Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰንደቃችን …

0 281

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰንደቃችን …

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

የሠላምና የልማት መሠረት ፌዴራላዊ ሥርዓት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ በድምቀት ተከብሯል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትም የአገሪቱ የሠላምና የልማት መሠረት ሆኖ ቀጥሏል።

10ኛው የኢፌዴሪ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመከባበርና በእኩልነት በህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ አገር በፈቃዳቸው መሥርተው ሊኖሩ ቃል ኪዳናቸውን የሚያድሱበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዘውዳዊውና ከአምባገነናዊው ወታደራዊ  ሥርዓት ነጻ ለመውጣት የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው ታግለዋል። በዚህም የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። በዚህ ምክንያት የአኃዳዊ ሥርዓቶቹ ሰንደቅ ዓላማ የነጻነታቸው ምልክት ሳይሆን ቀርቷል። የዛሬው ሰንደቅ ዓላማ ግን ይህን ሁሉ ጭቆናና ሥቃይ መጥፎ ጠባሳ ትቶ ዜጎች በአዲስ መልክ ተከባብረውና በእኩልነት ግንኙነት በጋራ የመኖር ዓላማን የሰነቁበት ሆኗል።

ከወታደራዊው የደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተነጣጥለው የየራሳቸውን ነጻ መንግሥት ከመመሥረት ይልቅ አንድ የጋራ አገር መሥርተው ለመኖር ከስምምነት የደረሱበት ነው። በዚህ ወቅት ታዲያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባፀደቁት ህገ መንግሥት ራሳቸውን እያስተዳደሩ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የህዝቦች አንድነት ያላት ፌዴራላዊት አገር መሠረቱ።

ባለፉት ሥርዓቶች በጭቆና ሥር ይኖሩ የነበሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጭቆና የዳረጓቸው አኃዳዊ ሥርዓቶች ሲጠቀሙበት የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ የፌዴራላዊው መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ሆኖ እንዲያገለግል አልፈቀዱም። ፍላጎትም አልነበራቸውም። አንድ አድርጎ የሚያስተሳስራቸውን ሰንደቅ ዓላማ መረጡ።

ዜጎች መልካም ታሪካቸውን መነሻ በማድረግ የፌዴራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ መሠረቱን ቀድሞ የነበረውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ እንዲሆን ከስምምነት ደርሰዋል።  ሰንደቅ ዓላማው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የተለያዩ ኃይማኖቶች የተጎናፀፉትን ነጻነት፣ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያላት አገር መመሥረታቸውን የሚያንፀባርቅ ዓርማ እንዲታከልበት ተስማምተዋል። በህገ መንግሥቱ ላይም በዝርዝር እንዲህ ቀርቧል።  

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 3 “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ” በሚል ርዕስ ሥር፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመካከሉ ብሄራዊ ዓርማ ይኖረዋል (ኮከብና ጨረር)። ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው አግድም ይቀመጣሉ ይላል። እንዲሁም ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሄራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ኃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል። ይላል።

የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 በአንቀጽ 5 የሰንደቅ ዓላማ ምንነት በሚል ርዕስ ሥር ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የህዝቦች በመፈቃቀድደ ላይ የተመሠረተ አንድነት መገለጫ ነው በሚል አስፍሯል።

እዚህ ላይ ህገ መንግሥቱን ተከትሎ በ1988 ዓ.ም. በቁጥር 16/1988 “የሰንደቅ ዓላማና ዓርማ አዋጅ” እንዲወጣ መሠረት ተጥሏል። ምሥጋና የህይወት መስዋዕትነት ገብረው  ሰንደቅ ዓላማውን ላስረከቡን ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ክብርና ሞገስ ይድረሳቸው።  

እናም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰማዕታቱን አደራ ተቀብለው በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ሥር ተሰባስበው አያሌ አገራዊ ተግባራትን ከውነዋል። ሁለገብ ለውጥን በማምጣት ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል። ሰንደቅ ዓላማውን የማንነታቸው መገለጫ በማድረግም በአንድነትና በእኩልነት ጉዛቸውን ቀጥለዋል።

የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠበት ፌዴራላዊ ሥርዓት የብሄር ቅራኔን በመፍታት በአገሪቱ ሠላም እንዲረጋገጥ አድርጓል። አልፎ አልፎ ከወሰን ይገባኛል፣ ከማንነትና ከአስተዳደር ጥያቄ ጋር በተገናኘ አለመግባበቶችና ግጭቶች ሲያጋጥሙ የቆዩ ቢሆንም፣ እነዚህ ሁኔታዎች ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ የመነጩ ሳይሆኑ የአፈጻፀም ችግር ውጤቶች ናቸው።

የፌዴራላዊው ሥርዓት ህገ መንግሥት የዚህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍታት የሚያስችል ሥርዓት አለው። ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ሠላም ማረጋገጥ የተቻለውም በዚሀ ሁኔታ ነው።

ይህ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተረጋገጠው ሠላም፣ ህዝቡ ትኩረቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ዕድል ፈጥሮለታል። ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ሥጋት ሳያድርባቸው መዋለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ እንዲያውሉ አግዟቸዋል። የውጭ ባለለሃብቶች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ የሚስብ ዋስትናም ፈጥሮላቸዋል። እነዚህ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያረጋገጣቸው ዋስትናዎች ናቸው። በዚህም አገሪቱ በአማካይ ባለሁለት አኃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስመዝገብ አስችሏታል።  

የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነት መገለጫ ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ኃይማኖቶችና ቋንቋዎች የሚገኙባት ናት። ባለፉት ዓመታት ይህን ልዩነት እንደ ጥንካሬ በመውሰድ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት የተፈጠረው ብሎም ብጥብጥና ሁከት ውስጥ እንዳትገባ ማድረግ የተቻለው ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችልና ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ ስለተቻለ ነው። ለዚህም ደግሞ መቋጫው ህገ መንግሥቱ ነው።

እርግጥ በህገ መንግሥቱ ሣቢያ ሁሉም ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማለትም የግልና የቡድን መብቶች በተቀናጀ መልኩ አንዱ የሌላውን በሚደግፍ መልኩ ምላሽ አግኝተዋል። በዚህም ብዝሃነትን ለማስተናገድ ችግር ሆነው የቆዩ አያሌ ጉዳዮች ምላሽ አግኝተዋል። ይህ ሁኔታ መፈጠሩ ነው አገሪቱ ለተከታታይ ዓመታት በፈጣን የዕድገት ጉዞ ላይ ለመገኘት ያበቃት።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ አገራዊ ውጤታማነት ሊመዘገብ የቻለው የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግሥታቸው እየተመሩ ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በሰንደቅ ዓላማው ሥር መሰባሰብ በመቻላቸው ነው። ሌት ተቀን በመሥራት ውጤቱ መመዝገቡን ማየት ተችሏል።

በሁሉም አቅጣጫ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሠረት አድርጎ በመቁጠር በ‘ሰንደቅ ዓላማው’ ሥር ተጠልሎ ድህነትን ለማሸነፍ ለዓመታት ታግሏል። የትግሉ ውጤት ተቋዳሽም እየሆነ ይገኛል – ከዓለም በፈጣን ዕድገት ላይ ከሚገኙ ጥቂት አገሮች ረድፍ በመሰለፍ። ዛሬም ኢትዮጵያዊያን በሰንደቅ ዓላማቸው ሥር በአንድነት ቆመው ወደ መከከለኛ ገቢ የመገስገስ ራዕያቸውን ሰንቀው ጉዟቸውን ቀጥለዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy