰባስቦ ልማቱንና ዕድገቱን ማፋጠን ስለቻለ ነው።

የሰንደቅ ዓላማ ምንነት ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ጥልቅ ትርጉሞች አሉት። አንድም ከታሪካችን ጋር የሚያይዘው ዕውነታ ስላለ፣ ሁለትም ከብዝሃነታችን ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ስለሆነ ነው።

ከታሪክ አኳያ ስንነሳ፤ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን  የሀገራችንን የግዛት አንድነት ለማስከበርና ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪዎች ለመታደግ እንደ አንድ ሰው በመሆን በዱር በገደሉ ያካሄዱትን ተጋድሎ ዕውን ያደረጉት በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው ነው።

የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከብዝሃነታችን አኳያም ስንመለከት፤ በሰለጠነው የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት የዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው መገለጫ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።  በልዩነታችው ውስጥ ያለው አንድነታቸው ሁነኛ ማሳያም መሆኑ እንዲሁ።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማው ስር ሆነው አንዱ የሌላውን ማነነት እንዲያውቅ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩ ስራዎችን አከናውነዋል። በተለይም ያለፉት ፊውዳላዊና ጨቋኝ ስርዓቶች በህዝቦች መካከል ጥለዋቸው ያለፉት ቁርሾዎችና ጠባሳዎች እንዲሽሩ፣ የመፈቀቃቀድና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲጎለብት፣ ልዩነታቸው ተጠብቆ በሚያስተሰስሯቸው እጅግ የበዙ ታሪካዊና ነባራዊ ጉዳዩች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጉ ስራዎችን ገቢራዊ አድርገዋል።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም የገዘፈ ነው። በቡድንም ይሁን በግል አሊያም በሀገር ደረጃ የሚሰራ ማናቸውም ጉዳይ ያለ አንድነት ዕውን ሊሆን አይችልም። አዎ! በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል።

አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖር ነው። የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፅኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅና የብዝሃነታችን ጥላና ከለላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይደለም። ሁሉም ያውቀዋልና።

ሆኖም አንዳንድ ወገኖች በስሜት ተገፋፍተው ሰንደቅ ዓላማውን ዝቅ ለማድረግ ሲሞክሩ ይስተዋላል። ይህ ተግባር እጅግ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁትን ሀገ መንግስት መፃረር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው በተለይ ከዕድሜው አኳያ ለነገሮች ሁሉ ችኩልና ለጊዜያዊ ስሜቶች ቅርብ የሆነው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በማወቅም ይሁን በፀረ ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች አሉባልታ ተገፋፍቶ ባለማወቅ የሰንደቅ ዓላማውን ጥቅም ካለመረዳት ይህን መሰሉን ተግባር ይፈፅማሉ። ይህ የለየለት የህዝቦችን ፍላጎትና ህግን የመፃረር ድርጊት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ፀረ-ሰላም ሃይሎችና እዚህ ሀገር በተጨባጭ በመምጣት ላይ ያለውን ለውጥ የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች በሰልፍ ሰበብ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ለማኮስመን ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ የህዝቦች አንድነትና እኩልነት የሆነውን መሰረታዊ ጉዳይ አለመቀበል በመሆኑ ከህገ መንግሰቱ ጋር የሚጣረስ ነው። ተቀባይነትም የለውም።

ርግጥ የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅ መሰባሰቢያ ጥላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ አይካድም። እናም የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ጠብቀው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን እነዚህ ወገኖች ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል።

በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሰረት አድርጎ በመቁጠር በሰንደቅ ዓላማው ስር ተጠልሎ ድህነትን ለማሸነፍ ላለፉት ዓመታት ታግሏል። የትግሉ ባለቤትም በመሆን ላይ ይገኛል። ለዚያውም ከዓለም በፈጣን ዕድገት ከቻይና እና ከህንድ ቀጥሎ የልማት ተምሳሌታዊ ማማውን ከፍታ ላይ ሰቅሎ።

እናም ድሉን ይበልጥ ለማጠናከር የሚችልበትን በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከአንዴም ሁለቴ ተልሞ ወደ መከከለኛ ገቢ የመገስገስ ራዕዩን ተያይዞታል። ይህ ህዝብ የተናገረውን የሚፈፅም በመሆኑ በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስቦ ራዕዩን እውን አንደሚያደርገው በርግጠኛ መናገር የሚቻል ይመስለኛል።

ሰንደቅ ዓላማችን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የተቀየሰው ህዳሴ መሰረትም ነው። ከዚህ አኳያም ሀገራችን በምጣኔ-ሃብት እንድታድግ፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ብሎም በርካታ ተግባራት ገቢራዊ ሆነው ውጤት ተገኝቶባቸዋል።

የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የሀገራችን ህዝቦችና ሃይማኖቶች አንድነትና እኩልነት መገለጫ በመሆን ዜጎች በስሩ ተሰባስበው ዛሬ ላይ ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ነው። ስለ ሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሲነሳ፤ ጉዳዩ አንድነት ፈጣን ልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማስገኘት አኳያ ያለው ፋይዳም ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው በየትኛውም ሀገር ውስጥ በቡድንም ይሁን በሀገር ደረጃ ከአንድነት ውጪ የሚከናወን ምንም ዓይነት ነገር የለም። አዎ! አንድነት ሲኖር ፈጣን ልማትና የተሻለ አቅም መፍጠር ይቻላል። አንድነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የህዝቦች ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችለው እኩልነትና መፈቃቀድ ሲኖሩ ይመስለኛል። እናም እነዚህ እኩልነቶች ደግሞ በሰንደቅ ዓላማው ስር በመሰባሰብ የተገኙ ናቸው። በጥቅሉ የሀገራችን ህዝቦች “ራዕይ ሰንቀናል፤ ለላቀ ግብ ተነስተናል” በማለት ለአስረኛ ጊዜ የሚከበረውን የሀገራችን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታችን አኳያ በመመልከት ለላቀ ድል መነሳት ይኖርብናል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማውን በስሜት ተገፋፍቶ መቃወም ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህን ሁሉ ሀገራዊ ጥቅሞች መፃረር፣ የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎቶችን መቃወም፣ በዓለም ላይ አሉ የተባሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለሁሉም ሀዝቦች በእኩልነት የሰጠውን ህገ መንግስት በህገ ወጥነት ተፃርሮ መቆም መሆኑን መረዳት የሚጠቅም መሆኑን ሳልገልፅ አላልፍም።