Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰንደቃችን ሥር ተሰባስበን  ህዳሴያችንን …!

0 439

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰንደቃችን ሥር ተሰባስበን  ህዳሴያችንን …!

ወንድይራድ  ኃብተየስ

ኢትዮጵያዊያን  ለሰንደቅ ዓላማቸው ልዩ ክብርና ፍቅር አላቸው። ኢትዮጵያዊያን  ከቀድሞ ጀምሮ በሰንደቅ ዓላማቸው ስር ተሰባስበውም የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደጎን በማለት የአውሮፓ ወራሪ ሃይሎችን  በአድዋ ተራሮች ዙሪያ  ድል በመንሳት ጊዜ የማያደበዝዘው ታሪክ በደማቅ  ቀለም  መጻፍ ችለዋል።  የዛሬው ትውልድ ደግሞ በሰንደቁ ስር በመሰባሰብ  ድህነትን ትርጉም ባለው ሁኔታ  በመዋጋት ተጨባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ ነው። የዚህ ትውልድ ታሪክ ሲወሳ የሚኖረው በድህነት ላይ የተጀመረውን ትግል በማጠናከር  የአገራችንን  ህዳሴ ማሳካት ሲቻል ነው።  

 

ባለፉት 14 ዓመታት አገራችን በዓለም ዓቀፍ  ደረጃ  እውቅናን ያተረፈ ባለሁለት አሃዝ  ፈጣን ልማት በማስመዝገብ ላይ ነች። የተጀመረውን  ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥና የአገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ መንግስት የሃይል አቅርቦትን ለማሳደግ በርካታ ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ላይ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከሃይል ማመንጫነቱ ባሻገር ህዝቦችን በአንድ ጥላ ስር ማሰባሰብ የቻለ ፕሮጀክት ነው።  ታላቁ የኢትዮጵያ  የህዳሴው ግድብ  ፕሮጀክት የኢትዮጵያን  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በጋራ ያስተሳሰረ የአንድነት ገመድ፣ የአብሮነታቸው መገለጫ የሆነ ፕሮጀክት ነው።   

 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለበርካታ አፍሪካዊያን የነጻነት ምንጭ ተደርጋ ትወሰዳለች።  ለዚህም ጥሩ ማረጋገጫ የሚሆነው የበርካታ  የአፍሪካ  አገራት  ከነጻነት ብኋላ የሰንደቅ ዓላማቸው ቀለማት ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ተቀራራቢ መሆናቸው ናቸው።  በቅኝ ግዛት ወቅት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለመላው ጥቁር ህዝቦች እንደ ነፃነት ምልክት  እንዳገለገለች ሁሉ  ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም አፍሪካዊያን በራሳቸው  ዕቅድ በራሳቸው  አቅም ትልቅ ነገር መስራት እንደሚችሉ ያመላከተ ፕሮጀክት ነው።

ከአፍሪካ አንድነት ምስረታ እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህዝቦች ጥቅም  የቆመች ግንባር ቀደም አፍሪካዊ አገር  ነች ቢባል የተጋነነ ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያ  አፍሪካዊያን ከቅኝ  ግዛት  እንዲላቀቁ ለነጻነት ተዋጊዎች ስልጠና፣ የሎጀክስትክ አቅርቦት እንዲሁም በዲፕሎማሲው ረገድም የአፍሪካዊያን ድምጽ በመሆን ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክታለች። ኢትዮጵያ  ለአፍሪካ ህብረት  መጠናከርና ስኬት  የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ላይ ነች። ባለፉት 26 ዓመታት ብቻ የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በስድስት የአፍሪካ አገሮች ማለትም በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን ዳርፉር፣ ደቡብ ሱዳን በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በሶማሊያ ለህዝቦች ሰላም መረጋገጥ ውድ ህይወታቸውንና አካላቸውን መስዋዕት በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ ነው በተግባር  ለአፍሪካ  ጥቅም መቆም!

 

አሁን ላይ ደግሞ  ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን መጠጊያ መሸሸጊያ በመሆን ላይ ነች።  አሁን ላይ  ምዕራባዊያን በተለይ አውሮፓዊያን ለስደተኞች በራቸውን በዘጉበት ወቅት እንኳን  ኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ሚሊዮን  ለሚጠጉ  አፍሪካዊያን  ስደተኞችን መጠጊያ አምባ  ሆናለች። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አገራት  ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በኢኮኖሚ ጥቅም እንዲተሳሰሩ ጠንክራ በመስራት ላይ ነች። ኢትዮጵያ በርካታ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ከአካባቢው አገሮች ጋር በመተሳሰር ላይ ነች።  ኢትዮጵያ የቀጠናው አገሮች  በኢኮኖሚው ጥቅም እንዲተሳሰሩ ከምታደርገው ጥረቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱ ተጠቃሽ ፕሮጀክት ነው።  

 

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በዋነኝነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠውን  ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ይሁን እንጂ  የጎረቤት አገሮች በተለይ የሃብቱ ቀጥታ ተጋሪ የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ከዚህ ፕሮጀክት የሚያገኙት ጠቀሜታ ቀላል የሚባል አይደለም። አገራችን እየገነባቻቸው ካሉት ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች  ፍላጎቷን ካሟላች ብኋላ ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ የሃይል ምንጭ ማቅረብ ነው።  ከዚህም ባሻገር  የህዳሴው ግድብ የወንዙን ስነምህዳራዊ ሁኔታ መጠበቅ ስለሚያስችል በትነት የሚባክነውን ውሃ ይቀንሰዋል።   

 

በየወቅቱ  የሚዋዥቀውን የወንዙን  የፍሰት መጠን በማስተካከል  ዓመቱን ሙሉ የተስተካከለ ፍሰት እንዲኖረው ያደርጋል። ከዚህም ባሻገር የህዳሴው ግድብ በታችኛው የተፋሰስ አገራት በተለይ በሱዳን ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ የመከላካል ጉልህ ሚና ይኖረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ህዝባዊነቱን በተግባር አሳይቷል። የሚገነቧቸው የልማት ስራዎች ሁሉ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም ባሻገር ለቀጠናው አገራት የሚበጁ ሆነዋል።

 

ኢትዮጵያ አባይን በተመለከተ እየተከተለችው ያለው መርህ  “የወንዙን ውሃ እኩል ተጠቃሚነት”  የሚል  ሳይሆን   “ፍትሃዊ ተጠቃሚነት” የሚል ነው። ይህ የሚያመላክተው ሌሎች ሳይጎዱ እኛ እንጠቀም ነው።  የትኛውም የተፋሰስ አገራት እስካሁን አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት  የታላቁን  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  በታችኛው አገሮች ላይ የሚያሳድረው ጫና በገለልተኛ አካል እንዲገመገም አድርጓል። ይህ በራሱ የሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግስት በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያለውን መተማመን ነው።  እውነት እንነጋገር ከተባለ  ግብጽም ሆነች ሱዳን በአባይ ላይ በርካታ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውኑ ለላይኞቹ የተፋሰስ አገራት  ፕሮጀክቶቻቸውን ማስገምገም ይቅርና  አሳውቀው አያውቁም። ይህ ነው ለሌሎች ማሰብ። ይህ ነው ህዝባዊነት።   

 

ግብጻዊያን የታላቁን የህዳሴ ግድብ  ለማጨናገፍ  በማስፈራራትም፣  በማግባባትም እንዲሁም በሶስተኛ አካልን በመጠቀም ኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ  የተለያዩ  ተግባራትን ሲከተሉ ነበር። ሁሉም ጥረቶች አልተሳኩም። ታላቁ የህዳሴው ግድብን  ለማስቆም ምንም አይነት ሙከራዎች ስኬታማ  ሊሆኑ አይችሉም። ምክንያቱም  ታላቁ የህዳሴ ግድብ  የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበትና ህዝባዊ ድጋፍ ያለው ፕሮጀክት በመሆኑ ነው።  ይህ ፕሮጀክት  ግንባታው ሊጠናቀቅም ሆነ ሊቋረጥ  የሚችለው በኢትዮጵያዊያን  ፍላጎት ብቻ መሆኑን ግብጻዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን በመረዳታቸው አሁን ላይ ከጥፋት ድርጊታቸው ተቆጥበው  ከኢትዮጵያ መንግስት  ጋር መነጋገርና መወያየት ብቸኛው አማረጭ መሆኑን የተረዱ ይመስላሉ።

 

ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ መንግስት ህብረተሰቡን ማስተባበር ስለቻለ  ፕሮጀክቱ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ  ደም ውስጥ እንዲሰርጽ በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የእኔነት ስሜት እንዲዳብር አድርጓል።  የህዳሴው ግድብ  በህዝቦች ውስጥ “የእንችላለን” ስሜት እንዲጎለብት እንዲሁም ህዝብና መንግስትን የበለጠ እንዲተሳሰሩና እርስ በርስ እንዲናበቡ አድርጓቸዋል። አሁን ላይ  እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊያን በለገሳት ጠብታ ድጋፍ ታላቁ ግድባችንን  እውን ወደማድረግ እየተቃረብን ነው። “ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንደሚባለው  በመተባበራችን በታዳጊ አገር አቅም  አይታሰብም የተባለ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እውን ለማድረገ በመቃረብ ላይ ነን። አሁንም ድጋፋችንን በማጠናከር ፕሮጀክቱን ማጠናቀቅ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።

 

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ድሮ እንደሚያስቧት ደካማ፣ በቀላሉ የምትከፋፈል፣ ይህን አድርጊ ይበጅሻል፣ ይህ ደግሞ ይቅርብሽ አይጠቅምሽም እየተባለች እንደ አሻንጉሊት የምትበጃጅ አገር አይደለችም።  እኛ ኢትዮጵያዊያን  የሚያዋጣንንና የማያዋጣንን በራሳችን መወሰን የምንችልበት ጠንካራ ህዝባዊ መንግስት ያለን ዜጎች ነን።  በአገራችን ታሪክ እስካሁን ከታዩ የልማት ፕሮጀክቶች እንደ ህዳሴው ግድብ ያለ  የህዝብን ቀልብ የገዛና የሁሉም ህዝቦች አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት አልታየም። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ  የአገራችንን ገጽታ የሚቀይር በህዝቦች መካከል “የይቻላል” ስሜት የፈጠረ  ፕሮጀክት በመሆኑ የልማት ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች መለያ ብራንድ ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ ጉዳይና  በብሄራዊ ጥቅማችን ዙሪያ ያለንን ጥንካሬ የበለጠ ማጎለበት ይኖርብናል።  ወዳጆቻችንና የልማት አጋሮቻችን ጭምር  “አይቻልም”  ያሉትን ፕሮጀክት  60 በመቶ በላይ አድርሰነዋል።  ይህን አገራዊ ፕሮጀክት  ከዳር ለማድረስ እስካሁን ስናደርግ የነበረውን  ሁሉን አቀፍ ድጋፍ  የበለጠ ማጠናከር እንድንችል በሰንደቅ ዓላማችን  ሥር  መሰባሰብ ይገባናል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy